አንድ ሰው የተሳካለት ሥራ ፈጣሪ ወይም ኧንተርፕረነር (አዲስና የተለየ የቢዝነስ ሃሳብ ወይም ዘዴ ይዞ የተነሣ) ለመሆን፣ የያዘው ሃሳብና ሃሳቡን ተግባራዊ ማድረጊያ ገንዘብ ወሳኝ መሆናቸው አይጠረጠርም። ሆኖም፣ እነዚህ ሁለቱ ብቻ ኧንተርፕረነሩ የተሳካለት የቢዝነስ ሰው እንዲሆን አያስችሉትም።
ኧንተርፕረነር፣ ስኬትን መቀዳጀት እንዲችል ወይም ጉዞው ወደ ስኬት የሚገሰግስ እንዲሆን፣ ዓይነተኛ የሆኑ የሰብዕና መገለጫዎች ያስፈልጉታል። እንደ ኧንተርፕረነር፣ እነዚህ የሰብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ካሉን ልናዳብራቸው፣ ከሌሉን ደግሞ እንደ አዲስ በውስጣችን ኮትኩተን ልናሳድጋቸው ይገባል።
በመቀጠል እነዚህ ለስኬታማ ኧንተርፕረነር የሚያስፈልጉ የሰብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ምን እንደሆኑ እናያለን።
- የራስ ተነሳሽነት
ወደ ስኬት ለመድረስ፣ አንድ ኧንተርፕረነር ቆስቋሽ ሳያስፈልገው የራሱ ተነሳሽነት ሊኖረው ያስፈልጋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የበለጠ ኃላፊነትን መሻትም እንዲኖረው ይጠበቃል። በዙሪያችን የሚያበረታቱን፣ ጎሽ የሚሉን ሰዎች ቢኖሩ መልካም ነው። ሆኖም፣ ከማንም በላይ ራሳችንን “ሞራል የምንሰጠው” እና የምናነሳሳው ራሳችን መሆን ይኖርብናል። - አደጋን የመጋፈጥ ፈቃደኝነት
አደጋን (“ሪስክ”) ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን የስኬታማ ኧንተርፕረነር ቁልፍ መለያ ነው። አዲስ ቢዝነስ ጀምሮ ስኬት ላይ ለመድረስ፣ ወይም ያለንን ቢዝነስ ለማሳደግ እየፈለግን በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ዓይነት አደጋ መሰል ነገር ማሰብ አንፈልግም ማለት አብሮ አይሄድም። በእርግጥ አደጋ መጋፈጥ ማለት በቅጡ ሳያስቡ በዘፈቀደ እርምጃ መውሰድ ፈፅሞ መሆን የለበትም። ይሁን እንጂ በሚገባ አሰላስሎ፣ አውጠንጥኖ፣ ግራ ቀኙን ተመልክቶ አዲስን ነገርን የመጀመርና የመሞከር “አደጋን” ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል። - በችሎታ የራስ መተማመንን ማዳበር
ልንሰማራ ባሰብንበት መስክ፣ አስተማማኝ የሆነ ችሎታ እንዳለን በራሳችን መተማመን ያስፈልገናል። በጠራ አእምሮ ስናስብ የሚታየን የችሎታ ክፍተት ካለብን፣ ራሳችንን ከማታለል ይልቅ ችሎታችንን ለማዳበር መነሣት ወይም ሌላ የሚስማማንን የሥራ መስክ መምረጥ ይኖርብናል። ነገር ግን፣ ችሎታው እንዳለን እያወቅን እየመላለሰ ብቅ የሚል የመተማመን ጉድለትን “አናት አናቱን” ብለን ማስወገድና በራስ መተማመንን መገንባት አለብን። - ከሌሎች ምላሽን (ግብረ መልስን) መፈለግ
ስኬታማ ኧንተርፕረነር ወይም የቢዝነስ ባለቤት ለመሆን፣ “ነገሮች ከሌላ አንፃር ሲታዩ ምን ይመስላሉ?” ብሎ መላልሶ መጠየቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት፣ አንድ መስክ ውስጥ ስንዘፈቅ “ከውጪ” በቀላሉ ሊታዩ የሚችሉ ዕድሎች ወይም ክፍተቶች ላይታዩን ስለሚችሉ ነው። ስለዚህ የሌሎችን አስተያየትና ግብረ መልስ መላልሶ መጠየቅ ወሳኝ ነው። ታዲያ የምናገኘውን ምላሽ በቀና አስተሳሰብ መመልከትና ስሜታዊ ሳይሆኑ አሠራርን ለማሻሻያ ግብዓት አድርጎ የመጠቀም ሰብዕናም አብሮ ያስፈልገናል። - ከፍተኛ የሚንቀለቀል መሻት/ ኃይል
