መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / መጣለም ጌጤ ጠቅላላ የእንጨት፣ ብረታብረት እና አልሙኒየም ሥራዎች
metalem-getie-logo

መጣለም ጌጤ ጠቅላላ የእንጨት፣ ብረታብረት እና አልሙኒየም ሥራዎች

መጣለም ጌጤ ጠቅላላ የእንጨት፣ ብረታብረት እና አልሙኒየም ሥራዎች የግል ኢንተርፕራይዝ በመጣለም ጌጤ በ2006 ዓ.ም. ተመሰረተ።

ምሥረታ እና ማስፋፋት

አቶ መጣለም ከልጅነት ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው ሲሠሩት የነበረውን የእንጨትና የብረታብረት ሙያ እያዩ ስለነበር ያደጉት የሙያው ፍቅር አድሮባቸው ነበር። ከልጅነት ጊዜ አንስቶ ሲያመላልሱት እና መሥራት ሲፈልጉት የነበረውን የእንጨትና ብረታብረት ሙያ ዘጠነኛ ክፍል ሲደርሱ ሥራውን ለመጀመር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሙያው ለመስጠት በመወሰን በባህርዳር አካባቢ በአንድ ድርጅት ውስጥ በቀን 5 ብር እየተከፈላቸው መሥራት ጀመሩ።  ይሁን እና የአቶ የመጣለም ህልም እና ሙያውን በደንብ ማወቅ ስለሚፈልጉ የተሻለ ሙያ ልምድ የሚቀስምበት እና የተሻለ ክፍያ የሚያገኙበት ከዚያም አልፎ የራሳቸውን ትልቅ ድርጅት በማቋቋም ለውጥ የሚፈጥሩበትን አጋጣሚ በማሰብ በ1996 ዓ.ም. አዲስ አበባ በመምጣት ቤቴል አካባቢ በሚገኝ የእንጨትና ብረታ ብረት ድርጅት ውስጥ በቀን 10 ብር እየተከፈላቸው በረዳትነት ለአንድ ዓመት ከሠሩ በኋላ በ1997 ዓ.ም. በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በተደራጀ ድርጅት ውስጥ ለ10 ዓመታት ያህል በመሥራት ብዙ ልምድን መቅሰም ችለዋል።

አስፈላጊውን ልምድ ከቀሰሙ በኋላ አቶ መጣለም በ2006 ዓ.ም. ያጠራቀሙትን ገንዘብ ከተወሰኑ የብድር አጋጣሚዎች ጋር በማመቻቸት በ 6,000 ብር (ስድስት ሺህ ብር) መነሻ ካፒታልና በአንድ ባለሙያ በመቅጠር “መጣለም ጌጤ የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረት የግል ኢንተርፕራይዝ”  አቋቁመዋል። በወቅቱ ምንም እንኳን ድርጅቱ ደረጃቸውን ባልጠበቁና ኋላቀር በሆኑ መሣርያዎች ቢጀምርም በነበረው የተቀናጀ አመራርና እና የቡድን ሥራ ከ2007 እስከ 2010 ዓ.ም. በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በብየዳ፣ የእንጨት ሥራ፣ የአልሙኒየም ሥራዎች፣ መስታወት ገጠማ፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ሥራዎች ሠርቷል። የሰው ኃይሉንም ከ1 ወደ 8 በማሳደግ 6,000 ብር (ስድስት ሺህ ብር) የነበረውን መነሻ ካፒታል ወደ 2,000,000 ብር (ሁለት ሚሊየን ብር) በማሳደግ እንዲሁም አብረው ይሠሩ የነበሩ ወጣቶችን በማሠልጠን እና በማብቃት የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው እንዲያስተዳድሩ ተከታታይ ድጋፍና እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛል። ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪ  ለሥራው አጋዥ የሆኑ እንደ ጄኔሬተር፣ መበየጃ ማሽን፣ መቁረጫ ማሽን፣ ቀለም መቀቢያ ማሽን፣ ወዘተ ማሟላት ችሏል። አቶ መጣለ የከፍታን አገልግሎት በቴሌግራም ቻናል ሲከታተሉ ቆይተው በቅርቡ ለኢንተርፕራይዞች የተዘጋጀውን የቅናሽ ፓኬጅ በመጠቀም ይበልጥ ሥራቸውን እያሰፉ ይገኛሉ።

ድርጅቱ ካጠናቀቃቸው ሥራዎች ውስጥ ለምሳሌ የሚጠቀሰው የ 4,000,000 ብር (አራት ሚሊዮን ብር) ሥራ ጨረታ በማሸነፍ ያገኘው የሳሪስ የገበያ ማዕከል የሻተር እና ሃንድል ሥራዎች ሲሆን፣ ሥራውንም በሚገባ አጠናቋል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ በከፊሉ

  • ቁም ሳጥን ኦስትሪያ እሽግ – 8,000 ብር በካሬ
  • ኤምዲፍ ቁምሳጥን – ከ6,500 ብር እስከ 7,000 ብር በካሬ
  • 91 ሳንቲም ስፋት ያላቸው በሮች – ከ11,000 ብር ከኦስትሪያ እንጨት
  • የብረት ኢሚቴሽን ሥራ – በካሬ 4,000 ብር
  • የግቢ ትልልቅ በሮች – ከ60,000 ብር ጀምሮ

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ድርጅቱ ላይ በጣም ከባድ ተፅዕኖ ነበረው፤ ምክንያቱም ጥሬ እቃ፣ ፈርኒቸር እና ብረት ከውጭ የሚመጡ እቃዎች ስለነበሩ የዋጋ መጨመር እና ብሎም የማቴሪያልም አለመኖር ተከስቶ ስለነበር ነው። በዚህም ጊዜ ሠራተኞች ሳይቀንስ ያለውን ሂሳብ በማስላት እና ከወጪ ቀሪ በመመደብ በኪሣራ የተገኘውን ሥራ በመሥራት የኮሮናን ጊዜ ተሻግሯል።

እቅድ

ድርጅቱ ወደ ፊት ዘመኑን የጠበቁና በቴክኖሎጂ የታገዙ ማሽኖችን በማስመጣት፣  እንዲሁም አሁን ያለበትን የመሥርያ ቦታና የገበያ ትስስር ችግሮች በመፍታት፣ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል በውስጡ በማቀፍ ዘመናዊና ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለገበያ የማቅረብ እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …