ምስረታ ወይም ጀማሪ

ጥቃቅን/አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለምን አስፈለጉ?

ጥቃቅን/ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በተለገልጋዮች ፍላጎት መነሻነት፣ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለመሰማራት የሚፈልጉ ሥራ ፈላጊዎችን በተለያዩ አደረጃጀት አማራጮች መዝግቦ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደ መሣሪያ የታሰቡ ናቸው። አገልግሎቱ፣ ልዩ ልዩ ድጋፎች እንዳሉ ሆነው፣ በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ እና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ መሠረት የሚሰጥ ነው።

በጥቃቅን/ አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ለመሰማራት ምን ላድርግ?

በጥቃቅን/አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ለመመዝገብ፣ በቅድሚያ በወረዳው ጽሕፈት ቤት በሥራ ፈላጊነት መመዝገብ ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ ወደ ወረዳው ጽሕፈት ቤት በመሄድ በነዋሪነት መታወቂያ ላይ፣ ሥራ የሚለው ላይ “ሥራ ፈላጊ” ተብሎ መመዝገብ ይኖርበታል።

በመቀጠል፣ የሥራ አጥ መታወቂያ ጠይቆ ይወስዳል።

የሥራ አጥ መታወቂያ ሲወስድ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሥራ ፈላጊዎች መመዝገቢያ መዝገብ ላይ ይመዘገባል። የሚመዘገበው የሚከተለውን መረጃ በመስጠት ይሆናል፡-

  • ሙሉ ስም (ከነ አያት)
  • የመኖሪያ/ የቤተሰብ አድራሻ
  • ሊሠሩበት የመረጡት ከተማ (አድራሻ)
  • የትምህርት ደረጃ እና ዓይነት
  • ትምህርት የጨረሱበት/ ያቋረጡበት ዓመት
  • የተማሩበት ትምህርት ቤት
  • የሥራ ልምድ/ ዝንባሌ (ግለሰብም ይሁን የተደራጀ ተቋም)
  • በጥቃቅን/ አነስተኛ የሥራ ዘርፍ ሊሠሩት የመረጡት የሥራ ዓይነት (ሦስት ዘርፎች በቅደም ተከተል)
  • የተመረጠው ሥራ የሚፈልገው ክህሎት
  • ሥራውን ለመሥራት ያለ የክህሎት ክፍተት (ግለሰብም ይሁን የተደራጀ ተቋም)
  • የሚያስፈልገው የሥልጠና ዓይነትና የጊዜ መጠን
  • ኢንተርፕራይዝ ለመመስረት የሚፈልጉት የአደረጃጀት ዓይነት (የግል፣ ሽርክና፣ ኃ/የተ/የግ/ማ፣ ህ/ሥ/ማ)

የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች

ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር ተያይዞ ለሥራ ፈላጊዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በ “አንድ ማዕከል” አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች የሚሰጡ ናቸው። ይህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ በየወረዳው የሚገኝ ሲሆን፣ ተከታዮቹን አገልግሎቶች ሁሉ (ተለይቶ ካልተቀመጠ በስተቀር) የሚያገኘው ከዚያው ከአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ነው።

የሥራ አጥ መታወቂያ ከወሰደ በኋላ፣ ሥራ ፈላጊው ከሥራ ፈጠራ ጋር ተያይዞ ስለ ጥቃቅን/ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የምክርና የግንዛቤ አገልግሎት ያገኛል።

በዚህ ጊዜ፣ አዋጭ ተብለው የተመረጡ 5 የሥራ ዘርፎች ላይ መግለጫ ይደረግለታል። አምስቱ ዘርፎች፡-

  • ማኑፋክቸሪንግ
  • ኮንስትራክሽን
  • ንግድ
  • አገልግሎት እና
  • የከተማ ግብርና ናቸው።

ይህ ገለፃ ከተደረገለት በኋላ፣ ሥራ ፈላጊው በቅጥር ሥራ የማግኘት ወይም የመደራጀት አማራጭ ይሰጠዋል።

የቅጥር አማራጩን የወሰደ ሰው፣ የሥራ አጥ መታወቂያ ሲወስድ በሰጠው መረጃ መሠረት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ሌሎች ኢንተርፕራይዞች፣ ኢንዱስትሪ ዞኖች ወይም የመሳሰሉት ውስጥ እውቀትና ክህሎቱን ይስማማል የሚባል ሥራ ሲገኝ እንደሚጠራ ተነግሮት ከማዕከሉ ይሰናበታል።

በጥቃቅን/አነስተኛ ኢንተርፕራይዝነት ለመደራጀት የሚፈልግ ሰው፣ አራት የመደራጃ አማራጮች ይቀርቡለታል፡-

  1. የግል
  2. የኅብረት ሽርክና ማኅበር
  3. ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር

ከእነዚህ ከሦስቱ በአንዱ፣ በጥቃቅን/አነስተኛ ኢንተርፕራይዝነት ተደራጅቶ መሥራት የመረጠ ሰው፣ ተከታዮቹን ሦስት ነገሮች ማቅረብ ይጠበቅበታል፡-

  • የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ
  • የሥራ አጥ መታወቂያ
  • የሥልጠና ሰርትፍኬት (ካለ)

ምን ምን ዓይነት የኢንተርፕራይዝ የመደራጃ አማራጮች አሉ?

1. የግል ኢንተርፕራይዝ / ግለሰብ ነጋዴ

የግል ኢንተርፕራይዝ በአንድ ሰው የግል ሃብት የሚመሠረትና የሚተዳደር ሲሆን፣ የድርጅቱ ባለቤት በድርጅቱ እንቅስቃሴ ላይ ብቸኛ ውሳኔ ሰጭ የሆነበት ነው።

የግል ኢንተርፕራይዝ የማቋቋሚያ መስፈርት፡-

  1. የስራ አጥ መታወቂያ ካርድ፣
  2. የአመልካቹ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ጉርድ ፎቶ ግራፍ፣
  3. የነዋሪነት የመታወቂያ ካርድ ኮፒ፣
  4. ዕድሜው 18 ዓመት የሞላው መሆን፣
  5. ቋሚ አድራሻ ያለው መሆን፣
  6. የመነሻ ካፒታል ማስረጃ፣
  7. የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ሰርተፍኬት፣
  8. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ለሚያስፈልጋቸው የስራ መስኮች)

2. ኅብረት ሽርክና

የኅብረት ሽርክና ማህበር አደረጃጀት ሕጋዊ ሕልውና ያለው ከንግድ ማኅበራት ወይም ድርጅቶች ሁሉ ቀላል ቅርፅ ያለው አደረጃጀት ነው። በኅብረት ሽርክና አደረጃጀት የሸሪኮች አነስተኛ ቁጥር ሁለት ብቻ ሲሆን የአነስተኛ ካፒታል ጥያቄ ገደብ የለበትም። ካፒታሉ በውስጠ ደንቡ ውስጥ ቢካተትም ከምዝገባ በፊት መክፈሉ አስፈላጊ አይደለም። የሙያ ወይም የአገልግሎት መዋጮ የተፈቀደ ነው።

የኅብረት ሽርክና ማኅበር የማቋቋሚያ መስፈርት፡-

  1. የሥራ አጥ መታወቂያ ካርድ
  2. በሁሉም መስራች አባላት የተፈረመ ማመልከቻ ማቅረብ
  3. የአባላቱ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ኮፒ ማቅረብ
  4. የፀደቀ የንግድ ስም ስያሜ ማስረጃ
  5. የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ማስረጃ
  6. የአዋጭነት የንግድ ስራ እቅድ ማቅረብ
  7. የጸደቀ የመመስረቻ ጽሑፍ እና የመተዳደሪያ ደንብ
  8. የመስሪያ ቦታ ቋሚ አድራሻ
  9. ስራ ለመጀመር የሚያስችል መነሻ ካፒታል
  10. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ለሚያስፈልጋቸው የስራ መስኮች)

ይህን አደረጃጀት የመረጡ፣ በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ፣ ሞዴል የመተዳደርያ ደንብ እና የመመስረቻ ፅሁፍ ሰነድ ማግኘት ይችላሉ።