ስኬታማ ኧንተርፕረነሮች ስለሚሠሩት ሥራ ውስጣቸው የሚንቀለቀል “እሳት” ያላቸው ናቸው። ስለምናመርተው ምርት ወይም ስለምንሰጠው አገልግሎት፣ ወይም ተያይዞ ስለምንፈጥረው ተፅዕኖ በቀላሉ የማይበርድ ውስጣዊ ትኩሳት ሊኖረን ያስፈልጋል። ይህ ስሜት ከሌለን፣ ሥራችን ሲሳካ የሚፈጥርብንን ስሜት በማሰብ ራሳችንን መቆስቆስ፣ ወይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊፈጥርብኝ የሚችለው እንዴት ያለ የሥራ መስክ ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። በቢዝነስ ጉዟችን ብዙ ውጣ ውረድ ሊገጥመን ስለሚችል፣ እንዲህ ያለ ውስጣዊ ኃይል እንደ ነዳጅ ውጣ ውረዱን እንድንወጣ ኃይል የሚሰጠን ይሆናል። - ስለወደፊቱ ማሰብ
ስኬታማ ኧንተርፕረነሮች ከዛሬው እንቅፋት፣ ውጣ ውረድ ወይም ጊዜያዊ ድል ይልቅ የወደፊቱ ጊዜና የሚደርሱበት ከፍታ የሚታያቸው ናቸው። ሁልጊዜም ከወራት፣ ከዓመታት በኋላ ሥራችን የት እንደሚደርስ በማሰብ መቃኘት ይኖርብናል። ራዕይና ዓላማችንን ስናስብና የወደፊት ግባችንን መላልሰን የምናስብ ስንሆን፣ ዛሬ የሚገጥሙንን እንቅፋቶችም ሆነ “ማታለያዎች” ለማለፍ አቅም ይኖረናል። - ነገሮችን የማቀናጀት ክህሎት
አዲስ ሥራ ስንጀምር፣ እየሠራንም ከሆነ ሥራችንን ለማስፋት ስናስብ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆኑልናል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። ያለን ገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የሥራ ቦታ፣ የገበያ ትስስር ወዘተ በምንፈልገው “ሃሳባዊ” ልክ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው። ስለዚህ ያሉንን ነገሮች ቅደም ተከተል በማስያዝና በሁነኛ መንገድ በማቀናጀት መሥራት መቻል አለብን። እንዲህ ማድረግ እንድንችል ደግሞ ነገሮችን የማቀናጀትና ውጤት የማምጣት ክህሎትን ማዳበር ያስፈልገናል። - ከገንዘብ ይልቅ እሴትን ዋጋ መስጠት
በእርግጥ አንድ ቢዝነስ ህልውናው ሊቀጥል የሚችለው አትራፊ ከሆነ፣ በሌላ አባባል ከወጪው ይልቅ ገቢው ከበለጠ ነው። የዚህ ዋናው መለኪያ ደግሞ የተስተካከለ የገንዘብ ፍሰት ነው። ይሁን እንጂ፣ አንድ ቢዝነስ ትርፋማ ለመሆንና ላለመክሰር መጠንቀቅ ያለበትን ያህል ዋና ግቡን እንደው ዝም ብሎ ገንዘብ ማጋበስ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ስለዚህም፣ “በፍጥነት” ከምንሰበስበው ገንዘብ ይልቅ፣ በምርታችን ወይም በአገልግሎታችን ለምንጨምረው እሴት ዋጋ መስጠት ይኖርብናል። ለጥራት፣ ለአገልግሎት እርካታና ለመሳሰሉት እሴቶች ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጥ ከሆነ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተዓማኒነታችን ከፍ እያለና ትርፋችን እየጨመረ መሄዱ አይቀሬ ነው።