መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ደሳለኝ እሸቱ ግንባታ ማጠናቀቅና ሕንጻ ተቋራጭ
dessalegn-finishing

ደሳለኝ እሸቱ ግንባታ ማጠናቀቅና ሕንጻ ተቋራጭ

ደሳለኝ እሸቱ ግንባታ ማጠናቀቅ ሕንጻ ተቋራጭ ድርጅት የተመሠረተው በ2007 ዓ.ም በግል ኢንተርፕራይዝነት በአቶ ደሳለኝ እሸቱ ነው። ድርጅቱ የሚሠራቸው ሥራዎች አጠቃላይ የፊኒሺንግ ሥራዎች ናቸው።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ደሳለኝ ይህ ድርጅት ከመመስረታቸው በፊት በፕላስቲክ ፋብሪካ ውስጥ ለስምንት ዓመት ተቀጥረው ሲሠሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ በዚያን ጊዜ እዚህ ግባ የሚባል ገቢ ወይም ጥሪት አልነበራቸውም። እሳቸው ከበፊት ጀምሮ የፊኒሽኒንግ ሙያ ይስባቸውና ያስደስታቸው ነበር። ይህንንም ሙያ የመማር እና የማወቅ ትልቅ ጉጉት ነበራቸው። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች መማር ባለመቻላቸው ጊዜ እየተራዘመ ቢሄድም በአንድ ወቅት በተፈጠረ አጋጣሚ የመማር እድል አገኙ። በፋብሪካ ውስጥ እየሠሩ ለሦስት ዓመት የማታ የፊኒሺንግ ትምሕርት ተምረው ከጨረሱ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል በፋብሪካው ከሠሩ በሁዋላ ነው ድርጅቱን የመሠረቱት። አቶ ደሳለኝ በፊኒሺንግ ሥራ ራሳቸውን ችለው በመሥራት የአምስት ዓመት የሥራ ልምድ አላቸው።

ድርጅቱ በዋናነት የሚሠራቸው ሥራዎች ፣

  • የውስጥ እና የውጭ የቀለም ቅብ ሥራዎች፤
  • የሕንፃ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፤
  • የፊኒሺንግ ቻክ እና ሴራሚክ ሥራዎችን በጥራት ይሠራል።

ድርጅቱ አንድ የቀበሌ ወይም የወረዳ ይዘት ያለው ሕንጻን ከሠላሳ እስከ ስድሳ ቀናት ውስጥ የማጠናቀቅ አቅም አለው። የጊዜ ገደቡ እንደ ሕንጻው ዲዛይን እና የጥሬ እቃ አቅርቦት ይወሰናል። ይህ ድርጅት ለአራት ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ሲሆን፣ እንዲሁም ሥራ ሲበዛ ደግሞ ለሚጨመሩ ስምንት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ይህ ድርጅት ቃሊቲ እና ኮተቤ አካባቢ የሚገኙ ሕንጻዎች የማጠናቀቅ ሥራ ጨርሶ አስረክቧል። አሁን ደግሞ አራብሳ ኮንዶሚኒየም እየሠራ ሲሆን በቅርቡ አጠናቆ ያስረክባል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በመንግስት ትስስር እና በሰው በሰው ትውውቅ ነው። በቅርቡ ደግሞ አቶ ደሳለኝ 2merkato.com በከፍታ ፓኬጅ ለኢንተርፕራይዞች ያዘጋጀውን አገልግሎት  (የገበያ ትስስር (የማስታወቂያ) እና የጨረታ አገልግሎት) በመጠቀም ይበልጥ ብዙ የሥራ ትስስር በማግኘት አቅማቸውን ለማሳደግ ወስነዋል።

አቶ ደሳለኝ በህይወታቸው በግል ሥራ እና ተቀጣሪነት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ ሲሉ አስረድተዋል። ለምሳሌ እሳቸው በፋብሪካ ውስጥ በሚሠሩበት ጊዜ መሥራት ቢፈልጉ እንኳን አይችሉም ነበር አሁን ግን የራሳቸው ሥራ ስለሆነ የፈለጉትን ሥራ ጊዜና ሌሎች ከልካይ ነገሮች ሳይግድቧቸው መሥራት ይችላሉ። ለዚህም ነው እሳቸው ሲጀምሩ ከነበራቸው መነሻ ካፒታል አንድ ሺህ ብር አሁን ወደ አንድ መቶ ሺህ  የሚጠጋ ካፒታል ማደግ እና ሦስት ደንበኞችን ማፍራት የቻሉት። ነገር ግን በየመሀሉ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ ለምሳሌ የዕቃ መወደድ እና ድንበኞች ክፍያን በአግባቡ አለመክፈል፤ እነዚህን ችግሮች በትዕግስት እና በተረጋጋ መንፈስ ማስተናገድ ለውጤታማነት ያበቃል ይላሉ የድርጅቱ መሥራች።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ በድርጅት ሥራ ላይ ብዙ ችግር አልነበረውም ምክንያቱም ሥራው በባህሪው ከሰው ጋር የሚያገናኝ አይደለም። ባለሙያዎቹ የተሰጣቸውን ሥራ  ለብቻቸው ነው የሚሠሩት፤ ከሰው ጋር ብዙ ንክኪ የለውም። እንዲሁም በወቅቱ የያዙት ሥራ ስለነበር የኮቪድ መከሰት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳት አላደረሰባቸውም። ይህ ማለት ግን በአጭር ጊዜ ከባድ ጉዳት አላደረሰብኝም ቢሉም  በእቃዎች ላይ የነበረው የዋጋ መናር ድርጅቱ ላይ  ተፅዕኖ ነበረው።

ምክር እና እቅድ

አዲስ ወደ ፊኒሽኒንግ ሥራ የሚገቡ ሰዎች ስለሥራው ዕውቅት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት አለባቸው። በንግድ ሥራ ብዙ ሥራ ተቀብሎ በወቅቱ ምላሽ ባለመስጠት ደንበኛን ማጉላላት ተገቢ ካለመሆኑ በላይ በሂደትም ንግድ ሥራ ላይ ጉዳትና ኪሳራ በማስከተል ከሥራ ውጭ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ዛሬ የሚያልቅ ሥራ ዛሬ ማለቅ አለበት። ያለበለዚያ በአንድ ጊዜ ብዙ ሥራ ሊሠራ ይችላል ተብሎ ሥራዎችን ማቀዝቀዝ አይገባም ምክንያቱም ደንበኛ ጋ አንዴ ቅሬታ በመፍጠር እርካታን ከማሳጣቱ በላይ ለኪሳራ ይዳርጋል። ስለዚህ ለሁሉም ሥራ የሚያስፈልገውን የሰው ሃብት፣ ማሽን፣ ጥሬ ዕቃ፣ ፋይናንስ መመደብ፣ በተባለው የጊዜ ገደብ ማስረከብ እና ብክነት መቀነስ መቻል አለባቸው ብለው ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ድርጅቱ ከአምስት ዓመት በኋላ የግንባታ ማጠናቀቅ ሥራን ከፍ በማድረግ ወደ ሕንጻ ተቋራጭ የማደግ እቅድ ያለው ሲሆን በተጨማሪም የአሉሚኒየም ሥራ የመሥራ ዕቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …