መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ፊልጶስ፣ ኤደን እና ታረቀኝ ሽርክና ማኅበር
Eden

ፊልጶስ፣ ኤደን እና ታረቀኝ ሽርክና ማኅበር

ፊልጶስ፣ ኤደን እና ታረቀኝ ሽርክና ማኅበር የተመሠረተው በ2004 ዓ.ም በአቶ የማነ አብርሐም እና ሦስት መሥራች አባላት ሲሆን ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች አቸቶ (ኮምጣጤ) እና የለውዝ ቅቤ ናቸው። ድርጅቱ በቀን አንድ ሺህ ሊትር አቸቶ የማምረት አቅም አለው።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ ግማሽ ሊትር አቸቶ በማዘጋጀት አሥራ ሁለት (አንድ ደርዘን) በማድረግ ይህንንም ምርት በመቶ ሀምሳ ብር ለገበያ ያቀርባል። በፆሙ ምክንያት ለውዝ በጣም ስለተወደደ የለውዝ ቅቤ ምርት ለሁለት ወር ማምረት አቁሟል። ፆሙ ሲያልፍ ምርታቸውን ማምረት እንደሚቀጥሉ አቶ የማነ ጠቅሰዋል።

አቶ የማነ አብርሐም ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት ወደ ኬንያ አገር ሄደው ነበር። በዚህ ወቅት በአቸቶ እና ተያያዥ ሥራዎች ተቀጥረው ሠርተዋል፤ አስፈላጊውን ልምድ ከተማሩ በኋላ አገሬ ተመልሼ ይህን (የአቸቶ) ሥራ ብሞክረው ጥሩ ነው ብለው ወደ አገራቸው በመምጣት ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ድርጅቱን መሥርተዋል። ወደዚህ ሥራ ሲገቡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለውበታል። ምርቱን ማስተዋወቅ እና ገበያ ሰብሮ መግባት እንዲሁም ደንበኛ መያዝ አስቸጋሪ ነበር። ዱቤ እቃ ወስደው ያልመለሱ ብዙ ነጋዴዎች ነበሩ። እነዚህን ችግሮች አልፎ ድርጅቱ ስምንት ዓመታትን ሊያስቆጥር የቻለው በቤተሰቡ ጥንካሬ እንደሆነ አቶ የማነ ጠቅሰዋል። የድርጅቱ መሥራች አባላት ያለባቸውን ችግሮች በመመካከር ማን ምን ድክመት አለበት የሚለውን በመነጋገር እና እንዴት ይታረም ብሎ በመጠየቅ መፍትኂ የመሥጠት ሥራ ይሠራሉ። በተጨማሪም የሥስት እና የአራት ቀን ሥልጠናዎችን ከተለያዩ አካላት ወስደዋል። ይህም አስፈላጊ እና መሠረታዊ ክህሎቶችን እንዲቀስሙ አድርጓቸዋል።

ድርጅቱ በቀጥታ ትዕዛዝ ሲመጣ ምርቱን በማዘጋጀት የማቅረብ ሥራ ይሠራል። ይህም ለተጠቃሚም፣ ለአምራችም መሃል ላይ ያሉ ደላሎችን እንዳይኖሩ በማድረግ አምራችም ተጠቃሚዎችም እንዲጠቀሙ ያደርጋል። በዚህም አካሄድ ብዙ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል። ከዐሥራ አምስት የሚበልጡ ጅምላ የሚወስዱ ደንበኞች እንዲሁም መርካቶ ላሉ ነጋዴ እና ለሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች በራሱ ትራንስፖርት ምርቱን ያደርሳል። የድርጅቱ ምርቱ ጥሩ ስለሆነ የታወቀ ነው፤ በመቀጠልም የፕላስቲክ ማሸጊያው ላይ አድራሻው ስላለ በዛ መሠረት ፈላጊ ይደውላል በደወለው መሠረት ይስተናገዳል።

ድርጅቱ ለአራት ቋሚ ሠራተኞች እና ለዐሥራ ሁለት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። ይህ ድርጅት ሲመሠረት የነበረው ካፒታል ሠላሳ ሺህ ብር ሲሆን አሁን ወደ ካፒታሉ ሦስት መቶ ሺህ ብር ደርሷል። እንዲሁም ከሃያ በላይ ደንበኞችን አፍርቷል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ከባድ ነበር፤ ሥራ በጣም ቀንሶ ስለነበር የቤት ኪራይ ያለ ሥራ ነበር ድርጅቱ ሲከፍል የነበረው። በኮቪድ ወቅት ወሳኝ ለሚባሉ ደንበኞች በፊት ዐሥር ደርዘን የሚገዙ ከሆነ ሦስት ደርዘን በመስጠት፣ አምስት ደርዘን የሚገዙ ከሆነ ደግሞ አንድ ደርዘን በመስጠት እንዲሁም የድርጅቱ መሥራች ቤተሰቦች ብቻቸውን ምርቱን በማምረት ለደንበኞቻችው በዙር እንዲደርሳቸው በማድረግ ነው የኮቪድን ጊዜን ያለፉት።

ምክር እና እቅድ

አቶ የማነ ስለ ሥራ የሚከተለውን ብለዋል። “ቢዝነስ ላይ ትርፍ ድንበኛ ነው፤ ስለዚህ ደንበኛን ማክበር፣ ስቆ እና ተሳስቆ ቀልዶ ማለፍ ጥሩ ነው። ለድርጅቱ እድገት የደንበኞች አክብሮት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። ስለዚህ ማንም ሰው ሥራ ሲሠራ ደንበኞችን ማክበር እና መንከባከብ አስፈላጊ ነው።”

አዲስ ወደ ማንኛውም አይነት ሥራ የሚገቡ ሰዎች ሥራውን ለመሥራት ውስጣቸውን ማሳመን አለባቸው። የውስጥ ተነሳሽነት ካለ ሥራ በጣም ይቀላል፣ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ያስችላል ብለው መልዕክታቸውን አስተላፈዋል።

ድርጅቱ ለወደፊት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁለት የመሥሪያ ቦታዎች በማዘጋጀት ያለውን የምርት ፍላጎት ለማሟሟላት አቅዶ እየሠራ ነው። እንዲሁም ሰፋ ያለ ቦታ በማዘጋጀት የጨው ምርት ለመጀመር ጥናቱን ጨርሶ መጋዘን በማፈላለግ ላይ ይገኛል። አቶ የማነም ወደ ፊት ከፍታ ላይ ምርት እና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ አቅደዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …