መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / “ዓላማ፣ ትዕግሥት እና ጠንክሮ መሥራት እዚህ አድርሰውናል”

“ዓላማ፣ ትዕግሥት እና ጠንክሮ መሥራት እዚህ አድርሰውናል”

ኃይለገብርዔል፣ ፈረደ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት

ኃይለገብርዔል፣ ፈረደ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ኅብረት ሽርክና ማኅበር የተመሠረተው 1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነው – በ3,000 ብር ካፒታል። መሥራቾቹ፣ ድርጅቱ ሲመሠረት ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደነበሩ ይናገራሉ። በተለይ የመደራጀት ችግር፣ መነሻ ካፒታል ማጣት፣ ብድር አለማግኘት ፣ የመሥሪያ ቦታ አለመኖር ወዘተ። በወቅቱ 5,000 ብር እንኳን በብድር ለማግኘት ምን ያህል ፈተና እንደ ነበር ያስታውሳሉ። ይህንን ፈተና እንደ ምንም ተወጥተው ሥራ ከጀመሩ በኋላም፣ 1,500 ብር ያህል ክፍያ የሚገኝበት ሥራ ብርቅ ነበር ይላሉ።

   

ከ2000-2004 ዓ.ም የነበረው ጊዜም አስቸጋሪ ነበር። ከመሥራቾቹ አንዱ እና የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ የሆነው ኃይለገብርዔል ዋቅጂራ ከ2005 ዓ.ም ወዲህ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መጥተዋል ይላል። የካይዘን ሥልጠና ወሰዱ፤ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ጥሩ መስመር ያዙ። በአሁኑ ወቅት በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የማይመረቱ ምርቶችን ማምረትም ጀምረዋል። አሁን አጠቃላይ የእንጨት እና የብረታ ብረት ሥራዎች በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸውልናል።

ተለይተው ከሚታወቁባቸው ምርቶች መካከል የኬብል ድራም ምርት በዋናነት ይጠቀሳል። ከዚህ ቀደም አገር ውስጥ ይመረት ያልነበረ በመሆኑ እና እነርሱ ማምረት በመጀመራቸው፣ ይህም ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እንድታወጣ በማስቀረት  የራሳቸውን አስተዋጽዖ እያደረጉ እንደሆነ ኃይለገብርዔል ይናገራል። ለራሳቸውም ቢሆን ተጠቅመውበታል።

ድርጅቱን የመሠረቱት 10 አባላት ቢሆኑም፣ በአስቸጋሪዎቹ ዓመታት አራቱ ከማኅበሩ ወጥተው አሁን ስድስቱ ብቻ ቀርተዋል። ይሁን እንጂ እነዚያን ፈታኝ የሚሏቸውን ዓመታት ካለፉ ወዲህ ማኅበሩ አድጓል፤ ተመንድጓል። በ3,000 ብር ካፒታል ተነሥተው፣ አሁን ካፒታላቸው ከ18 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ይገመታል። የአባላቱን ኑሮ ለመደገፍ እንኳ የማይስተማምን ይመስል የነበረው ማኅበር አሁን ከ30 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሠራል። ሥራ ሲጀምሩ ምንም መሥሪያ ማሽን እንኳን አልነበራቸውም፤ አሁን የሚሠሩባቸው የራሳቸው ዘመናዊ ማሽኖች አሏቸው። ማኅበሩ ስድስት መኪኖች ያሉት ሲሆን፣ ከስድስቱ ሦስቱ “ፒክ አፕ” መኪኖች ልዩ ልዩ ሥራ በመሥራት ለማኅበሩ ተጨማሪ ገቢ የሚያመጡ ናቸው።

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ኃይለገብርዔል ዋቅጅራን እነዚያን ፈታኝ እና አስቸጋሪ ያሏቸውን ዓመታት እንዴት እንዳለፏቸው ጠይቀነው ነበር። ኃይለገብርዔል በቅድሚያ ያነሣው ማኅበሩ ትልቅ ራዕይ ይዞ መመሥረቱን ነው። ለዚህም ብዙ እንደደከሙ ይናገራል። “ምንም አይነት ሥራ ሲጀመር ቀላል የሚባል ነገር የለም። ብዙ አድካሚ ነገር አለ፤ ብዙ አሰልቺ ነገር አለ” ይላል። እነዚያ ጊዜያት የማይታለፉ የሚመስሉበት ወቅት ይኖራል። ሆኖም ጠንክሮ መሥራት እና ተስፋ አለመቁረጥ እዚህ አድርሶናል ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ለመሰል ማኅበራት ምን እንደሚመክር እና እንደሚመኝ ሲጠየቅ ኃይለገብርዔል እንዲህ ይላል፡- “እንዲህ በቡድን መሥራት ኢትዮጵያ ውስጥ አልተለመደም። ይህ መቀየር አለበት። [በቡድን መሥራትን] መልመድ እና መሥራት አስቸጋሪ ነው፤ ብዙ ማኅበራት እየፈረሱ ያሉት በዚህ ችግር ነው። ይህ ችግር እዚህ ማህበር ጋርም አጋጥሞ ነበር፤ ግን [አንዳችን ሌላችንን] በመታገስ፣ የግል ችግሮችን በመተው ተወጥተነዋል።” እንዲሁም “ከምንም በላይ ጠንካራ የሥራ ባሕል ራሱ ያልነበረ እና በሥራው ሒደት ውስጥ አለመግባባት የፈጠረ ቢሆንም በሂደት ቀስ በቀስ እየተቀረፈ ነው” ይላል። ስለዚህ አዲስ ኢንተርፕራይዞችም ቶሎ ተስፋ ባለመቁረጥ ሥራቸውን እንዲሠሩ ይመከራል።

በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ እንደተቀዛቀዘባቸው ይናገራሉ። ከዚህም ጋር አያይዘው ሁሉም ለደረሰበት ችግር የራሱን የፈጠራ መፍትሔ በመጠቀም ይህን አስከፊ ጊዜ ማለፍ ይቻላል በሚል ከጊዜው ጋር የሚሄድ የሥራ ፈጠራ አክለዋል። ኃይለገብርዔል እንደ እነርሱ በእንጨት እና ብረታብረት ዘርፍ ለተሰማሩ ለአብነት የእጅ ንክኪ የሌላቸው የእጅ መታጠቢያዎች መሥራትን ይጠቅሳል። ለምሳሌ ዘርፍ  ጨርቅ ዘርፍ ያሉ ማስክ ሊይመርቱ፣ ሌሎችም ሳኒታይዘር ሊያቀርቡ ይችላሉ ሲሉ ሐሳብ ይሰነዝራል። እነርሱም በድርጅታቸው በተራረፉ የእንጨት ግብዓቶች መልሰው በመስራት ለአገልግሎት እንዲውል አድርገዋል፤ ይህም ለሦስት ወር የሠራተኛ ደምወዝ እንደቻለላቸው እና ይህንን ጊዜ ለማለፍ እንደጠቀማቸው ያስረዳል።

ለማኅበሩ እዚህ መድረስ ወረዳው ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎላቸዋል። ለጨረታ ዋስትና በቀን ከ10-20 ደብዳቤ ይጽፉልናል ይላል – ኃይለገብርዔል፤ ይህ ደግሞ ከአስር እስከ ስድሳ ሺህ ብር እንደሚያድንላቸው ያስረዳሉ። እንዲሁም የመሥሪያ ቦታ እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በማግኘታቸው ደስተኛ ናቸው።

ማኅበሩ በከፍታ አገልግሎት ተጠቃሚ ነው። ዓመታዊ የደንበኝነት ክፍያ በመክፈል የጨረታ ማስታወቂያ እና የሥራቸውን ማስታወቂያ አገልግሎት ያገኛሉ። ማኅበሩ ጨረታ በብዛት እንደሚሳተፍ በመግለጽ፣ ጨረታ ለመፈለግ እና ለመምረጥ አንድ ሰው ይመድቡ እንደነበር ሥራ አስኪያጁ ይናገራል። በከፍታ አገልግሎት የቱመርካቶ (2merkato) የጨረታ ማስታወቂያዎችን ማግኘት ከጀመሩ ወዲህ ግን ያለ ሐሳብ በሚሠሩበት ዘርፍ የሚወጡ ጨረታዎች ተመርጠው ይደርሷቸዋል። በወር ከሃያ እስከ ሰላሣ ጨረታ ይሳተፋሉ፤ ሁለት ወይም ሦስት ያሸንፋሉ። ጨረታ ለማሸነፍም ቢሆን ሳይታክቱ፣ ሳይቆርጡ ደጋግሞ መሞከር ቁልፍ መሆኑን ይመሰክራሉ።

ኃይለገብርዔል፣ ፈረደ እና ጓደኞቻቸው ወደ ፊት በፋብሪካ ደረጃ ከፍተኛ አምራች የመሆን ሐሳቡ አላቸው፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ግባቸውን ማሳካታቸው እንደማይቀርም በቁርጠኝነት ይናገራሉ።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …