መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / በከፍታ የቴሌግራም ቻናል የሥራ ትስስር አግኝተናል – ጦቢያ ብረታ ብረት ማሽን ሥራ

በከፍታ የቴሌግራም ቻናል የሥራ ትስስር አግኝተናል – ጦቢያ ብረታ ብረት ማሽን ሥራ

ጦቢያ ብረታ ብረት ማሽን ሥራ የተመሠረተው በ2000 ዓ.ም ዐሥራ ሰባት ሺህ ብር ብድር በመበደር ነበር። ድርጅቱ የተመሠረተው በስድስት መሥራች አባላት ሲሆን፣ በነበረው የልምድ፣ የሙያ እና የፍላጎት መከፋፈል ምክንያት አምስት የድርጅቱ መሥራች አባላት የወጡ በመሆኑ በአሁን ወቅት አቶ ሚሊሻ ባህሩ ብቻ ድርጅቱን እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ምሥረታና ዕድገት

ጦቢያ ብረታ ብረት ማሽን ሥራ በ2000 ዓ.ም ቢመሰረትም እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ጥቃቅን እና መካከለኛ ማሽንኞችን ማለትም እንደ ሽንኩርት መፍጫ፣ የውሀ ማሞቂያ የመሳለሉትን ማሽኖች በመጠገን ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። የጥገና ቆይታ ጊዜውም ልምድ ለመቅሰም እና ወደ ውድድር ለመግባት ዝግጁ እንዲሆን እንዳደረገው የድርጅቱ መስራች ገልፀዋል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለሆቴል እና ለካፌ አገልግሎት የሚውሉ የሻይ ማፊያ ማሽኖችን መሥራት በመጀመሩ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደ ነበረው አቶ ሚሊሻ ባህሩ ጥቅሰዋል። ይሁን እና እንጂ ከ 2005 አስከ 2006 ዓ.ም ገደማ የመጣው የጀበና ቡና ሥራ የማሽን ሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፤ ይህም ድርጅቱ እንዳያድግ መሰናክል ሆኖ እንደ ነበር ገልፀዋል። ይሁን እና እንደዚህ አይነት ችግር ሲያጋጥም መፍትሔ መፈለግ ስለሚገባ ከሚጠገኑት ማሽኖች በተቀሰመ ልምድ እና ተሞክሮ የኬክ ማሳያ ፍሪጅ (Cake Display) እና የኪችን ዳክት በማምረት እንዲሁም የሽንኩርት መፍጫ ማሽኖችን በሀገር ውስጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ሰርቶ ለገበያ በማቅረብ የነበረውን የሥራ መቀዛቀዝ ሊያረጋጉት እንደቻሉ የድርጅቱ መሥራች ገልፀዋል።

የዋጋ ንጽጽር

  • ኬክ ዲስፕሌይ ከውጭ የሚመጣው ሁለት መቶ አርባ ሺህ ብር (240,000) ሲሆን ድርጅቱ በዘጠና ሺህ ብር (90,000) ያመርታል፡፡
  • የሻይ ማሽን ከውጭ የሚመጣው ሁለት መቶ ሀያ ሺህ ብር  (220,000) ሲሆን ድርጅቱ በሀምሳ ሺህ ብር (50,000) ያመርታል።
  • እንዲሁም ለሚያመርታቸው ምርቶች ጥራቱን የጠበቀ የሰርቪስ አገልግሎት ይሰጣል።

ጦቢያ ብረታ ብረት ማሽን ሥራ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የኬክ ዲስፕሌይ ማሽኖች ከማቀዝቀዣ ፍሪጆች ጋር
  • የኪችን ዳክት (ዘመናዊ የማዕድ ቤት ጭስ ማውጫ ማሽኖች)
  • የሽንኩርት መፍጫ ማሽኖች
  • ዘመናዊ የሆኑ የሻይ ማፍያ ማሽኖች

ድርጅቱ በዐሥር ቀን ከአንድ እስከ አራት የኬክ ዲስፕሌይ ማሽኖችን የማምረት አቅም ያለው ሲሆን ኪችን ዳክት (ጭስ ማውጫ) ደግሞ በሦስት ቀን አንድ የማምረት አቅም አለው። የሻይ ማሽን የማምረት አቅም – እንደሚኖረው የእቃው አቅርቦት፣ ከአምስት እስከ ዐሥር ባሉ ቀናት ውስጥ ማምረት ይችላል። ድርጅቱ ለሁለት ሴት እና ለአምስት ወንድ ሠራተኞች ቋሚ የሥራ እድል ፈጥሮ ይገኛል። እንዲሁም አምስት ጊዜያዊ – ሥራ ሲበዛ – የሚመጡ ሠራተኞች አሉ።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ሚሊሻ ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት የተለያየ ቦታዎች የመስራት እድሉ ነበራቸው፤ ከ1991 ዓ.ም እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ለሰባት አመት በሀገር መከላከያ ድርጅት ውስጥ በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል። አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ በማሽን ጥገና ለሦስት አመት በግለሰብ ቤት ሲሠሩ ቆይተዋል። ከዚህ በመቀጠል አስፈላጊውን ልምድ እና ክህሎት ከያዙ በኋላ ጦቢያ ብረታ ብረት ማሽን ሥራ ድርጅትን አንዱ መሥራች አባል በመሆን ድርጅቱን መሥርተዋል። ምርት በማምረት ላይ ከተሰማሩ ዐሥራ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል።

