መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ያሬድ እና ጓደኞቹ ቡና እና ቁርስ

ያሬድ እና ጓደኞቹ ቡና እና ቁርስ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ያሬድ ጌታሁን እና በአራት መሥራች አባላት በ2012 ዓ.ም አጋማሽ ነው። ድርጅቱ የሻይ እና ቡና፣ የቁርስ እና ምሳ እንዲሁም እንዳንድ ቀለል ያሉ የሻይ ሰዓት አገልግሎቶችን በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት አገልግሎት ይሰጣል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ያሬድ እና ጓደኞቻቸው ይህን ዘርፍ ሲመርጡ አንደኛ በሥራው በአረብ አገር ላይ ከዐሥራ አንድ አመት በላይ ያላቸውን የሥራ ልምድ በማመዛዘን እና በመቀጠል ደግሞ ለሥራው የመረጡት ቦታ ለምግብ አገልግሎት ተስማሚ በመሆኑ የምግብ አገልግሎት ዘርፍን ሊመርጡ ችለዋል። ቦታው ግን ሲመርጡት ንፁህ አልነበረም ቆሻሻ የተጣለበት  ኝ አካባቢው ብዙ ሥራ ሊያሠራ የሚችል ቦታ ነበር። አቶ ያሬድ እና ጓደኞቻቸው አንድ ላይ በመሆን ሦስት ሲኖ ትራክ አፈር በማስመጣት ቦታውን በማፅዳት ለሥራ ምቹ እንዲሆን ካደረጉ በኋላ የመሥሪያ ቦታቸውን በመገንባት ወደ ሦስት መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ አውጥተው ድርጅቱን መሥርተዋል። አካባቢው ለሥራ በጣም ተስማሚ ነው ምክንያቱም ብዙ የሥራ መሥሪያ ቦታዎች በአካባቢው ስለሚገኙ።

ድርጅቱ ሲመሠረት በአራት መሥራች አባላት ቢሆንም አሁን መሥራች አባላት ወደ ስምንት አድገዋል። ድርጅቱ አንድ መቶ ሀምሳ ሰው የመስተንግዶ አገልግሎት መስጠት ይችላል። ለሦስት ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ፈጥሯል። አቶ ያሬድ ከጓደኞቻቸው ጋር በመመካከር የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርገዋል፤ እንዲሁም ችግሮችንም በመመካከር ነው የሚፈቱት። የማኅበሩ አባሎች ሥራ በመመዳደብ ድርጅቱን ለማስፋት እየሠሩ ይገኛሉ።

ድርጅቱ ከመቶ የሚበልጡ ደንበኞች ማፍራት የቻለ ሲሆን እነዚህ ደንበኞች ከባንክ፣ ከኢንሹራንስ ካምፓኒ፣ ከፖሊስ ካምፕ፣ ከትልልቅ የግል ድርጅቶች፣ ከተግባረ ዕድ፣ እና ልደታ ፍርድ ቤት አካባቢ እየመጡ የሚመገቡ ናቸው። የዚህ ምክንያት ደግሞ የምግቡ ጥራት እና የዋጋው ተመጣጣኝነት ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ወቅት ብዙና አስከፊ ችግር ነበር። አሁን ቀንሷል፤ ግን ቀጥሎ የመጣው የኑሮ ውድነት የድርጅቱን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል ለምሳሌ አንድ በየአይነት በ35 ብር ነው ድርጅቱ የሚያቀርበው። ነገር ግን የግብዓቶች ዋጋ በጣም ጨምሯል። ለምሳሌ ዘይት ስንት በጣም ተወዷል፤ አሁን ደግሞ ጭራሽ ጠፍቷል። ድርጅቱ ደግሞ ብዙ ተጠቃሚ ደንበኞች አሉት። ነገር ግን የኑሮ ውድነቱ በጣም ድርጅቱን እየጎዳው ነው፤ እንደ ሱቅ ዋጋ ቶሎ ቶሎ መጨመር ከባድ ነው። ስለዚህ መንግሥት የሆነ ነገር ቢያደርግ ጥሩ ነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል የድርጅቱ መሥራች።

ምክር እና እቅድ

አዲስ ወደ ምግብ ሥራ ለሚገቡ ምክር  “ዘርፉ ምግብ እንደመሆኑ መጠን ጥራት ያለው ነገር ማቅረብ አስፈላጊ ነው። ምንም አሁን ያለው የነሮ ውድነት በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ነገሮችን ምንን ከምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ከብዛት ማትረፍ መቻል አለባቸው። ለምሳሌ ደንበኛ በብዛት ምን ይፈልጋል? ያንን መሥራት። በመቀጠል ጊዜውን ያገናዘበ ሸመታ ቀድመው ማድረግ ለምሳሌ ፆም ሲገባ የሚወደዱ ነገሮችን ቀድሞ መግዛት። የሚሠራው ምግቡ ጥራት ያለው መሆን አለበት፤ ሌላው ቢቀር ለህሊና መሥራት መቻል አለባቸው። ከመስተንግዶ ጀምሮ እስከ ምግብ ጥራት በሚገባ መሠራት አለበት። ዘርፉ ላይ ለመሠማራት በጣም ጠንካራ እና ታጋሽ መሆን ያስፈልጋል። ትርፍ ለማግኘት ጊዜ ይወስዳል ስለዚህ በትዕግስት ሥራውን መሥራት ተገቢ ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ድርጅቱ ወደ ፊት የተሟላ አገልግሎት በመስጠት እና እንጀራ በብዛት በማቅረብ ለተለያዩ ድርጅቶች እና አቅራቢዎች ለማድረስ በእቅድ ላይ ይገኛል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …