ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ማርቆስ አሠፋ እና በአራት መሥራች አባላት በ2012 ዓ.ም ነው። ደርጅቱ የኮንስትራክሽን፣ የዲዛይን ሥራዎችን እና ተያያዥ የማማከር አገልግሎቶች ይሠጣል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
አቶ ማርቆስ ከጓደኞቻቸው ጋር የዲዛይን እና የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን ያጣመረ ጥሩ ቡድን ፈጥረው፤ በኮንስትራክሽን እና የዲዛይን ሥራ በሚፈለገው የጥራት ደረጃና ልዕቀት የማጠናቀቅ አቅም ያለው ድርጅት ለመመሥረት በማሠብ ነው ድርጅቱን የመሠረቱት።
አቶ ማርቆስ ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፍ የገቡበት መሠረታዊ ምክንያት በጊዜው ገበያው ላይ በጣም ጥሩ የሥራ ዕድል ስለነበር ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው በሁለት ቡድን በመከፈልና የሥራ ክፍፍል በማድረግ ሁለቱ አባላት የኮንስትራክሽን ሥራዎችን ሁለቱ ደግሞ የዲዛይን ሥራዎችን በመሥራት ነው። ይህም አሠራር ሁለቱን (ኮንስትራክሽን እና ዲዛይን) ሥራዎች በተለያዩ የጋራ ዓላማ በሌላቸው/በማይሰማቸው ሠራተኞች ሲከናወኑ የሚፈጠረውን የሥራ አለመግባባት እና መጣረስ በማስቀረት አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደቻሉ አቶ ማርቆስ ተናግረዋል።
ድርጅቱ በብዛት የሚሠራቸው ሥራዎች የመኖሪያ (Residential) ሕንጻ ዲዛይኖችን ሲሆን በተጨማሪም የሚክስድ ፕሮጀክት ሥራዎችን (ለምሳሌ የጋርመንት ፋብሪካ፣ የፋርማሲዩቲካል ፋብሪካ መጋዘን ዲዛይኖችን) ይሠራል። ድርጅቱ በውስጡ ፕሮፌሽናል አርክቴክት፣ ሲቪል መሃንዲስ እንዲሁም በስትራክቸራል ዲዛይን የመጨረሻ ደረጃ ፕሮፌሽናል ፕራክቲሲንግ ፈቃደ የተሰጠውን ባለሙያ ስላካተተ ምንም ዓይነት ሥራ ቢመጣ በጥራት ተልዕኮውን የመወጣት አቅም አለው። ድርጅቱ በዲዛየን ሥራ ከሃምሳ በላይ ሥራዎችን አጠናቋል። በተጨማሪም ችግሮች ሲፈጠሩ የሚያማክሯቸው ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ያሉ ሲሆን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሲመጡ ከተሻሉ ድርጅቶች (ደረጃ ሦስት እና በላይ ያሉ) ጋር በመካከር ሥራዎችን ያከናውናል።
ድርጅቱ ሲመሠረት በአራት መሥራች አባላት እና በአምስት መቶ ብር ካፒታል የነበረ ሲሆን አሁናዊ ሁኔታ ለአራት ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም የካፒታሉን አቅም ወደ ሀምሳ ሺህ ብር አሳድጓል።
አቶ ማርቆስ ተመርቀው ቀጥታ ወደ ድርጅቱ ሥራ ነበር የገቡት፤ ነገር ግን በአፕረንቲስሺፕ ላይ ብዙ ልምድ እና ተሞክሮዎችን መቅሰም ችለው ስለነበር ድርጅቱ ውስጥ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ ጠቅሰዋል። የሥራ ባልደረቦቻቸው ተቀጥረው የመሥራት እድሉ ነበራቸው፤ እነሱም ከተሞክሯቸው ሳይት ላይ መሥራት የተሻለ ዕቅም ለመገንባት እንደሚያስችል አክለዋል። ድርጅቱ ልምድ በብዛት ከሥራ በመማር ነው ያካበተው። ትምርት እና ሥራ ይለያያል፤ ለምሳሌ የፋርማሲዩቲካል ፋብሪካ መጋዘን ሥራ ላይ የዲዛይን ቡድን፣ የፋርማሲስት ቡድን፣ የኬሚስት ቡድን፣ አርክቴክት እና መሐንዲስ እና ሌሎችም ብዙ ባለሙያዎችን ያካትታል። እነዚህ ሁሉ እየተማሩ ስለሚያስተምሩ ብዙ ጠቃሚ ልምድ መውሰድ ያስችላል ሲሉ ተሞክሯቸውን አቶ ማርቆስ አካፍለዋል።
ድርጅቱን ሥራዎቹን የሚያስተዋውቀው ሶሻል ሚዲያ በመጠቀም እና በሰው በሰው ሲሆን እንደ ተጨማሪ ቢዝነስ ካርድ እና ብሮሸር ይጠቀማል ግን ሁለቱ (ቢዝነስ ካርድ እና ብሮሸሮች) የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ አይደሉም ። ድርጅቱ በጥሩ ዲዛይን የተሠሩ ሥራዎችን በፌስቡክ ገፅ ላይ በመለጠፍ ጥሩ ውጤት አምጥቷል። ባነርም በሩ ላይ ይገኛል ባነሩንም አንዳንድ ደንበኛ እግረ መንገዱን አይቶ ይመጣል። በተጨማሪም በከፍታ ፕሮጀከት በ2merkato.com ላይ ለኢንተርፕራይዞች የቀረበውን የጨረታ አገልግሎት እየተጠቀመ ይገኛል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
ኮቪድ ድርጅቱ ላይ ብዙ ተፅዕኖ አልነበረውም ማለት ይቻላል ምክንያቱም ይዟቸው የነበሩ ሥራዎችn እያጠናቀቀ ስለነበር ነው። ሆኖም በጊዜው የክፍለ ከተማ ማዕከል ለአራት ወር ተዘግቶ ስለነበር በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ነበረው። ድርጅቱ የያዛቸውን ሥራዎችን አዲስ አበባ በቃሊቲ እና ንፋስ ስልክ አካባቢ እየሠራ ስለነበር ብዙም አልተጎዳም በማለት ገልጸዋል።
ምክር እና እቅድ
ቴክኖሎጂ መጠቀም ለዲዛይን ሥራ በጣም ጥሩ እንደሆነ አቶ ማርቆስ ይመክራሉ። ቀደም ባሉት ዓመታት ዲዛይኖች በእርሳስ እና በማስመሪያ ነበር የሚሠሩት። አሁን በአውቶ ካድ በጥራት በአጭር በጊዜ መሥራት ያስችላል። በመቀጠል ደግሞ (BIM) Building Construction Molding የሚባል ቴክኖሎጂ በመምጣቱ የተለያዩ ነገሮችን በአንድ ላይ ለመሥራት ያስችላል። ለምሳሌ አርክቴክቸራል፣ ስትራክቸራል፣ ሳኒተሪ፣ ኤሌክትሪካል ሥራዎችን በውስጡ ያካተተ ሲስተም ስለሆነ ሥራን በጣም አቅሏል። ጥራትን ጨምሯል እና የጊዜ ፍጆታን ቀንሷል። ስለዚህ አዲስ ጀማሪዎች ራሳቸውን በእነዚህ ሶፍትዌሮች ቢያዳብሩ በጣም ውጤታማ እንደሚሆኑ አቶ ማርቆስ መክረዋል።
ድርጅቱ ወደ ፊት የማማከር ሥራውን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ደረጃ አንድ ለማሳደግ እቅድ አለው።