አቶ ሚሊሻ የራሳቸው ድርጅት ከከፈቱ በኋላ በውትድርና አገልግሎት ወቅት የተማሩት ስነ-ምግባር የግላቸውን ሥራ ሲጀምሩ በጣም እንደ ጠቀማቸው ገልፀዋል። ለምሳሌ ሥራን በማክበር፣ ለዓላማ ፅኑ መሆን እና ምንም አይነት ፈተና ቢመጣ እንዲቋቋሙ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

መሥራቹ ይህን የሙያ ዘርፍ የመረጡበትን ምክንያት አንዲህ ሲሉ ገልፀዋል። “እቃ ገዝቶ መሸጥ ቀላል ነው ነገር ግን ማምረት በጣም ደስ ይላል። አንድን ሥራ እኔ ነኝ የሠራሁት ብለህ ስታሳይ ያለው ስሜት ደስ ይላል። ከዚህ በተጨማሪ ለመጠገን የሚመጡ ማሽኖች ሲመጡ እና ሲጠገኑ ማሽኑ ለመጠገን ሲፈታ አዳዲስ ነገሮች የማየት እና የመማር እድል ይፈጥራል። ይህ ደግሞ ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ላይ በየጊዜው አዳዲስ እና የተሻሻሉ ነገሮችን እንዲጨምር እንዲሁም ዘመናዊ እንዲሆን ረድቶታል።” ድርጅቱ ውጤታማ ሊሆን

kitchen-duct

ከቻለባቸው መንገዶች ውስጥ ድፍረት አንዱ ሲሆን ይህም የማይታወቀውን ነገር እስከ መጨረሻ ድረስ በመጠየቅ ነው ሥራ የሚሰራው፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ድፍረት ያስፈልጋል። እንዲሁም ለመማር የትም ቦታ ድረስ ለመሄድ ፈቃደኛ መሆን ሌላው አስፈላጊ ነገር ነው። የማሽን ሥራ ዘወትር አዳዲስ ነገሮችን ያስተምራል፤ ድርጅቱም እየተማረ እራሱን እያሻሻለ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ሊደርስ ችሎአል። እንዲሁም የከፍታን የቴሌግራም ቻናል በመጠቀም ሥራዎቹን በማስተዋወቅ የሥራ ትስስር ሊያገኝ እንደቻ አቶ ሚሊሻ ጠቅሰዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ

በኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ ምክንያት ምንም አዲስ የተከፈቱ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ካፌውም፣ ወዘተ አልነበሩም። በሥራ ላይ የነበሩትም ሥራ አቁመው ስለነበር በዚህ ምክያት ሥራ ቀዝቅዞ ነበር። ነገር ግን ድርጅቱ በሚሠራው የማሽን ጥገና ሥራ ምክንያት የሥራ እንቅስቃሴ በሙሉ ስላልቆመ ሠራተኛም ሳይቀነስ ሊቀጥል ችሏል።

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ ሥራ የሚያገኘው በሰው በሰው ሲሆን ይህም አንድ ደንበኛ እቃ ከገዛ በኋላ የሰርቪስ አገልግሎት ስለሚኖረው ቋሚ ደንበኛ ይሆናል ማለት ነው። ለምሳሌ ኪችን ዳክት በዓመት አንድ ጊዜ ይጸዳል፤ ሻይ ማሽኑም እንደዚሁ፣ ኬክ ዲስፕሌይም እንደዚሁ በረዶ ሲይዝ ወይም ማንኛው አይነት ብልሽት ሲያጋጥመው አጠቃላይ የጥገና ሥር ይሠራል።ይህም ሌሎች ደንበኞችን ሊያመጣ ችሏል። አሁን ደግሞ በቅርብ ኢንተርኔት በመጠቀምም ሥራ አንደሚያገኙ ገልጸዋል።

ጦቢያ ብረታ ብረት ማሽን ሥራ ለወደፊቱ የሚያመርተውን ማሽን አይነት እና ብዛት በመጨመር ትልቅ አምራች ድርጅት ለመሆን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

አሁን ባለው ሁኔታ በድርጅቱ የሥራ ዘርፍ ብዙ ጨረታዎች ስለማይወጡ እና ቢወጡም የሚጠይቁት መስፈርት ከድርጅቱ ከአቅም በላይ ስለሆኑ ወደፊት የድርጅቱ አቅም ሲጠነክር በከፍታ በኩል የሚመጣውን 2merkato.com የጨረታ እና ማስታወቂያ አገልግሎት ለመጠቀም እቅድ አንዳላቸው ገልጸዋል።

ማንም ሰው የሚሠራውን ሥራ በሚገባ ማወቅ አለበት።  ሰው ተቀጥሮ ሙያ ቢማር ከፍሎ ከሚማር የተሻለ ያውም እየተከፈለው ሙያ ማወቅ ይችላል፣ በደንብ ከሥራው ጋር ይጣመራል። ስለዚህ ማንም ከፍሎ ከሚማር ይልቅ የሚፈልገውን ሙያ ጥቂት መስዋዕትነት በመክፈል ተቀጥሮ ከታች ጀምሮ ቢማር በጣም ተጠቃሚ ይሆናል። ዋናው ነገር ግን የሚወደውን ሥራ እንዲሠራ እና ሲሠራ ትዕግስት እንዲኖረው ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …