ብሩክ እና አስማረች ኮንስትራክሽን እና ማኑፋክቸሪንግ የተመሠረተው በ 1996 ዓ.ም በ አቶ ብሩክ ዘውዴ እና ዐሥራ አራት መሥራች አባላት ነው። ድርጅቱ ከተግባረ ዕድ የቴክኒክ እና ሙያ ት/ቤት ጋር በመተባበር ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርቷል እየሠራም ይገኛል። እንዲሁም ትልልቅ የማኑፋክቸሪንግ ማሽኖችን በመሥራት ለገበያ ያቀርባል። ቆየት ላሉ ማሽኖች ደግሞ የጥገና አገልግሎት ይሰጣል።
ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ
- የኮንስትራክሽን ማሽኖች
- ፕሪካስት
- የፕሪካስት ሞልድ
- የቤት እና የቢሮ የፈርኒቸር እቃዎች
- ሶፋዎች
- ቁም ሳጥን
- ጌጣጌጦች
- በር እና መስኮት እንዲሁም የሕንጻ የፊኒሽንግ ሥራዎችን በጥራት ይሠራል።
ማስተዋወቅ እና መስፋፋት
አቶ ብሩክ ዘውዴ ወደ የማኑፋክቸሪንግ የሥራ መስክ ከልጅነቻቸው ጀምሮ ያደጉበት ነው፤ በዐሥራ ሁለት አመታቸው ደሴ በመሄድ የፈርኒቸር ሥራ ሠርተዋል። በሙያው ከልጅነቻቸው ጀምሮ ማደጋቸው ሙያውን እንዲወዱት አድርጓቸዋል። ይህም በህይወታቸው ለማንኛውም ሥራ ሙሉ መነሻ እና ጉልበት እንደሆናቸው አክለዋል። አቶ ብሩክ ያላቸውን የእንጨት ሥራ ፍላጎት አዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ትምሕርት ቤት በመግባት በእንጨት እና ማኑፋክቸሪንግ ሥራ ላይ ያላቸውን እውቀት አጠናክረዋል። ትምሕርታቸውን እንደጨረሱ እሳቸው እና ዐሥራ አራት አባላት በመሆን በ 1996 ዓ.ም ተደራጅተው ሥራ ጀምረዋል። ድርጅቱ በዐሥራ አራት አባላት የተመሠረተ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ዘጠኝ አባላት ወጡ። በአምስት አባላትም ረዘም ላለ ጊዜ ከቆየ በኋላ ሦስት አባላት በመውጣታቸው በአሁን ጊዜ በሁለት አባላት ብቻ አየተስደዳደረ ይገኛል ።
ድርጅቱ ተመሥርቶ ሥራ በጀመረበት ወቅት አመቺ የሆኑ የሥራ እድሎች ነበሩ፤ ሥራም በበቂ ሁኔታ ነበር። ድርጅቱም በጥሩ እንቅስቃሴ ነበር። ችግር መከሰት የጀመረው ጥሩ ገንዘብ መምጣት ሲጀምር ነው፤ ይህም ገንዘብ ያላግባብ ማባከን፣ ኦዲት ሳይደረግ የተለያዩ አላስፈላጊ አገልግሎቶች ላይ ማዋል ተጀመረ። አግባብነት የሌለው የገንዘብ አጠቃቀም በመኖሩ ድርጅቱን አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን ብር እዳ ውስጥም ከትቶት ነበር። በነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች የድርጅቱ ሁኔታ እየተዳከመ ሲመጣ አባላቶቹም መውጣት ጀመሩ። አቶ ብሩክ ግን ተስፋ ስለነበራቸው እና ሙያውን ይወዱት ስለነበር እሳቸው የሚሠራቸው ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን በመጠቀም አዳዲስ ነገሮችን በመሞከር እና ሥራ ውስጥ በማስገባት እየሰሩ ቆይተዋል።
