መነሻ / ሥራ ፈጣሪዎችና ሥራ ፈጠራ / “የቢዝነስ ሰሌዳ” መጠቀም

“የቢዝነስ ሰሌዳ” መጠቀም

የቢዝነስ ሰሌዳ (Business Canvas) አዲስ ሥራ ለመጀመር ለተነሣ የቢዝነስ ሰው/ ድርጅትም ሆነ ሥራ ላይ ለቆየ፣ ሥራን ውጤታማና ትርፋማ ለማድረግ ሁነኛ መሣሪያ ነው። የቢዝነስ ሰሌዳ፣ እንደ ቢዝነስ ማጤን ያለብንን ዋና ዋና ነገሮች እንዳንስት ይረዳል። ውጤታማና ትርፋማ ለመሆን፣ በሰሌዳው ላይ የተቀመጡትን ነጥቦች ልብ ማለት ይበጃል። ሰሌዳውን በወረቀት ላይ አትሞ፣ በእያንዳንዱ ነጥብ ሥር ምላሽን መሙላት ይመከራል።

 

የቢዝነስ ሰሌዳ

በመቀጠል፣ በሰሌዳው ውስጥ የተዘረዘሩትን 9 ነጥቦች ምንነት እናያለን። ነጥቦቹ የግድ በተራ መታየት/መሞላት ያለባቸው ናቸው ማለት አይደለም፤ ከቀለለን ጀምረን በተመቸን ቅደም ተከተል ልንሞላቸው እንችላለን።

  1. የምናቀርባቸው እሴቶች
    ይህ ክፍል እንደ ቢዝነስ ተለይተን የምንወጣበት አንድ ወሳኝ ማሳያ ነው። የምናቀርባቸው እሴቶች የምንሰጣቸው አገልግሎቶች/ምርቶች ድምር ውጤት ናቸው። እንዲሁም፣ እነዚህ ከሌሎች መሰል ቢዝነሶች በምን እንለያለን የሚለውን ጥያቄ የምንመልስባቸው ናቸው። በዚህ ሥር፣ ከሌሎች የእኛን ዓይነት ምርት ከሚያመርቱ ወይም አገልግሎት ከሚሰጡ ቢዝነሶች፣ ደንበኞች እኛን በተለይ ለምን ይምረጡን የሚለውንም የምናስረዳበት ነው። የሥራችንን ዓይነት እና ጥራት ለይተን ማስቀመጥ አለብን። ለማሳሌ ጫማ የምናመርት ቢሆን፣ ገበያውን ከሞሉት ጫማዎች ለምን የእኛ ጫማ መመረጥ አለበት፤ ወይም ምግብ የምንሸጥ ቢሆን ሰው በተለየ ለምን የእኛን መምረጥ አለበት የሚለውን የሚመልሱ ነጥቦች ማለት ናቸው።
  2. ቁልፍ ተግባሮች
    ሥራችን ውጤታማ እንዲሆንና እንደ ቢዝነስ እናቀርባለን የምንለውን አገልግሎት/ምርት ማቅረብ እንድንችል ምን ምን ተግባሮች ማከናወን ያስፈልገናል? የምንዘረዝራቸው ቁልፍ ተግባሮች እንደ ቢዝነስ የምንቀዳጀውን ስኬት የሚወስኑ እና ከገቢ ምንጮች ጋር የተቆራኙ (ገቢ ከማመንጨት ጋር ግልፅ ተያያዥነት ያላቸው) መሆን አለባቸው።

  3. ቁልፍ አጋሮች
    በምንሠራው ሥራ ውስጥ አጋሮች የሚሆኑን እነማን ናቸው? ጥሬ እቃ የምናገኘው ከማን/ከየት ነው? እንደ አጋር አብረናቸው ልንሠራ የምናስባቸው የቢዝነስ/የመንግስት/መንግስታዊ ያለሆኑ ድርጅቶች የትኞቹ ናቸው? የእነ ማንን አገልግሎት/ምክር/ድጋፍ እንፈልጋለን?

  4. ደንበኞችን መለየት
    አንድ ቢዝነስ፣ እንደው ዝም ብሎ አንድን ምርት ከማምረት ወይም አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ የምርቴ ወይም አገልግሎቴ ተጠቃሚ ማነው የሚለውን በዝርዝር መመለስ ይኖርበታል። ደንበኞች በሁለት ዋና መደቦች ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ:-
    • ጅምላ:- ምርታችን ወይም አገልግሎታችን ፆታ፣ ዕድሜ፣ የትምህርት/የዕውቀት ደረጃ፣ የገቢ መጠን ወዘተ ሳይለይ ሁሉንም ዒላማ ያደረገ ሲሆን
    • የተለየ የደንበኛ መደብ:- ምርታችን ወይም አገልግሎታችን ፆታ፣ ዕድሜ፣ የትምህርት/የዕውቀት ደረጃ፣ የገቢ መጠን ወዘተ መሠረት አድርጎ ያነጣጠረ የገበያ ደንበኛ ሲኖረው
      አንድ ቢዝነስ ያለው ደንበኛ ዓይነት እንደየሁኔታው ሁለቱም ዓይነት ደንበኛ፣ ወይም የሁለቱ ድብልቅ ሊኖረው ይችላል።

  5. የደንበኛ ግንኙነት
    “ደንበኛ ንጉሥ ነው/ ንግሥት ናት” እንደሚባለው፣ ለየትኛውም ቢዝነስ ስኬት የደንበኞች መስተንግዶ/ አያያዝ ወሳኝ ነው። ስለዚህም በማያሻማ መልኩ ደንበኞች እንዴት እንደሚያዙ/እንደሚስተናገዱ ማስቅመጥ ይኖርብናል።

    በዚህ ሥር ከደንበኞች ጋር እንዴት ዓይነት ግንኙነት እንደሚኖር፣ ስለምንሰጠው የድጋፍ ዓይነት፣ ቅሬታ እንዴት እንደምናስተናግድ፣ ከተስተናገዱ በኋላ እርካታቸውን በምን መልኩ እንደምንመዝን፣ እርካታቸው እየጨመረ እንዲሄድ ምን ማድረግ እንዳለብ እና የመሳሰሉትን በግልፅ መዘርዘር ይጠበቅብናል።

  6. አገልግሎት/ምርት ማድረሻ መንገዶች
    የአገልግሎት/ምርት ማድረሻ መንገዶች አንድ ቢዝነስ የሚያቀርባቸውን እሴቶች (በአግልግሎት፣ በምርት እና በአቀራረብ መልኩ) ለይቶ ወዳስቀመጣቸው የሚያደርስባቸው መንገዶች ወይም ዘዴዎች ናቸው። ሁለቱ ዋነኛ የአገልግሎት/ምርት ደንበኞች ጋር ማድረሻ መንገዶች በቀጥታ አቅርቦት እና በአከፋፋይ በኩል ናቸው።

    አንድ ቢዝነስ ከሁለቱ አንዱን ወይም ሁለቱንም እንደሁኔታው በጣምራ ሊጠቀም ይችላል። ሆኖም እነዚህን መንገዶች በምን መልኩ፣ ከማን ጋር፣ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚያውላቸው ግልፅ እይታ ሊይዝ ይገባል።

  7. ቁልፍ ግብዓት
    እነዚህ፣ አንድ ቢዝነስ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ለደንበኞቹ ለማድረስ የሚያስፈልጉት ዋና ዋና ግብዓት ናቸው። ቁልፍ ግብዓቱ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ፣ የንብረት፣ የዕውቀት እና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ።

  8. የገቢ ምንጮች
    እነዚህ አንድ ቢዝነስ ደንበኞቹ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን እንዲገዙ ለማድረግ የሚጠቀማቸው ዘዴዎች ናቸው።

    ቢዝነሱ ገቢ ከየት ከየት እንደሚያገኝ፣ በምን መልኩ እንደሚያገኝ፣ እንዴት እንደሚሰበስብ፣ እንዴት ደንበኞች ከፋይ እንዲሆኑ እንደሚይደርግ ዝርዝር ዘዴዎችን እና መንገዶችን ማስቀመጥ ይጠበቅበታል።

  9. የወጪ ሂደት
    በዚህ ሥር ቢዝነሱ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ የሚኖሩበት የወጪ መስመሮች ይሰፍራሉ። ቢዝነሶች በወጪ-ገቢ ስሌት እንዲሳካላቸው ለደንበኞቻቸው በሚያቀርቧቸው እሴቶች እና በሚያወጧቸው ወጪዎች ጥንቁቅነት ላይ መመርኮዝ አለባቸው።

    የምናስቀምጣቸው የወጪ ሂደት ዓይነቶች አራት ዓይነት ናቸው:-
    • ቋሚ ወጪዎች – እነዚህ በየጊዜው በቋሚነት የሚወጡ ናቸው። እንደ ደመወዝ፣ የቤት ኪራይ እና የመሳሰሉት ቋሚ ወጪዎች ናቸው።
    • ተለዋዋጭ ወጪዎች – እነዚህ እንደየምርት ወይም አገልግሎታችን መጠን የሚለዋወጡ ናቸው። ለምሳሌ ለጥሬ ዕቃ ግዢ የምናወጣው ወጪ እንደ ምርታችን ወይም አገልግሎታችን መጠን ከፍ ዝቅ ስለሚል ተለዋዋጭ ወጪ ሊባል ይችላል።
    • የዕድገት ወጪዎች – የምርት ወይም የአገልግሎታችን መጠን እያደገ በሄደ ቁጥር፣ ቋሚ ወጪዎች እንዳሉ ሆነው ተለዋዋጭ ወጪዎችን ብቻ በመጠኑ ከፍ በማድረግ በአነስተኛ ወጪ የምናድግባቸው መንገዶች ናቸው።
    • የስፋት ወጪዎች – ከጀመርነው ምርት ወይም አገልግሎት ጋር ተያያዥ የሆኑ ምርት ወይም አገልግሎት በመጨመር በአነስተኛ ወጪ ጭማሪ የሥራ መስካችንን የምናሰፋባቸው መንገዶች ናቸው።

ይህንንም ይመልከቱ

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ምን አያደርጉም?

የራሳቸውን ቢዝነስ የሚመሩ ወይም በአንድ ቢዝነስ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ሰዎች፣ አካላዊ ጤና …