መነሻ / ሥራ ፈጣሪዎችና ሥራ ፈጠራ / የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ምን አያደርጉም?

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ምን አያደርጉም?

የራሳቸውን ቢዝነስ የሚመሩ ወይም በአንድ ቢዝነስ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ሰዎች፣ አካላዊ ጤና እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ የአእምሮ ጽናትም ያሻቸዋል። በተለይ አንድ ቢዝነስ በሁለት እግሩ እንዲቆም ለማደረግ ለሚጥሩ ኧንተርፕረነሮች፣ የአእምሮ ጽናት እጅግ አስፈላጊ ነው።

የአእምሮ ጽናት ሲባል ራሱ ጽናት፣ አይበገሬነት፣ በቀላሉ አለመረበሽ፣ ይሳካል ብሎ ማመን እንዲሁም በትናንሽ “ውድቀቶች” ተስፋ አለመቁረጥን ያካትታል።

የአእምሮ ጽናትን ለመረዳት ሌላው መንገድ፣ የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች የማያደርጓቸውን ነገሮች ለይቶ መመልከት ነው። ታዋቂው የቢዝነስ መጽሔት ፎርብስ የሚከተሉት 13 ነገሮች የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች የማያደርጓቸው ናቸው ሲል ይዘረዝራል።

 1. ለራሳቸው ከንፈር መምጠጥ

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች “ወይኔ ሳሳዝን” እያሉ በረባ ባልረባው ለራሳቸው ከንፈር ሲመጡ አይገኙም፤ “እንዲህ ተደረግኩ” እያሉ አይብሰለሰሉም። በዚህ ፈንታ ላሉበት ሁኔታ ራሳቸው ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ። የሚገጥማቸው ነገር ፍትሃዊ እንዳልሆነ ቢሰማቸው እንኳ፣ ከሚያልፉበት ነገር ትምህርት ወስደው ራሳቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይወስናሉ። አንድ ነገር እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር ቀጥለው ምን እንደሚያደርጉ ወደማሰብ ይሄዳሉ።

 1. ስለራሳቸው የሚሰማቸው ስሜት በሌሎች እንዲወሰን መፍቀድ

አንዳንዴ ሌሎች ሰዎች በንግግር ወይም በአካኋናቸው የበታችነት እንዲሰማን ወይም በአጠቃላይ ስለራሳችን ያለን ስሜት ቀና እንዳይሆን ሊያደርጉን ይችላሉ። የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ግን እንዲህ ላለ ነገር በጄ አይሉም። ስሜታቸውንም ሆነ ድርጊታቸውን ራሳቸው ይዘውሩታል እንጂ ሌሎች እንዲጠመዝዙት አይፈቅዱም። የብርታታቸው አንዱ ምንጭ ለሚገጥማቸው ነገር የሚሰጡትን ምላሽ በራሳቸው ለመምረጥ ያላቸው አቅም ነው።

 1. ለውጥን መሸሽ

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ለውጥ ሲመጣ “ግባ በሞቴ” የሚሉ ናቸው። የሚፈሩት ነገር ለውጥን ሳይሆን ባሉበት መርገጥን ነው። ለውጥ እና አንዳንዴም የማያስተማምን የሚመስል ሁኔታ እንዲህ ያሉ ሰዎችን የበለጠ ለመትጋት ያነሣሣቸዋል።

 1. ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆኑ ነገሮች ላይ ጊዜ ማጥፋት

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ስለመንገድ መጨናነቅ፣ ስለጠፋባቸው እቃ፣ ወይም ስለሌሎች ሰዎች እምብዛም ሲያማርሩ አይሰሙም። ለምን ቢባል፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ናቸው። አጉል ነገር ሲገጥማቸው ከማማረር ይልቅ መቆጣጠር የሚችሉት ነገር ላይ ያተኩራሉ፤ ያም ለዚያ ነገር እነርሱ የሚሰጡት ምላሽ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ፦ የስኬታማ ሥራ ፈጣሪ (ኧንተርፕረነር) መለያዎች

 1. ሌሎችን ለማስደሰት መጨነቅ

ሰው ለማስደሰት ሲሉ ራሳቸውን ውጥንቅጥ ውስጥ የሚከቱ ሰዎች ታውቁ ይሆን? አሊያም በተገላቢጦሽ ሌሎችን “ለማብሸቅ” ሲሉ አሳራቸውን የሚያዩስ? ሁለቱም በጎ አይደሉም። የአእምሮ ጽናት ያለው ሰው ለሁሉም መልካም እና ፍትሃዊ ለመሆን ይጥራል፤ ሆኖም ሌላን ሰው ለማስደሰትም ሆነ ለማስከፋት ሲል ያልሆነውን አያስመስልም፤ አቋሙን አይቀያይርም። ይህም ሆኖ፣ አቋሙን ለመፈተሽ ፈቃደኛ ነው፤ ምናልባት ሰዎችን ቢያስከፋም ከእነርሱ በኩል ጉዳዩ ምን እንደሚመስል ለማጤን ፈቃደኛ ነው።

 1. አደጋን (ሪስክን) መፍራት

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች የተጠና “ሪስክ” መውሰድን አይፈሩም። ይህ ማለት ሳያመዛዝኑ ያገኙት ነገር ውስጥ ሁሉ ዘው ይላሉ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ፣ አደጋ (“ሪስክ”) ያለውን ነገር ጥቅም እና ጉዳቱን መዝነው ለመጋፈጥ አይፈሩም።

 1. ያለፈ ነገር ላይ ችክ ማለት

ያለፈ ነገርን መቀበል፣ ከዚያ የሚገኝ ማበረታቻም ሆነ መሻሻል ያለበት ነገር ካለ መማር አስፈላጊ ነው። ዳሩ ግን ያለፈ ጊዜን እያሰቡ መብከንከንም ሆነ “ደጉን ዘመን” እያሰቡ በቀን ሕልም መዋኘት የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች የማያደርጉት ነገር ነው። አብዛኛውን አቅማቸውን የሚያውሉት የአሁኑን እና መጪውን ጊዜ የተሻለ ማደረግ ላይ ነው።

 1. ተመሳሳይ ስህተት ደጋግሞ መሥራት

“እብደት ማለት ተመሳሳይ ነገር ደጋግመው እያደረጉ የተለየ ውጤት መጠበቅ ነው” የሚል አባባል አለ። የአእምሮ ጽናት ያለው ሰው የተሳሳተውን ነገር ተቀብሎ እና አርሞ ለመጓዝ ፈቃደኛ ብቻ ሳይሆን ቀዳሚ ነው።

 1. በሌሎች ሰዎች ስኬት መቆጨት

በሌሎች ሰዎች ስኬት የእውነት መደሰት ጠንካራ ባህሪን ይጠይቃል። የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ይህንን ጠንካራ ባህሪ የተጎናጸፉ ናቸው። ሌሎች ሲሳካላቸው ቅናት ጠቅ አያደርጋቸውም። ያም ሆኖ “ይህ ሰው እንዴት ሆኖ ነው እዚህ ስኬት ላይ የደረሰው?” ብለው በመጠየቅ ለራሳቸው ትምህርት ይቀስማሉ። “አቋራጭ” ሳያሻቸው በራሳቸው ስኬትን ለማግኘት ይተጋሉ።

 1. ሳይሳካላቸው ሲቀር ተስፋ መቁረጥ

እያንዳንዷ ውድቀት የመሻሻል እድል አብራ ይዛ ትመጣለች። በዓለም ታሪክ ታላላቅ የሚባሉ የቢዝነስ ጀማሪዎች እንኳን፣ በተለይ መጀመሪያ አካባቢ አንድን ነገር አቃንተው ከሠሩበት ያበላሹበት ጊዜ እንደሚበዛ ለመናገር አያፍሩም። የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ወደሚፈልጉት ግብ የሚያቀርባቸው ይሁን እንጂ፣ አሥሬ እየወደቁ አሥሬ አቧራቸውን አራግፈው ለመነሣት ፈቃደኛ ናቸው።

 1. ብቻቸውን መሆን መፍራት

የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች ለብቻቸው ጊዜ ማሳለፍ አያሸብራቸውም፤ እንደውም ይናፍቁታል። የብቻ ጊዜያቸውን ለማሰላሰል፣ ለማቀድ እና ውጤታማነታቸው ላይ ለመሥራት ይጠቀሙታል። ከዚህም በላይ፣ ደስታቸው ሙሉ በሙሉ በሌሎች አብሮነት ላይ የተደገፈ አይደለም። ከሌሎች ጋር አብረው በመሆን ደስ እንደሚላቸው ሁሉ፣ ብቻቸውን ሆነውም ደስታን ማጣጣም ይችላሉ።

ይህንንም ይመልከቱ፦ ግብ እንዴት ልቅረጽ?

 1. የይገባኛል ስሜት

ከተማሩት ትምህርት ወይም ካለፉበት የተለያየ የዝግጅት ሂደት የተነሣ፣ እንዲህ ያለ ሥራ፣ ኑሮ፣ ሕይወት ወዘተ ሊኖረኝ ይገባል ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። እንዲህ ከማለት አልፈው፣ ያለምንም ተጨማሪ ጥረት እንዲህ ያሉ ነገሮች የኔ ሊሆኑ ይገባል የማለት አባዜ ግን አይጠቅምም። የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች እነዚህኑ ነገሮች (አንዳንዴ እንደውም በይበልጥ) ቢፍልጉም፣ ነገሮቹን ለማግኘት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።

 1. ፈጣን ውጤትን መፈለግ

ክብደት መቀነስ ይሁን፣ አዲስ ቢዝነስ መጀመር ይሁን ወይም ሌላ የሕይወት ጉዞ፣ የአእምሮ ጽናት ያላቸው ሰዎች በአንድ ጀንበር የስኬት ማማ ላይ የሚደረስበት እንዳልሆነ በሚገባ ያውቃሉ። ከቀን ቀን የመትጋት፣ ከቀን ቀን የማሻሻል ቁርጠኝነት አላቸው።

ይህንንም ይመልከቱ

የቢዝነስ መመዘኛ ዘዴ

አንድ ቢዝነስ እንዲሰምር፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎንን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚህም በመነሣት፣ ከጠንካራ ጎኑ የሚመነጩ …