ድርጅቱ የነበረበትን እዳ ለመጨረስ እና ወደ ተሻለ መስመር ለመግባት አቶ ብሩክ ከ ወ/ሮ አስማረች ጋር በመነጋገር ትክክለኛ አቅጣጫ በመቅረፅ በትጋት በመሥራት እና ሌሎችም የራሳቸውን ፈጠራዎች በማከል ሥራቸውን ቀጠሉ። ትልልቅ የሊዝ ማሽኖች ብልሽት ሲያጋጥማቸው ሞዲፍኬሽን ሠርቶ በመጠገን እንዲሠሩ በማድረግ፣ በተጣሉ ካርቶኖች ሁለት እና አራት ሰው ማስቀመጥ የሚያስችሉ ወንበሮችን በመሥራት፣ እንዲሁም ወረቀቶችን በመሰብሰብ የተለያዩ አይነት ቅርጻ ቅርጽ ያላቸው ጌጣጌጦች በመሥራት እና ድርጅቱ የሚያገኘውን ማንኛውም አይነት ሥራ ሳይመርጡ በመሥራት ሥራቸውን ማሳደግ ያዙ። እንዲሁም ከተግባረ ዕድ ጋር በመተባበር ድጋፍ እና ሥልጠናም ወሰዱ። ተግባረ ዕድንም በማገዝ ብዙ ሥራ የመሥራት እድል አጋጥሟቸዋል። በዚህም ድርጅቱ ያለበትን አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር እዳ ከፍሎ በመጨረስ የአንድ ሚሊየን ብር ካፒታል ማፍራት ችሏል።
ድርጅቱ አንድ የኮንዶሚኒየም ሕንጻ በር እና መስኮቶችን በሶስት ቀን የመጨረስ አቅም አለው። ይህም ማለት አርባ መስኮቶች እና ሀያ በሮች በሶስት ቀን የመጨረስ አቅም አለው። እንዲሁም በሶስት ቀን ውስጥ አንድ ሶፋ ማውጣት ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ብሎኬት፣ ፕሪካስት በማምረት እና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሚሠራበት ወቅት እስከ አርባ ለሚደርሱ ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። አሁን ግን የኮንስትራክሽን ሥራ በጣም በመቀዝቀዙ ሙሉ ኃይሉን ማኑፋክቸሪንግ ላይ በማድረግ እየተንቀሳቀ ይገኛል፤ በዚህም ሁኔታ ለሁለት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሮ ይገኛል። ድርጅቱ አዳዲስ ሥራ የሚሠራው በሰው በሰው እና ቢዝነስ ካርድ በመጠቀም ነው።
አቶ ብሩክ ተቀጣሪነት እና ቀጣሪነት ያላቸውን ልዩነቶች እንደሚከተለው አስረድተዋል። ተቀጥረው ሲሠሩ ያለው ጥቅም:- ተቀጥሮ መሥራት ደመወዝ አለው እና ደግሞ ባለቤትን የሚያሳስቡ ነገሮች አያሳስቡም። ለምሳሌ የጥሬ እቃ መወደድ ወይም አለመኖር በሥራው ሂደት ላይ ከሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት እና ብዙ ነገሮች አያሳስቡም። አንድ ሰው ተቀጥሮ ሲሠራ ብዙ ነገሮች የመማር እድል ያገኛል ጎበዝ ከሆነ። የራሱን ሥራ ሲሠራ ደግሞ የጊዜ ነጻነት አለው። የፈለገውን ሥራ መሥራት ይችላል የሚያግደው ራሱ ግለሰቡ ነው እንጂ ቆራጥነት ካለው የፈለገውን ማሳካት ይችላል። ስለዚህ የተስተካከለ ነገር እና ራዕይ ካለው የራስ ሥራ በጣም ይጠቅማል ካልሆነ ግን አይመከርም ሲሉ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።
ድርጅቱ እዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው በትምህርት፣ በሥራ ልምድ እና ሰዎችን በመጠየቅ እንዲሁም እንድን ሥራ ለመሥራት ቦታው ድረስ መሄድ እና መገኘት ካለበት በመገኘት በመመልከት እና በመጠየቅ ነው። ጥያቄ መጠየቅ በጣም ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል የድርጅቱ መሥራች። አንዳንዴ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትዕግስት ማለፍ ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ጨረታ ላይ ብቁ የሆነ ድርጅት እያለ ምንም ስለ ሥራው እውቀቱ የሌለው ሰው ሰብሮ ይገባና ከዛም ያሸንፋል። የሥራው ግንዛቤ ስለሌለው ሥራውን አይሰራም ወይም ደግሞ ሥራውን ይዞ ባለሙያዎች በማምጣት ያሠራል ይህ ደግሞ ሥራው በሚገባው ጥራት እና ጊዜ እንዳያልቅ ያደርጋል። እንደዚህ ዐይነት ችግሮች ስለሚያጋጥሙ በምን አይነት ፈተና ተስፋ አለመቁረጥ በጣም አስፈላጊ ነው ይላሉ።
የኮቪድ ተፅዕኖ
የኮቪድ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ድርጅቱ ምንም ሥራ አልነበረውም። እቃም ገበያ ላይ የለም እቃ የሚገኘው በሰው በሰው እሱም በጣም በውድ ዋጋ ነው። ስለዚህ ድርጅቱ ብዙ ሠራተኞችን ቀንሶአል። አቶ ብሩክም የራሳቸውን የፈጠራ ውጤቶች በመጠቀም የተለያዩ ጌጣጌጦች በመሥራት እና በመሸጥ ሊያልፉት ችለዋል።
ምክር እና እቅድ
የገንዘብ አጠቃቀማችን ጥሩ ስላልነበር ድርጅቱ ትልቅ ደረጃ መድረስ ሲችል፣ ሳይደርስ ቀርቷል። የገንዘብ አያያዝ ሥልጠና ቢኖር ግን ይህ አይፈጠረም ነበር። ስለዚህ አሁን ላይ ግን የገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከት የወሰድነው ሥልጠና በጣም ጠቃሚ ስለሆነ ማንም ሰው ሥራ ሲጀምር ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም አለበት ሲሉ መክረዋል።
አቶ ብሩክ አንድ ሰው ወደ እንጨት ሥራ ሲገባ፣ “ሥራውን መውደድ አለበት ሁለተኛ ደግሞ የሚሠራውን ሥራ በመዝናናት ቢሠራ ውጤታማ መሆን ይችላል ምክንያቱም አይሠለቸውም። ሌላው ደግሞ ቆረጣ እና ልኬት ላይ በጣም ጎበዝ መሆን ያስፈልጋል ፈርኒቸር ላይ እቃ ማትረፍ የሚቻለው በዚህ ስለሆነ ነው። ለምሳሌ አንድ ቁም ሳጥን በስምንት ሺህ ብር ብትሠራ ትርፉን ማቴሪያል ታስቀምጠዋለህ። ከዛም ትንንሽ ኮመዲኖ ለመሥራት ያገልግላል። እንጂ አንድ ኮመዲኖ ለመሥራት ሁለት ኮምፖርሳቶ ይፈጃል ስለዚህ በአንድ ሺህ ብር ብትሠራው አያዋጣም ነገር ግን ከቁም ሳጥን በተረፈው የምትሠራ ከሆነ ውጤታ መሆን ያስችላል”ሲሉ መክረዋል።
ድርጅቱ ወደ ፊት ከገቢዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያሉትን ነገሮች ሲጨርስ የማስፋፊያ ፈቃድ በማግኘት የሚሠራቸውን ሥራዎች በሰፊው ለመሥራት አቅዷል።
የከፍታን አገልግሎት በደንብ ለመከታተል እና ለመጠቀም በቴሌግራም ቻናል ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እና ጨረታዎችን ለመከታተል አቅደዋል። እንዲህም ፈቃዳቸውን ሲጨርሱ የkefta.2merkato.com አገልግሎት ለመጠቀም ወስነዋል።