መነሻ / ሥራ ፈጣሪዎችና ሥራ ፈጠራ / ግብ እንዴት ልቅረጽ?

ግብ እንዴት ልቅረጽ?

ለቢዝነሳችንም ሆነ ለግል ሕይወታችን የት እና እንዴት መድረስ እንደምንፈልግ ግልጽ የሆነ ግብ መያዝ ከመባከን ያድነናል። ይሁን እንጂ ሰዎችም ሆኑ ቢዝነሶች ብዙ ጊዜ ግባቸውን ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ይቸገራሉ፤ አንዳንዴ እንደውም ጭራሽ ምንም ግብ ሳይቀርጹ ይቀራሉ።

የትኛውም ዓይነት ግብ ሲቀረጽ፣ በሚከተለው መልኩ ቢሆን ለመቅረጽም፣ ለመከታተልም፣ እንዲሁም ለመተግበር ያመቻል። ይህ የግብ አቀራረጽ ዘዴ በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል “SMART” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ 5 መስፈርቶች አሉት።

 

የትኛውም የምናስቀምጠው ግብ የሚከተሉትን መስፈርቶች የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል።

1.      የማያሻማ (Specific)

የማያሻማ ግብ ማለት ግልጽ እና “ምን ማለት ይሆን?” የማያሰኝ መሆን አለበት።

ለምሳሌ፣ “በዚህ ዓመት ስኬታማ መሆን” የሚለው ፈጽሞ ለአንድ ቢዝነስ ግብ ሊሆን አይችልም። ስኬታማ ሲል ምን ማለት እንደሆነ፣ በዝርዝር እና ቁልጭ ባለ መንገድ መገለጽ መቻል አለበት።

2.     የሚለካ (Measurable)

የሚለካ ግብ ማለት ተሳክቷል አልተሳካም የሚለው በቀላሉ መመዘን የሚችል ማለት ነው።

ለምሳሌ፣ “ትርፋማ መሆን” የሚለው ግብ የሚለካ አይደለም። “የአንድ ሺህ ብር ትርፍ ማግኘት” የሚል ብናደርገው፣ ምን ያህል ተሳክቷል የሚለው በቀላሉ መመዘን ስለሚችል የሚለካ ግብ ሆነ ማለት ይቻላል።

3.     ሊደረስበት የሚችል (Achievable)

ግባችን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ለመሳካት የማይቻል መሆን የለበትም። ሊደረስበት የሚችል የሚለው የሚያመለክተው ካለንበት ወቅታዊ ይዞታ አንጻር የመሳካት ዕድል ያለው መሆኑን ነው።

ለምሳሌ፣ በወር የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ዝውውር ያለው ቢዝነስ፣ “በዓመቱ መጨረሻ የአንድ ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት” ቢል ካለበት ሁኔታ ጋር የማይጣጣም እና ሊደረስበት የማይችል ሆኖ ይገኛል። ይልቅ፣ ነገሮችን አገናዝቦ የበለጠ ሥራን በሚያበረታታ መልኩ ከፍ ያለ ግን ከእውነታው በጣም ያልራቀ ግብ ማስቀመጥ ይኖርበታል።

4.     ከእውነት ያልራቀ (Realistic)

ይህ “ሊደረስበት የሚችል” ከሚለው ጋር ተቀራራቢ የሆን መለኪያ ነው። “ሊደረስበት የሚችል” የሚለው የራስን አቅም ማገናዘብን የሚመለከት ሲሆን፣ “ከእውነት ያልራቀ” የሚለው ደግሞ የምንኖርበትን አገር እና አካባቢያዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባትን የተመለከተ ነው።

ለምሳሌ፣ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ፣ የቱንም ያህል የገንዘብ እና የሰው ኃይል አቅም ቢኖረን በኦንላይን የገንዘብ ዝውውር የመላው ዓለም ሰዎች የሚገበያዩበት የግብይት ቢዝነስ ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመር አይቻልም። እንዲህ ያለ ግብ አንድ ሰው ቢቀርጽ፣ ከእውነት የራቀ ሆኖ ይገኛል።

5.     በጊዜ የተገደበ (Time-bound)

የጊዜ ወሰን ያልተበጀለት ግብ፣ ግብ ሳይሆን ሕልም ነው። “የእኔ ቢዝነስ ወደፊት አንድ ቀን አንድ ሚሊየን ብር ትርፍ ይኖረዋል” ማለት ጥሩ ሃሳብ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግብ አይደለም። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል።

ለምሳሌ፣ “አንድ ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት” የሚለው ‘ሕልም’ “የሚቀጥለው ሰኔ መጨረሻ አንድ ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት” የሚለው ቢጨመርበት በጊዜ የተገደበ ግብ ይሆናል።

አምስቱን የትክክለና ግብ መገለጫዎች ስናስብ መርሳት የሌለብን ነገር፣ አንድ ግብ እውነትም ግብ እንዲባል ከአምስቱ አንዱን ወይም ሁለቱን ቢያሳካ በትክክል ግብ ሊባል አለመቻሉን ነው። ግባችን እውነትም ግብ እንዲባል አምስቱንም የትክክለኛ ግብ መለያዎች ማሟላት ይኖርበታል።

ይህንንም ይመልከቱ

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ምን አያደርጉም?

የራሳቸውን ቢዝነስ የሚመሩ ወይም በአንድ ቢዝነስ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ሰዎች፣ አካላዊ ጤና …