አሰገደች የልብስ ስፌት ሥራ ድርጅት
አሰገደች የልብስ ስፌት የተመሰረተው በ 2005 ዓ.ም ሲሆን ድርጅቱ ሲመሰረት በሦስት መስራች አባላት እና በሦስት የልብስ ሲፌት ማሽኖች ነበር። ድርጅቱ በተመሰረተበት ወቅት ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደ ነበሩ ወ/ሮ አሰገደች ይናገራሉ። እንዲያም ሆኖ፣ እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቋቋሙ የዘለቀው ድርጅት በተሻለ ደረጃ ምርት ማምረት የጀመረው በ2009 ዓ.ም ነበር።
ከ2009 ዓ.ም በፊት መሰናክሎቹ ብዙ ነበሩ። በቂ ውሃ አለመኖር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዲሁም የብድር እና የገበያ እጥረት ከነበሩት ብዙ መሰናክሎች ጥቂቶቹ ናቸው።
ከድርጅቱ ሦስት መስራች አባላት መካከል እስከ አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት ወ/ሮ አሰገደች ብቻ ናቸው፤ ድርጅቱ ሲመሰረት ከነበሩት መስራች አባላት መካከል ሁለቱ አባላት በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ታግሰው ወድ ውጤት ላይ ከመድረስ ይልቅ ትዕግስት በማጣት ለቅቀው ወጥተዋል።ወ/ሮ አስገደች ግን እነዚያን ፈተናዎች በማለፍ አሁን በአንጻሩ ስኬታማ የሚባለውን ጊዜ እያጣጣሙት ይገኛሉ።
ወ/ሮ አሰገደች ስለ ድርጅቱ ዕድገት ሲናገሩ፣ ከ2009 ዓ.ም ወዲህ የነበሩትን መሰናክሎች በትዕግስት በማለፍ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ እንደመጡ ያስረዳሉ። ለድርጅቱ ስኬት የእርሳቸው የሥራ እውቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እና የሥራው መላመድ ነገሮችን እያቀለላቸው እንደመጣ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የካይዘን ሥልጠና መውሰዳቸው ለሥራው ከፍተኛ አስተዋጻኦ ማበርከቱን አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት የልብስ ስፌት ሥራው በአስደሳች ደረጃ ላይ እንደሚኝ በመግለጽ፣ ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል ባሕላዊ አልባሳት፣ የህፃናት እና የአዋቂ አልባሳት፣ የወንዶች ቲሽርት፣ አልጋ ልብስ፣ የባሕል አልጋ ልብስ፣ መጋረጃ እና አጠቃላይ የልብስ ስራዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚ ያቀርባሉ።
ወ/ሮ አሰገደች ካላቸው ጥልቅ የሥራ ፍቅር እና ፍላጎት በመንሣት፣ በሥራው ላይ በመቆየት የስኬቱ ተካፋይ እና ደስተኛ ለመሆን ችለዋል። በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ሰባት ማሽኖች አሉት፣ እንዲሁም ስድስት ሠራተኞች ቀጥረው ሲያሠሩ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አምስት ሠራተኞቻቸው ሥራ አቁመዋል። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ እጅግ ተቀዛቅዟል ይላሉ – ወ/ሮ አስገደች። የተሻለ ገበያ እና ገቢ የሚያገኙት በኤግዚቢሽን እና በባዛር ላይ ነው። በእርግጥ ይህ ችግር አብዛኞቹ ኢንተርፕራይዞች እየተፈተኑበት የሚገኝ ችግር ነው። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ባዛር በመገደቡ ኢንተርፕራይዙ ምርቱን ለገበያ በብዛትና በዓይነት ማቅረብ አልቻለም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምርት በመቀነሱ በአሁኑ ጊዜ ራሳቸው ወ/ሮ አስገደች እና አንድ ሠራተኛ ብቻ በሥራ ላይ ይገኛሉ።
የወደፊት ዕቅድዎ ምን ይመስላል ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ወ/ሮ አሰገደች ቀዳሚ ዓላማቸው በራሳቸው የሚታወቁበት የልብስ ዲዛይን መሥራት እና ለተገልጋዮች ማቅረብ መሆኑን ይናገራሉ። ይህንኑ በማስፋፋት፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት እና ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለሀገራቸው ማምጣት ያስባሉ። በዚህ ሂደትም ራሳቸውንም አገራቸውንም የመጥቀም ሕልም አላቸው።
የራሳቸውንም ሆነ የሌሎች ድርጅቶችን እቅዶች ከማሳካት አንጻር ባዛር እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ፣ የባዛር ችግር የሚፈታበት መንገድ ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢ ትኩረት እና መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር፣ ቀጥታ አምራቹ ከአቅራቢው የሚገናኙበት መንገድ አለመመቻቸት፣ እንዲሁም ከሆቴሎች እና ከትልልቅ ድርጅቶች ጋር አብሮ የመሥራት እድል አናሳ መሆን እና የመሳሰሉት ችግሮች ቢወገዱ ሥራቸውን በብዛት እና በጥራት በማስፋፋት ራሳቸውንም፣ ወገንንም፣ አገርንም መጥቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በተለይ በማኑፋክቸሪንግ እና መሰል ዘርፎች መሰማራት ለሚያስቡ ኢንተርፕራይዞች ምን እንደሚመክሩ ሲጠየቁ፣ ወ/ሮ አስገደች በዋናነት የራስ ጥረት እና ጽናት ወሳኝ ናቸው ይላሉ። እንዲሁም ምንም ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ተስፋ ባለመቁረጥ መፍትሔ መፈለግ እና የሚወዱትን መሥራት ለስኬት መሰረታዊ ቁልፎች መሆናቸውን አስረግጠው ይናገራሉ።