የመመስረቻ ጽሑፍ እና መተዳደሪያ ደንቡን በአቅራቢያቸው በሚገኝ የውልና ማስረጃ ቢሮ በመሄድ ማፀደቅ ይኖርባቸዋል። ለዚህም ቢሮው የሚጠይቀውን የአገልግሎት ክፍያ ራሳቸው መክፈል ይኖርባቸዋል።

3. ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር

ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር በንግድ ከ 2 – 50 በሆኑ አባላት (ከሁለት ባላነሰ፣ ከሃምሳ ባልበለጠ) የሚቋቋም ሆኖ፣ የማህበሩ መነሻ ካፒታል ከብር 15,000 ያላነሰ፣ የማህበሩ አክሲዮን እኩል በሆነ የአክሲዮን ዋጋ የተከፋፈለ ሆኖ የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከብር 10 ያላነሰ ሲሆን አባላቱም የተወሰነ ኃላፊነት ያለባቸው ድርጅት/ማህበር ነው።

የኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የማቋቋሚያ መስፈርት፡-

  1. የስራ አጥ መታወቂያ ካርድ
  2. የአመልካቾቹ የከተማ ነዋሪነት መታወቂያ ፎቶ ኮፒ ማቅረብ
  3. በሁሉም አባል የተፈረመ ማመልከቻ
  4. የፀደቀ የንግድ ስም ስያሜ ማስረጃ
  5. የጸደቀ የመመስረቻ ጽሑፍ እና የመተዳደሪያ ደንብ
  6. ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅቶ ማቅረብ
  7. 15 ሺ ብር በአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋም አስገብቶ ማስረጃ ማቅረብ
  8. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት
  9. የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ማውጣት
  10. የመስሪያ ቦታ ቋሚ አድራሻ

ይህን አደረጃጀት የመረጡ፣ በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ፣ ሞዴል የመተዳደርያ ደንብ እና የመመስረቻ ፅሁፍ ሰነድ ማግኘት ይችላሉ።

የመመስረቻ ጽሑፍ እና መተዳደሪያ ደንቡን በአቅራቢያቸው በሚገኝ የውልና ማስረጃ ቢሮ በመሄድ ማፀደቅ ይኖርባቸዋል። ለዚህም ቢሮው የሚጠይቀውን የአገልግሎት ክፍያ ራሳቸው መክፈል ይኖርባቸዋል።

የሕጋዊ ሰውነት ሰርትፍኬት አሰጣጥ

በግልም ሆነ በማህበር በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ሥራ ለሚገቡ ኢንተርፕራይዞች ለመደራጀት የሚያስፈልጉ ተብለው የተዘረዘሩትን መስፈርቶች አሟልተው የመመስረቻ ጽሁፍና መተዳደሪያ ደንባቸውን ካፀደቁ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ መሆናቸውን የሚገልጽ የሕጋዊነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ተዘጋጅቶ እንዲሰጣቸው ይደረጋል።

በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ሥራ የሚገቡ ስራ ፈላጊዎች አደረጃጀታቸውን እንደጨረሱ በጀማሪ ደረጃ ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል።

በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀታቸውን የሚገልጽ ሰርተፍኬት ከተሰጣቸው በኋላ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ እንዲያወጡ ይደረጋል። የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የማውጣቱ ሂደት፣ እዛው አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያው ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች የሚከናወን ይሆናል።

ሕጋዊ ሰውነት ያገኘ ጥቃቅን/አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የሚኖሩት ሰነዶች

  • የንግድ ምዝገባ ሰርተፍኬት
  • የንግድ ፈቃድ ሰርተፍኬት
  • የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN)
    ይህንን ለማገኘት፣ አመልካቹ ዕድሜው ከ18 ዓመትና በላይ መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ፣ የታደሰ የነዋሪነት መታወቂያ እና የንግድ አድራሻ ማስረጃ ማረጋገጥ ይኖርበታል
  • የጥቃቅን/ አነስተኛ ኢንተርፕራይዝነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት
    ይህ ኢንተርፕራይዞች መንግስታዊ ድጋፎችን ለማግኘት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝነት መደራጀታቸውን የሚያስረዳ ሰርትፍኬት ነው። አገልግሎቱም የሚሰጠው በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

industry

ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ዕድገት ደረጃ

ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ዕድገት ደረጃ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ ሀ) በኢንዲስትሪ …