መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ቴዎድሮስ አባይ የኤሌክትሮኒክስ እና ስፖርት እቃዎች አቅራቢ

ቴዎድሮስ አባይ የኤሌክትሮኒክስ እና ስፖርት እቃዎች አቅራቢ

ድርጅቱ የተመሠረተው በ 2005 ዓ.ም መጨረሻ በአቶ ቴዎድሮስ አባይ ነው። ይህ ድርጅት የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እና የስፖርት እቃዎችን የሚያቀርብ ድርጅት ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ እና የስፖርት እቃዎችን በበቂ ብዛት እና ጥራት የማቅረብ አቅም አለው።

ማስፋፋት እና ማስተዋወቅ

አቶ ቴዎድሮስ ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት መጽሔት ሲሸጡ ቆይተዋል። ነገር ግን የእጅ ስልኮች ሲመጡ እና ኢንተርኔት ሲስፋፋ ሠው በሙሉ መጽሔትን መጠቀም በመተው ኢንተርኔት መጠቀም ሲጀምር፣ እሳቸውም የመጽሔት ሥራውን በመተው ወደ ሶፍትዌር ወደመሸጥ ሥራ ገብተዋል። በሶፍትዌር ሥራ ለተወሰነ ጊዜ እንደሠሩ የፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት (በተለምዶ ዋይፋይ) እየተስፋፋ መጣ። ዋይፋይ ሲመጣ ደግሞ ሰው ሶፍትዌር በቤቱ ዳውንሎድ ማድረግ ጀምሮ ሥራው እየቀነሰ ስለመጣ እሳቸውም አሁን ወዳሉበት ንግድ ሥራ ገብተዋል።

የድርጅቱ መሥራች የሶፍትዌር ሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት ብዙ ችግሮች ነበሩ የኢንተርኔት እና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ  ሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበራቸው። አቶ ቴዎድሮስ የራሳቸው ህልም ስለነበራቸው የነበሩትን ችግሮች በመቋቋም ራሳቸውን ለማሳደግ እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ምን አይነት ሥራ መሥራት እችላለሁ የሚለውን እና ብዙ ነገሮችን ለማየት ኢንተርኔት በመጠቀም ብዙ ነገሮች ሊማሩ ቻሉ። አሁን ላይ ድርጅታቸው የቴሌ ብር፣ ኤም ብር እና ሲቢኢ ብር ኤጀንት ነው። ቴክኖሎጂ መጠቀም ለድርጅቱ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፤ እቃ ከመግዛት ጀምሮ ክፍያ እስከ መፈፀም እና ለደንበኛ እስከመስጠት ድረስ ሁሉ ነገር በቴክኖሎጂ ነው ሥራ የሚሠራው። ድርጅቱ ምርቱን ለማስተዋወቅ የቴሌግራም ቻናል ይጠቀማል teddysoft sport telegram channel እንዲሁም የዩቲዩብ ቻናልም ለመጀመር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ተፅዕኖ ነበረው ምክንያቱም ድርጅቱ እቃ የሚያመጣው ከውጭ ስለሆነ በኮቪድ ምክንያት ደግሞ እንቅስቃሴ እና መንገድ ተዘግቶ ስለነበር ትልቅ ችግር ነበር። የተቀመጡ እቃዎችን በመሸጥ እና አቶ ቴዎድሮስ ብዙ ሰዎችን ስለሚያውቁ ከነሱ ጋር በመነጋገር እና በመረዳዳት ሊያልፉት ችለዋል።

ምክር እና ዕቅድ

ድርጅቱ ሲመሠረት በአምስት ሺህ ብር ነበር፤ አሁን ከመቶ ሺህ ብር በላይ ካፒታል እና አንድ ሺህ ገደማ የሚጠጉ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል። ለዚህ ስኬት ሊበቃ የቻለው የሚያቀርባቸው እቃዎች ጥራታቸውን የጠበቁ እና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ ስለሆነ  ነው።

ወደ ሙያው የሚሰማራ ሰው አንድ ቋንቋ (እንግሊዘኛ) ማወቅ አለበት፤ ሁለት የሚሸጠውን እቃ ምንነት ማወቅ አለበት፤ ሶስተኛው እና ዋናው በዚህ ዘርፍ  ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በንግድ ዓለም ላይ ደንበኛ ንጉሥ ነው ስለዚህ ደንበኛን ማክበር አለበት። የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ሽያጭ በትንሽ  ተጀምሮ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ሥራ ነው ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ድርጅቱ ወደ ፊት አስተማማኝ እና ታዋቂ የሆነ የኤሌክትሮኒክስ እቃ አቅራቢ ሆኖ ስሙን ለመትከል እቅዶ እየሠራ ይገኛል።

ይህንንም ይመልከቱ

ሀሌታው ሀ ኅትመት እና ማስታወቂያ

ድርጅት የተመሠረተው በአቶ ዮናታን ታደሰ እና ሦስት መሥራች አባላት በ2012 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የኅትመት …