jendi-leather-logo

ጀንዲ ሌዘር

ድርጅቱ የተመሠረተው በወይዘሪት ናዲያ ይመር በ2012 ዓ.ም. ነው። ጀንዲ ሌዘር ጥራት ያላቸውን የቆዳ ውጤቶች በማምረት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ራሱን እና ማኅበረ ሰቡን እየጠቀመ ይገኛል። ወደ ፊት ደግሞ ለተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም የሚያመርታቸውን ምርቶች ወደ ውጭ ሃገር በመላክ ለሃገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የበኩሉን አስተዋፅዖ የማበርከት እቅድ አለው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የሴቶች እና የወንዶች የቆዳ ቦርሳዎች
  • የቆዳ ጫማዎች
  • ቀበቶ እና ክፍት የሆኑ የወንድ እና የሴት ጫማዎች

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ እንደ ጊዜው እና ቦርሳው መጠን ቢለያይም የድርጅቱ አሁን ላይ ያሉ ዋጋዎች

  • የወንዶች የኪስ ቦርሳ፦ ከሁለት መቶ ሃምሳ ብር እስከ አምስት መቶ ብር
  • የሴቶች ቦርሳ ዋጋ፦ በአማካይ አንድ ሺህ ብር

ምሥረታ፣ ማስተዋወቅ፣ ማስፋፋት እና የኮቪድ ተፅዕኖ

የድርጅቱ መሥራች ጀንዲ ሌዘርን ከመመሥረታቸው በፊት ሙያው ደስ ይላቸው ነበር፤ ይሁንና በደንብ አልሠሩበትም። የአካውንቲንግ ትምህርት እየተማሩም ስለነበረ ዋና ሀሳባቸው እዚያ ላይ ነበር። ትምህርታቸውን ጨርሰው በአካውንቲግ ሥራ እንደጀመሩ ግን ቦርሳ የመሥራት ፍላጎታቸው በጣም እየጨመረ መጣ። በዚህ ጊዜም ኢንተርኔት በመጠቀም የተለያዩ ትምህርቶችን ከተማሩ በኋላ በቀጥታ ደግሞ የቆዳ ትምህርት ቤት በመግባት ሙያውን ተማሩ። ተምረው እንደጨረሱም ሥራው እንዴት እንደሚሠራ ልምድ እየቀሰሙ ለአንድ ዓመት ሠርተዋል።

ወ/ት ናዲያ ለአንድ ዓመት ሠርተው አስፈላጊውን ልምድ እንዳካበቱ ጀንዲ ሌዘር ድርጅትን ሁለት ማሽን ይዘው መሠረቱ። ድርጅቱ በተመሠረተ ወቅት ጊዜው ኮቪድ የተከሰተበት ወቅት ስለነበር ሥራ፣ ሠራተኛ፣ ጥሬ ዕቃ፣ የሥራ ቦታ አለመገኘት እና የመሠረተ ልማት (እንደ ውሃ እና መብራ)ት አለሟሟላት የነበሩ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም የድርጅቱ መሥራች በነበራቸው ትዕግስት እና ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ በመፈለግ ቀስ በቀስ ሥራቸው መልክ እየያዘ መጥቷል። ለምሳሌ የነበረውን የቆዳ ሥራ ችግር ማስክ በመሥራት እንዲሁም በኮቪድ ጊዜ ድርጅት መሥርቶ ሥራ መፈለግ ከባድ ቢሆንም ያለ መታከት ሥራ በመፈለግ ሥራዎችን ሊያገኙ ችለዋል። በነበረውም ችግር ድርጅቱ ከመስከረም 2013 ዓ.ም. በኋላ ነው ሥራ የጀመረው፤ ለስድስት ወር ሥራ አልነበረም። በዚህ ጊዜ ማስክ ነው ሲሠሩ የነበረው፤ እንዲሁም አሁን ያለው ያለመረጋጋት ነገርም አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተውታል። ይህም ድርጅቱ ሱቅ መክፈት፣ ኤክስፖርት ማድረግ ደረጃ መድረስ እንዳይችል እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው ባዛር እና ኢተርኔት በመጠቀም ሲሆን ይህም በሶሻልሚዲያ፣ ኢንስታግራም፤ ፌስቡክ ማርኬት ፕሌስ በመጠቀም እንዲሁም የሽያጭ እና መገበያያ ዌብሳይት ቀፊራን በመጠቀም ነው። አሁን ደግሞ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመጠቀም  ጨረታዎች ላይ ለመሳተፍ እቅድ አላቸው። እንዲሁም በቅርብ ደግሞ ቴሌግራም ቻናል በመክፈት ምርታቸውን ማስተዋወቅ ለመጀመር አቅደዋል።

ጀንዲ ሌዘር አሁን ያሉትን የማሽኖች ቁጥር ወደ ስድስት ያሳደገ ሲሆን በዚህም በቀን አራት ደርዘን ጫማዎችን እንዲሁም አንድ መቶ ቦርሳዎችን በሰባት ቀን የማድረስ አቅም አለው። ይህንን በውስጡ በቀጠራቸው ሦስት ብቁ ባለሙያዎች ያከናውናል። ተጨማሪ ሥራ ከመጣ ለሌሎች ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፈጠር ሥራዎችን ይሠራል።

ምክር

አዲስ ለሚገቡ ሰዎች ይሄንን ምክር ሰጥተዋል “አሁን ሥራ መጀመር በኮቪድ ጊዜ ከሚጀምሩ የተሻለ ነው። ግን በዋናነት ገበያ ማፈላለግ ከምርት ሥራ ይቀድማል፤ ማርኬት ካለ ሥራ መሥራት ይቻላል። ስለዚህ ሥራውን ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው። ሌላው ቆዳው እኛ አገር ስላለ አያስቸግርም፤ ግን  አንዳንድ አክሠሠሪ አይኖርም ለዚህ ደግሞ አማራጭ መንገዶችን መጠቀም ይገባል። የቆዳ ሥራ እንደ ምግብ አይደለም፤ ምግብ ሁሌም የሚወሰድ አስፈላጊ ነገር ነው። ቆዳ ግን አይደለም በዓል ሲመጣ ብዙ ሥራ አለ። ከበዓል በኋላ (በአዘቦት) ቀን ምንም ሥራ ላይኖር ይችላል። እንዲሁም ለሥራው ፍላጎት ከሌለ በደንብ አይሠራም፤ ፍላጎት ሊኖር ይገባል።”

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …