ገነት ገብሩ የባህል አልባሳት የተመሠረተው በወ/ሮ ገነት ገብሩ በ2010 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የባሕል አልባሳትን በማምረት ለገበያ ያቀርባል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ወ/ሮ ገነት ገብሩ ይህን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ዘመናዊ አልባሳትን ይሸጡ ነበር። ከዚያም ከሰዎች ጋር በሚነጋገሩበት ወቅት የአልጋ ልብስ መሥራት ጥሩ እንደሆነ እና ቤታቸው ሊሠሩት እንደሚችሉ ተረዱ። ሙያውም ስለነበራቸው የአልጋ ልብስ እና የሶፋ ጨርቅ እንዲሁም የሶፋ ትራሶች እና የቴሌቪዥን ጠረጴዛ ማስዋቢያዎችን በመሥራት ቆዩ። ተመሳሳይ ምርቶች ከቻይና መምጣት ሲጀምሩ ምርቶቹ ጥራት ባይኖራቸውም በርካሽ ዋጋ ይሸጡ ስለነበር አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ወደ ልብስ ሽያጭ ተመልሰዋል።
ወደ ልብስ ሽያጭ ላይ ሲመለሱ ደግሞ ባዛር ላይ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲነጋገሩ የባሕል አልባሳት ሥራ ላይ መግባት ወቅት ቢኖረውም የተሻለ እንደሆነ ሰሙ። የልብስ ሽያጩን ሥራ እየሠሩ ማታ ማታ ደግሞ የዘመናዊ እና ባሕላዊ ልብስ ስፌት ተማሩ። ትምህርታቸው እንደጨረሱ የዚያን ጊዜ የብቃት ማረጋገጫ (COC) ፈተና ባይሰጥም እሳቸው የባሕል ልብሱ ላይ አተኩረው ይሠሩ ነበር። ቀስ በቀስ የብቃት ማረጋገጫ (COC) ፈተና በመጀመሩ ዌብዴብ በሚባል ድርጅት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ የብቃት ማረጋገጫ (COC) ሰርተፍኬት ማግኘት ችለዋል። የብቃት ማረጋገጫ (COC) ሰርተፍኬት እንደያዙ ብር 20,000 (በሃያ ሺህ ብር) መነሻ ካፒታል የባሕል አልባሳት የሚያመርት ድርጅትን መሠረቱ። ድርጅቱ አጠቃላይ የባሕል አልባሳት፣ የህጻናት፣ የአዋቂዎችን የወንድ እና የሴት አልባሳት በጥራት በመሥራት ላይ ይገኛል። አሁን ላይ አቅሙን በማሳደግ ለሦስት ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። የካፒታል አቅሙንም ወደ ብር 300,000 (ሦስት መቶ ሺህ ብር) ማሳደግ ችሏል።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ እንደ ጨርቁ ደረጃ ቢወሰንም አማካይ ዋጋዎች ከዚህ በታች ተጠቅሰዋል፦
- የህጻናት አልባሳት፦ ከብር 300 (ሦስት መቶ ብር) እስከ ብር 400 (አራት መቶ ብር)
- የአዋቂዎች ሀበሻ ቀሚስ እንደ ዓይነቱ ይለያያል፦ ከብር 1200 (አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር) እስከ ብር 2600 (ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ብር)
- የአዋቂ ወንዶች ልብስ ከብር 400 (አራት መቶ ብር) እስከ ብር 800 (ስምንት መቶ ብር) ለገበያ ያቀርባል
ድርጅቱ በዋናነት ሥራዎችን የሚያገኘው ንፋስ ስልክ አካባቢ ኖክ መብራት ኀይል የሚገኘው የመንግሥት ሱቅ ድረስ በሚመጡ ደንበኞች እና ወደ ባዛር እና ኤግዚቢሽን ለሚመጡ ደንበኞች በዕለቱ በመሸጥ ነው። ለነኝህም ደንበኞች ቢዝነስ ካርድም በመስጠት ሽያጭ ብቻ ሳይሆን ምርቱንም በማስተዋወቅ ጭምር ሥራው እያሳደገ ይገኛል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ሥራው ከባድ ሁኔታ ላይ ነበር፤ ከወረርሽኙ በኋላ ሥራው ቀስ በቀስ እድገት እያሳየ መነሳሳት የጀመረ ሲሆን በተለይም ኤግዚብሽን እና ባዛር በመከፈቱ በጣም ለውጥ ማምጣት እንዲችል እንዳደረገው ገልጸዋል።
ምክር እና ዕቅድ
ለአንድ ንግድ መስፋፋት የሀገር ሠላም በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህም ጋር ሥራቸውን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያም ጭምር ለማስፋፋት እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።