መነሻ / ሥራ ፈጣሪዎችና ሥራ ፈጠራ / የቢዝነስ መመዘኛ ዘዴ

የቢዝነስ መመዘኛ ዘዴ

አንድ ቢዝነስ እንዲሰምር፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎንን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚህም በመነሣት፣ ከጠንካራ ጎኑ የሚመነጩ ዕድሎችን፣ እንዲሁም ከደካማ ጎኑ የሚነሡ ሥጋቶችንም በቅጡ መረዳት አለበት። እንዲህ ሲሆን፣ ድካሙን አካክሶ፣ ጠንካራ ጎኖቹን አዳብሮ የተሳካ ቢዝነስን ማስኬድ ይችላል።

ይህ ሃሳብ፣ የቢዝነስ ጠበብት በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል “SWOT” ብለው የሚጠሩት የቢዝነስ ሂደት መመዘኛ መስፈርት ሆኖ ያገለግላል። እርስዎም ቢዝነስዎን በዚህ መለኪያ ቢመዝኑ ለውጦችን በአግባቡ እያስተናገዱ ይበልጥ ውጤታማ በሚሆኑበት አቅጣጫ እንዲጓዙ ይረዳዎታል።

“SWOT” በእንግሊዝኛ የ4 ቃላት ውህድ ሲሆን እነሱም ፦

 1. ጥንካሬ (Strengths)
 2. ድክመት (Weaknesses)
 3. ዕድል (Opportunities) እና
 4. ስጋት (Threats) ናቸው።

ከእነዚህ ከአራቱ፣ ጥንካሬ እና ድክመት የቢዝነሳችን ውስጣዊ ሁኔታ የሚያመለክቱ ሲሆኑ፣ ዕድል እና ስጋት ደግሞ ውጫዊ (ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ያሉ) ሁኔታዎችን ያመለክታሉ።

በእያንዳንዱ ነጥብ ሥር ጥንካሬያችን፣ ድክመታችን፣ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ዕድሎች እንዲሁም ስጋቶች ምንድን ናቸው የሚለውን ለመመለስ ምን ምን ጥይቄዎችን መጠየቅ እንደሚገባን እንመልከት።

ውስጣዊ ሁኔታዎች

የአንድ ቢዝነስ ውስጣዊ ሁኔታዎች የሚባሉት፡-

 • የገንዘብ አቅም (መዋጮ፣ የገቢ ምንጭ፣ የኢንቨስትመንት አማራጭ)
 • ቁሳዊ ሀብት (መገኛ ቦታ፣ አቅርቦት፣ መሣሪያ)
 • የሰው ሀብት (ሠራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ደንበኞች)
 • የተፈጥሮ ሀብትን የማግኘት እድል
 • የባለቤትነት መብት፣ የቅጂ መብት እና የመሳሰሉት ናቸው።

ውስጣዊ ሁኔታዎች የጥንካሬ ወይም የድክመት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

1.      ጥንካሬ

ጠንካራ ጎኖቼ (እንደ ቢዝነስ) ምን ምን ናቸው? የእኔን ቢዝነስ የተለየ የሚያደርገው ጥሩ ነገር ምንድነው? ከሌሎች ተመሳሳይ ምርቶች ወይም አገልግሎቶች በምን በምን የተሻልኩ ነኝ? የእኔን ቢዝነስ ተመራጭ የሚያደርጉ ምን ልዩ ነገሮች አሉ?

ጥንካሬያችንን ስናውቅ፣ ያወቅነውን በመጠቀም ማዳበር እና የበለጡ የቢዝነስ ዕድሎችን ማግኘት እንችላለን። ጠንካራ ጎኖቻችን የምናሳድጋቸው ነገሮች ናቸው።

2.     ድክመት

ያሉብን ድክመቶች ምን ምን ናቸው? ቢዝነሳችን የበለጠ እንዳይቀላጠፍ እንቅፋት የሆኑብን ከራሳችን ጋር ወይም ከውሳኔያችን ጋር የተያያዙ ችግሮች ምንድን ናቸው?

ድክመታችንን ስናውቅ፣ ድክመታችንን በማስወገድ ወይም በማካካስ መፍትሔ መፈለግ እንችላለን። ደካማ ጎኖቻችን የምናሻሽላቸው/የምናካክሳቸው ነገሮች ናቸው።

ውጫዊ ሁኔታዎች

የአንድ ቢዝነስ ውጫዊ ሁኔታዎች የሚባሉት፡-

 • የገበያ ሁኔታ (የተፎካካሪዎች ይዞታ፣ አዳዲስ ምርቶች፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት)
 • የኢኮኖሚ ሁኔታ (አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የገንዘብ ሁኔታ)
 • ከአቅራቢዎች እና ከሸሪኮች ጋር ያለ ግንኙነት
 • ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕጎች እና የመሳሰሉት ናቸው።

ውጫዊ ሁኔታዎች የዕድል ወይም የስጋት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

3.    ዕድል

ጊዜ፣ ስፍራ፣ ልዩ ልዩ አካባቢያዊ ወይም ሌሎች ሁኔታዎች ለቢዝነሳችን ምን ምን ዓይነት ዕድሎችን ያቀርቡልናል?

ዕድሎች የምንጠቀማቸው ነገሮች ናቸው።

4.     ስጋት

ከዕድል በተጻራሪ፣ ጊዜ፣ ስፍራ፣ ልዩ ልዩ አካባቢያዊ ወይም ሌሎች ሁኔታዎች እንዲሁም ተፎካካሪ ቢዝነሶች የሚጋርጡብን የቢዝነስ ስጋቶች ምንድን ናቸው?

ስጋቶች የምንከላከላቸው ነገሮች ናቸው።

ይህንን የቢዝነስ ምዘና ዘዴ በሚገባ የተጠቀመ ሰው በሥራ ላይ ለሚያጋጥሙት አዳዲስ ችግሮች መፍትሔዎችን መፈለግ ይቀለዋል። ከዚህም በላይ የለውጥ አማራጮችን እና ገደቦችን እየቃኘ ይበልጥ ውጤታማ በሚያደርግበት አቅጣጫ መጓዝም ይችላል።

ይህንንም ይመልከቱ

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ምን አያደርጉም?

የራሳቸውን ቢዝነስ የሚመሩ ወይም በአንድ ቢዝነስ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ሰዎች፣ አካላዊ ጤና …