አንድን ቢዝነስ ስኬታማ በሆነ መልኩ ማስተዳደርና መምራት ከፍተኛ ኃላፊነት ነው። በተለይ በቂ ልምድ ከማዳበራችን በፊት ያሉት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት፣ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥሩብንና ውጥረት ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ።
ይህንን ጫናና ውጥረት ለመቀነስና ቢዝነሳችንን በተሳካ መልኩ ለማስኬድ፣ የወጪ ገቢውን ፍሰት የተስተካከለ ለማደረግ፣ የቢዝነስ አስተዳደር ባለሙያዎችና ቢዝነሶችን በመምራት ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች የሚስማሙባቸው አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦች አሉ። እነዚህን ነጥቦች ማጤን ከብዙ ስህተት ሊያድንና ከአላስፈላጊ ጭንቀት ሊገላግል ይችላል።
በመቀጠል፣ ለተሳካ የቢዝነስ አስተዳደር ይጠቅማሉ የሚባሉ ነጥቦችን እናያለን።
1. የግልና የቢዝነስ ገቢና ወጪን መለየት
የቢዝነስ ባለቤቶች/አስተዳዳሪዎች፣ ቢዝነሱ የራሱ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም እንደሆነ ሁሌም ማስታወስ ያስፈልጋቸዋል። የራስን (የግል) ገቢና ወጪ ከቢዝነስ ገቢና ወጪ ጋር መደባለቅ ለቢዝነስ ዕድገትና ስኬት ትልቅ እንቅፋት ነው።
ምንም እንኳ አንዳንዴ ፈታኝ ቢመስልም፣ የቢዝነስንና የግል ኑሮን ገቢና ወጪ እንዳንደባልቅ በእጅጉ መጠንቀቅ አለብን።
2. ሠራተኞችን ስለሥራቸው ኃላፊነት በሚገባ ማሳወቅ
አንዳንዴ ሠራተኞቻችን ሥራቸውን “በራሳቸው” እንዲያውቁ እንጠብቃለን። ይህ በራሱ ክፋት ባይኖረውም፣ ከእያንዳንዱ ሠራተኛ (የቢዝነሱ ባለቤቶች/አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ) ምን እንደሚጠበቅ ግልፅ የሆነ ግንዛቤ መኖር አለበት። ሠራተኛው ስላለው ኃላፊነትና ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያለው ግንዛቤ አሻሚ ከሆነ፣ ሥራውን በመሰጠት እና በውጤታማነት ለማከናወን ያለው ተነሳሽነት በእጅጉ ይቀንሳል።
ማንኛውም በቢዝነሱ ውስጥ ያለው ሰው “መቼም ይሄን ያውቀዋል” ብለን የምንተወው ነገር መኖር የለበትም። ምናልባት እኛ ከራሳችን አንፃር በጣም ግልጽ የመሰለን ነገር ለሌላው ሰው እንዲያ ላይሆን ይችላል። ስለዚህም ከእያንዳንዱ ሰው ስለሚጠበቀው ነገር ጥርት ያለ ግንዛቤ መፍጠራችን ላይ እርግጠኛ መሆን አለብን።
3. ሽያጭን ለማሳደግ የገበያ/ማስተዋወቂያ ሥራን ትኩረት መስጠት
የቱንም ያህል ግሩም ድንቅ የተሰኘ ምርት ወይም አገልግሎት ቢኖረን፣ ዒላማ ያደረግናቸው ደንበኞች ካላወቁልን ድካማችን ከንቱ ነው። ስለዚህም ገና ከመነሻው ሽያጫችንን እንዴት እንደምንፈጽምና ገበያ እንደምናሰፋ ትኩረት ሰጥተን ማስተዋል ይኖርብናል።
ሽያጭ እና ገበያ ጥናት የሚለው ገፅ በዝርዝር ይህንን ጉዳይ ይዳስሳል።
4. “ከራስ” እና ከሠራተኞች ጋር ያለማቋረጥ መወያየት
በየጊዜው ነገሮች እንዳሰብናቸው መሆናቸውን መከለስ፣ ምናልባት መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማየት እንዲሁም አንዳንድ ነገሮችን ልናሻሽል የምንችልባቸው መንገዶች ካሉ እነሱን ለመዳሰስ ራሳችን ከራሳችን ጋር (ጥሞና በመውሰድ) እንዲሁም ከሠራተኞቻችን ጋር በተናጠልም ሆነ በጋራ በየጊዜው ውይይት ማድረግ ወሳኝ ነው።
እነዚህ ውይይቶች ብዙ ጊዜ ስብሰባ ተብሎ ረጅም ሰዓት እንደሚወሰደው ይሁኑ ማለት ሳይሆን፣ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተግባራዊ የሆኑ ነጥቦችን በማንሳት የሚደረጉ መሆን አለባቸው።
5. ግብርን በጊዜው መክፈል
አብዛኛዎቹ ቢዝነሶች የግብር/ታክስን ጉዳይ አስገዳጅ ቀነ ገደብ እስኪደርስ ድረስ ችላ የማለት ስህተትን ይፈጽማሉ። ይህ አላስፈላጊ ውጥረትን ከመፍጠሩም በላይ፣ በየጊዜው የሚከፈል ግብርን ወስኖ አለማቆየት የገንዘብ ጫናም ጭምር ይፈጥራል።
ግብርን በጊዜው መክፈል፣ እንደውም ቀደም ብሎ ለግብር የሚከፈልግ ገንዘብ መድቦ ማስቀመጥ ከውጥረት ይገላግላል።
6. ትኩረት የሚከፋፍሉ ሥራዎችን መገደብ
ለምንሠራቸው ሥራዎች ቅደም ተከተል መስጠት ይኖርብናል። አስፈላጊ ያልሆኑ ግን ጊዜና ትኩረታችንን የሚሰርቁ ሥራዎችን በቁርጠኝነት መተውና ዋና ሥራችን ላይ ማተኮር ያስፈልጋል።
አንድ ተግባር በራሱ “ጥሩ” ስለሆነ ብቻ ጊዜያችንን መውሰድ የለበትም። ከሌሎች ዋና ዋና ተግባሮቻችን አንፃር አነፃፅረነው እነርሱን የሚሻማ ከሆነ፣ እርሱን ትተን ትኩረታችንን መሰብሰብ ግዴታችን ነው።
7. ላልተጠበቁ ነገሮች ጊዜ መመደብ
ከጊዜያችን 20 በመቶ የሚሆነውን ከዕለት ተዕለት ሥራዎች ነፃ ማድረግና ላልተጠበቁ ነገሮች መቆጠብ ጥሩ ነው። ይህ ማለት፣ በቀን ስምንት ሰዓት በሥራ ላይ የምናሳልፍ ቢሆን አንድ ሰዓት ተኩል ያህሉ ማለት ነው።
ይህንን ጊዜ ያልተጠበቁ ነገሮች ካልተከሰቱ ቢዝነሳችንን ስለማሳደግና ማስፋት አማራጮችን በማየት ልናሳልፈው እንችላለን።
8. ራስን ያለማቋረጥ ማሳደግ
አንዳንድ ዕውቀት ወይም ክህሎት ገና የግድ ሳይሆንብን አስቀድመን ማወቅና ማዳበር ያስፈልጋል። ራሳችንን ለማሳደግ አስቀድመን ጊዜ መመደብ ከስህተት፣ ከራስ መተማመን ጉድለት እንዲሁም ተያይዞ ከሚመጣ ራስ ምታት ያድነናል።
እነዚህን ነጥቦች ማስተዋሉ ለቢዝነስ አስተዳደር ውጤታማነት ወሳኝ ነው። ይሁን እንጂ፣ የእነዚህ ሁሉ ጠቅላይ የሆነውን ምክር መርሳት የለብንም። ይህም ነገሮችን ሁሉ በአንድ ጊዜ ለማድረግ መሞከርና በጭንቀት ማጥ ውስጥ መዘፈቅን ማስወገድ ነው። ሥራችንን አንድ በአንድ፣ ደረጃ በደረጃ መሥራት ለዚህ መፍትሔ ነው።