መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / የልብስ ስፌት ሥራ – ቅድስት ሰለሞን ልብስ ስፌት

የልብስ ስፌት ሥራ – ቅድስት ሰለሞን ልብስ ስፌት

ቅድስት ሰለሞን ልብስ ስፌት የተመሰረተው 2005 ዓ.ም በወ/ት ቅድስት ሰለሞን ነው። ድርጅቱ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በመልካም የእድገት ሁኔታ ምርት በማምረት ሂደት ላይ እንደሚገኝ የድርጅቱ መሥራች አባል ወ/ት ቅድስት ሰለሞን አስረድታለች። የመስራቿ የልብስ ስፌት እውቀት እንዲሁም የሥራ ልምድ ተደምሮ ድርጅቱ ሲመሰረት ከነበረው አንድ ማሽን አሁን ላለው አምስት ማሽን እና አራት ሠራተኞች መድረስ ችሏል።

ወ/ት ቅድስት በራሷ ሥራውን የጀመረችበት ምክንያት ትሠራበት የነበረው ድርጅት ሲዘጋ ጀሞ አካባቢ የሱፐርቫይዘር ሥራ አግኝታ ቤተሰቦቿ ሩቅ እንዳትሄድ ብለው የልብስ መስፊያ ማሽን (overlock machine) ገዝተውላት ልትጀምር ችላለች። በተመሣሣይ ሁኔታ በአንድ ዘመዷ ቤት ውስጥ የሕጻን ልጅ መታቀፊያ በማየት ሥራውን እንዴት ልትሠራው እንደምትችል እናም ሱቆች ስንት እንደሚረከቡ በየቦታው መረከቢያ በማፈላለግ ረገድ በመርካቶና በሾላ እንዲሁም የተለያዩ ሱቆችንም መታቀፍያ እንደሚፈልጉ በመጠየቅ እና ጥናት በማድረግ ነው የተጀመረችው። “እግዚአብሔር ይመስገን እንደ ጀማሪ ሥራው ጥሩ ነበር” ስትል ወ/ት ቅድስት ተናግራለች።kids-clothing

ወ/ት ቅድስት የልብስ ስፌት ሙያ ዘርፍን የመረጠችበት ምክንያት ስትገልጽ በታዳጊ እድሜዋ ወደ ሙያው የመግባት እድል ስላገኘች በዐሥራ ሰባት አመቷ የልብስ ስፌት ሥራ መሥራት መጀመሯ ለልብስ ስፌት ሙያ ትልቅ ፍቅር አንዲኖራት እና ሥራውን ከልጅነቷ ጀምሮ መላመዷ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን አስተዋኦ እንዳለው ተናግራለች።

ቅድስት የልብስ ስፌት የሚያመርታቸው ምርቶች፦

kids-wedding-dress

  • የህፃናት አልባሳት አና  የቬሎ ሥራ – ከአንድ ዓመት እስከ አሥራ አራት አመት ላሉ
  • የጥበቃ አልባሳት፣
  • ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች የተለያዩ ዩኒፎርሞች
  • ቲሸርት
  • የባሕል አልባሳት
  • ማንኛውም ደንበኛ የሚፈልገውን የልብስ ስፌት ዲዛይን በጥራት እና በፍጥነት ይሰራል።

ምሥረታና  ዕድገት

ቅድስት ሰለሞን የልብስ ስፌት ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ሆኖታል።  በአንድ ኦቨርሎክ (overlock) እና በአንድ ሲንግል ማሽን (single machine) ከቤት የተጀመረ ሥራ አሁን አራት ሠራተኞችን እና አምስት ማሽኖች እንዲሁም ዐሥራ ሦስት የጅምላ ተረካቢዎችን ሊያፈራ ችሏል። እንዲሁም የተለያዩ ሥራዎችን አጠናቋል ለምሳሌ LH Security የጥበቃ የደንብ ልብስ ሥራ በሚገባ አጠናቆ አስረክቧል። ድርጅቱ ሲመሰረት የነበሩ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ነበሩ፤ ለምሳሌ ተረካቢ ደንበኛ አልነበረም፣ የማቴሪያል ዋጋ ከቦታ ቦታ መለያየት፣ ምርቱን እንደ ደንበኛ ፍላጎት በጥራት በማምረት ተገቢ ዋጋ ያለማግኘት፣ የማቴሪያል ዋጋ በየቀኑ መለዋወጥ፣ ዛሬ ባለው ዋጋ ሥራ ተረክቦ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ ለሥራው የታሰበው ዋጋ መጨመር፣ የመብራት መቆራረጥ እንዳንዴም እስከ አንድ ወር መብራት ያለ መኖር ሥራው ላይ ትልቅ ተፅኖ አለው። ሥራን በተገቢው ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ያደርጋል።

የነበሩትን ችግሮች በተረጋጋ ሁኔታ በማጤን እና መፍትኄ በመፈለግ ችግሩን ለመፍታት እንደተቻለ ወ/ት ቅድስት አስረድታለች። የገበያ እጥረት ችግርን ለመፍታት ራሳቸው በየሱቁ እየዞሩ ምርታቸውን በማስተዋወቅ ደንበኞችን ለማፍራት የሠሩት ሥራ እንደኛው መፍትሔ ነው። ሌላው የመብራት ችግር ጄኔሬተር በመከራየት ሥራው ቀጥሏል። “ችግሮች ብዙ ናቸው ግን ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግ መፍትሔ መፈልግ እና መቀጠል ነው።” ተስፋ አለመቁረጥ ስትል ወ/ት ቅድስት አስረድታለች። ለዚህ ለመድርስ ቤተሰቦቿ እቃ ከሟሟላት ጀምሮ እስከ ሥራ ቦታ ደረስ እየመጡ አብሮ በመሥራት እና በማምሸት ሥራ ሲበዛም እስከ ማደር ድረስ እየደረሱ እንደሚያግዟት ትናገራለች።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ቅድስት ሰለሞን የልብስ ስፌት ላይ ይህ የሚባል ተፅዕኖ አላሳደረም፤ እንደ አብዛኛው የልብስ ስፌት ኮቪድ ሲከስት ሥራ አላቋረጠም። እንደውም ተገቢውን ጥንቃቂ በማድረግ ድርጅቱ የፊት መሸፈኛ ጭንብል በብዛት በማምረት የኮቪድ ወረርሺኝን ለመከላከል የራሱን ማኅበራዊ ኃላፊነት በመወጣት ጠቀም ያለ ገቢ አግኝቷል፡፡ ከዚህም ጋር አያይይዛ ወ/ት ቅድስት “ችግር ብልሀትን ይፈጥራል እንደሚባልው” ሌሎችም ጀማሪ ቢዝነሶች ችግር ሲያጋጥም መፍትኄ መፈለግ እንዳለባቸው ገልጻለች።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት፣ ምክር

ቅድስት የልብስ ስፌት ድርጅት አሁን ባለው ሁኔታ ሁለት የማስታወቂያ መንገዶችን ይጠቀማል። ሰው በሰው (word of mouth) እየተነጋገረ እንዲሁም በቴሌግራም የራሱን ቻናል በመክፈት የሚያመርታቸው ምርቶች ያስተዋውቃል። ከዚሁ ተያይዞ ዐሥራ ሦስት በጅምላ የሚወስዱ ደንበኞችን አፍርቷል።

አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ በ’ከፍታ’ በኩል የሚሰጠውን የ2merkato የመረጃ አገልግሎት በቴሌግራም እየተጠቀሙ ነው፤ ወደፊት አስር ማሽን ሲደርሱ የ2merkato ጨረታ አገልግሎት ለመጠቀም አቅደዋል ።

አዲስ ቢዝነስ ለሚጀምሩ ሰዎች ስለሙያው የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው ቢጅምሩ ወይም ሥልጠና ወስደው ቢጀምሩ፣ እንዲሁም ደንበኛ ማክበር እና በምንም ነገር ተስፋ አለመቁረጥ፣ ትእግስት ማድረግ፣ ማስተዋል፣ ለሥራ ትጋት ማሳየት እናም ከሠራተኛ ጋር ያለው ግንኙነትም ጥሩ መሆን አለበት ስትል ወ/ት ቅድስት ትመክራለች። የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ደካማ እና ጠንካራ ጎንን ማወቅ በተጨማሪም የሂሳብ አያያዝ ዕውቀቱ ቢኖራቸው ጥሩ ነው።

ቴክኖሎጂ መጠቀም ጥሩ እንደሆነ ወ/ት ቅድስት ታስረዳለች። ኢንተርኔት አዳዲስ የልብስ ዲዛየኖችን ለማየት፣ የተለያዩ የልብስ አሠራር መንገዶችን ለመማር እንዲሁም ቴሌግራም በመጠቀም ምርትን ለማስተዋወቅ እና የተሻለ ገቢ ለማስገኘት ይጠቅማል።

ቅድስት ሰለሞን የልብስ ስፌት ዐሥር የሚደርሱ ቅርንጫፎችን የመክፈት እቅድ አለው። ከአምስት አመት በኋላ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ” ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ማሽኖች እንደሚኖሩት በስትራቴጂክ እቅድ አቅዶ እየሠራ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

ሀሌታው ሀ ኅትመት እና ማስታወቂያ

ድርጅት የተመሠረተው በአቶ ዮናታን ታደሰ እና ሦስት መሥራች አባላት በ2012 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የኅትመት …