መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ዘነበች፣ ኪያ እና ጓደኞቻቸው ጋርመንት

ዘነበች፣ ኪያ እና ጓደኞቻቸው ጋርመንት

ድርጅቱ የተመሠረተው ወ/ሮ ዘነበች ንጉሴ እና በሦስት መሥራች አባላት በ2008 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የጋርመንት ሥራዎችን በጥራት ይሠራል።

ድርጅቱ በዋናነት የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የህጻናት አልባሳት
  • የወንድ እና የሴት ቱታዎች
  • የህጻናት እና የዐዋቂዎች ቀሚሶች እና
  • ፒጃማዎች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ ዘነበች ወደ ጋርመንት ሥራ ከመግባታቸው በፊት በአልባሳት ንግድ ሥራ የተለያዩ አልባሳትን ከተለያየ ቦታ በማምጣት እና በመሸጥ ረዘም ላለ ጊዜ የሠሩ ሲሆን ልጆቻቸውንም በሥራው አሳድገውበታል። ሥራው ፈታኝ ቢሆንም እሳቸው ግን ጠንካራ የሥራ ባሕል የተማሩት ከእናታቸው ነው። ወ/ሮ “የዘሩትን ለማጨድ መታገስ ያስፈልጋል ዛሬ ዘርቶ ዛሬ ማጨድ አለብኝ የሚባል ነገር የለም። ገበሬ ዘር ዘርቶ በቂ ጊዜ ይፈልጋል።  ስለዚህ መታገስ ያስፈልጋል።” የሚለው የእናታቸው አባባል ብዙ ነገሮችን በትዕግስት ማሳለፍ እንዲችሉ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።

ይሁን እና እቃዎች መወደድ ሲጀምሩ እና ሥራው ትንሽ መቀዝቀዝ ሲጀምር ሌላ አማራጭ መፈለግ ጀመሩ። ቱሉዲምቱ አካባቢ የጋርመንት ሥራ ከምትሠራ ጓደኛቸው ጋር የጋርመንት ሥራን እንዴት መጀመር እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ምርቱን በብዛት ሊገዛ የሚችል ደንበኛ፣ የሳቸው የደንበኞች እነማን  ሊሆኑ እንደሚችሉ እና ፍላጎት እና ምርጫቸው ላይ ተወያዩ። ከተወያዩም በኋላ የህጻናት አልባሳት እና ቀሚስ የጥሬ እቃ ወጪያቸው ከባድ ቢሆንም ቀለል ያሉ ሥራዎች ስለሆኑ እነዚህን ለመሥራት በማቀድ ወደ ጋርመንት ሥራ ተቀላቅለዋል።

ድርጅቱ አሁን ላይ አጠቃላይ የጋርመንት ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ለአምስት ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ወ/ሮ ዘነበችም በሥራው ላይ ያላቸው ዕውቀት ሰፍቷል። ያሉትን የማሽን ቁጥሮች ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ በቀን ሠላሳ አልባሳትን የማምረት አቅም አለው። ድርጅቱ አሁን ባለው ዋጋ የህጻናት ልብሶችን ከሦስት መቶ ሃምሳ ብር እስከ አራት መቶ ብር በማረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። ድርጅቱ ሲመሠረት የነበረው መነሻ ካፒታል ሁለት ሺህ ብር የነበረ ሲሆን አሁን የካፒታሉን መጠን ወደ ስምንት መቶ ሺህ ብር ማሳደግ ችሏል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው ጎፋ መብራት ኀይል ያለው ሱቅ የሚመጡ ደንበኞች ከሚመጣ ትዕዛዝ እና ኤግዚብሽን እና ባዛር ላይ በመሳተፍ ከሚመጣ ገበያ እንደሆነ ከባዛር የሚገኘወም ሥራ በየጊዜው እያደገ እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከሄሎ ማርኬት ጋር አብረው በመሥራት ብዙ ልብሶችን መሸጥ ችለዋል።

ምክር እና ዕቅድ

የግል ሥራ ያለው ሰው ተግባቢ እና ታጋሽ የሆነ እንዲሁም እንደ ደንበኛው ፍላጎት የመሥራት ግዴታ እንዳለበት የተረዳ፣ ልባዊ ፈገግታ የሚታይበት፣ የሙያ ብቃት እና ዕውቀት ያለው መሆን ይኖርበታል። የገበያ ጥናት ከራስ ጋር፣ ከቤተስብ ጋር በመመካከር እና እጅ ላይ ባለ ሀብት ለገበያው ምን ማድረግ እንደሚገባ፣ በዚህ ምን መሥራት እችላለሁ የሚለውን በማሰብ ወደ ሥራ መግባት ጥሩ ነው። ከምንም በላይ ግን የራስ ተነሳሽነት እንዲሁም ፈተና ለማለፍ ትዕግስት እና ጽናት በጣም አስፈላጊ ነው።

ድርጅቱ አሁን ከአዲስ ካፒታል ጋር በመሆን ባስገባቸው አዳዲስ ማሽኖች የዐዋቂ ሸሚዝ በመጪው አዲስ ዓመት መሥራት ይጀምራል። ከሁለት ዓመት በኋላ ስድሳ የሚደርሱ ማሽኖችን በማስገባት ለውጭ ሀገር ገበያ ጭምር ለማቅረብ ዕቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …