መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ብርክቲ፣ ነጃት እና ጓደኞቻቸው ሻማ ማምረት ሥራ

ብርክቲ፣ ነጃት እና ጓደኞቻቸው ሻማ ማምረት ሥራ

ብርክቲ፣ ነጃት እና ጓደኞቻቸው ሻማ ማምረት ሥራ የተመሠረተው በ ወ/ሮ ነዲያ ሰኢድ መሐመድ እና በሁለት ጓደኞቻቸው በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ የተለያዩ የሻማ ዐይነቶችን የሚያመርት ድርጅት ነው።

ድርጅቱ ከሚያመርታቻው የሻማ ምርቶች መካከል፦

  • የልደት ሻማዎች
  • ለሰርግ፣ ለጋብቻ እና ቫላንታይን እና ተመሳሳይ አገልግሎት የሚውሉ ሻማዎች
  • የተለያየ ቀለም እና መአዛ ያላቸውን ሻማዎች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ ነዲያ ወደ ሻማ ማምረት ሥራ ከመግባታቸው በፊት በዱባይ ሰባት ዓመት ሠርተዋል። ከዱባይ ከተመለሱ በኋላ ግሪንላንድ የሚባል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ለስድስት ወር ሠርተዋል። በዚህ ሥራ እያሉ የአዲስ ዕይታን ማስታወቂያ በሬዲዮ ይሰሙና እና ከአንድ ጓደኛቸው ጋር በመነጋገር ቦታው ጋ ሜክሲኮ ይሄዳሉ። ያለውን ነገር ከተገነዘቡ በኋላ ሥራቸውን በማቆም የአንድ ሳምንት የሻማ አመራረት ሥልጠና ወስደው በመቀጠል አንድ የጭቃ ቤት ገርጂ አካባቢ በሦስት ሺህ ብር ተከራይተው፣ በሃያ ሰባት ሺህ ብር የሻማ ማሽኝ ገዝተው፣ ኬሚካል ደግሞ ሃያ አምስት ኪሎ ኬሚካል እና ክር በአጠቃላይ በሃምሳ ሺህ ብር ካፒታል ማሽን ድርጅቱን መሥርተዋል።

ድርጅቱ በኪራይ ለተወሰነ ጊዜ ከሠራ በኋላ ቢደራጁ የተሻለ ቦታም ከመንግሥት በቅናሽ ማግኘት እንደሚችሉ ስለተነገራቸው እንሞክረው ብለው ወደ ወረዳ ሄዱ። ለስድስት ወር ከተመላለሱ በኋላ አሥራ ሁለት ካሬ ቦታ ገርጂ ወረዳ 13 ሼድ ላይ ቦታ ተሰጣቸው። የድርጅቱ መሥራች የወሰዱት የሻማ ሥልጠና ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ሥልጠናው ሲኦሲ የለውም። ስለዚህ በደንብ የመማር ዕድሉ ትንሽ ነው በተለይ ደግሞ የተማሪው ፍላጎት ከሌለ። እነ ነዲያም ብዙ ሥራ ኢንተርኔት ላይ በማየት ራሳቸውን በማሳደግ ለማብቃት ችለዋል።

ድርጅቱ ሁለት የሻማ ምርቶችን በዋናነት የሚያመርት ሲሆን አንዱ የተለመደው የሻማ ዐይነት ሲሆን፣ አንዱን ሻማ (በፍሬ) በዐሥር ብር ከሃምሳ ሳንቲም (10 ብር ከ50 ሳንቲም) ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ሻማዎችን በግራም በመለካት አንድ ግራም በዐሥር ብር በማስላት ደንበኛው የሚፈልገውን ሻማ ያመርታሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሽታ ያላቸው ሻማዎችንም ያመርታል ይህን ሻማ ግን የሚያመርተው በቫላንታይን ጊዜ እና ፈላጊ ደንበኛ ሲመጣ ነው። ዐሥር ካርቶን የተለመደውን የሻማ አይነት እና ከዛ በላይ ለሚያዙ ደንበኞች በአንድ ካርቶን የዐምስት ብር ቅናሽ ያደጋል። ድርጅቱ ምርቱን ለባለሱቆችም ለቀጥታ ተጠቃሚም በ85 ብር እያቀረበ ይገኛል።

ድርጅቱ ከነበረው ሰላሳ ስድስት ሻማ የሚያወጣ ማሽን አሁን ትልቅ ማሽን በማስገባት በአንድ ጊዜ ሁለት መቶ ሻማ የሚያወጣ ማሽን ከሰው ላይ በመግዛት ምርት የማምረት አቅሙን በዐምስት አጥፍ ማሳደግ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ለአራት ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ነው።

የድርጅቱ መሥራች በሻማ ሥራ ላይ ያለው ትልቁ ችግር የግብዓት ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ። ምክንያቱም ጥሬ እቃ የሚገባው ከግብፅ፣ ቻይና እና ኢራን ነው። የጥራት ደረጃቸው ደግሞ የግብፅ አንደኛ ሲሆን ቀጥሎ የቻይና ነው መጨረሻ የኢራን ነው። ይህ አንዱ ችግር ሲሆን ሌላው ችግር ደግሞ ባለው የጸጥታ ችግር ከአዲስ አበባ ውጪ እንደልብ መንቀሳቀስ አይቻልም። ከዚህ በፊት ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ውጭ በክልል ከተሞች ብዙ መጠን ያላቸው ሥራዎችን መሥራት ችሏል። አሁን ግን ያለው ችግር በጣም ከባድ አድርጎታል፤ ሥራም በጣም ቀንሷል።

ድርጅቱ ምርቱን ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ያስተዋውቃል። በተጨማሪ ደግሞ ከሰዎች ጋር ቢዝነስ ካርድ በመለዋወጥ በሚፈጠር ግንኙነት አብረው ሥራዎችን ይሠራሉ። በተጨሪ ደግሞ የአዲስ አበባ ሴቶች ነጋዴ ማኅበር እነሱ ሊሳተፉባቸው የሚችሉ ባዛሮች ሲኖሩ ደብዳቤ በመጻፍ ደብዳቤውን በማቅረብ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አሁን 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት  በመጠቀም በከፍታ ፓኬጅ 2merkato.com ላይ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፤ ዋናው የነበረው ችግር የመርካቶ ሥራ ሙሉ በሙሉ ቆሞ ነበር። ሌላው ደግሞ ሥራውን ወ/ሮ ናዲያ ብቻ ነበሩ ይሠሩ የነበረው፤ ሌሎቹ ቤታቸው ከሥራ ቦታው ይርቅ ስለነበር አይመጡም። እሳቸው ብቻ የመኖሪያ አድራሻቸው ቅርብ ስለነበር ይሠሩ ነበር። ሥራው በእንኝህ ምክንያቶች ቀንሶ የነበረ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ አልቆመም ነበር። የሱቅ ትዕዛዝ ብቻ በመቀበል እና ምርት በማቅረብ ነው የኮቪድን ጊዜ ያሳለፉት።

አሁንም ከኮቪድ በኋላ የገበያው ፍላጎት ያመጣው ተፅዕኖ አለ። በፊት ድርጅቱ ሻማውን በማምረት ቀጥታ በላስቲክ ነበር የሚያከፋፍለው። አሁን ግን የማሸጊያ ካርቶን ግዴታ ነው። ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም በፊት፤ የሌለ ወጪ አሁን ተጨምሯል። አንድ የማሸጊያ ካርቶን አሁን ስድስት ብር ነው። ለአንድ ፓኮ ይህ ደግሞ ብዙ ወጪ ነው።

ምክር እና ዕቅድ

ድርጅቱ ለወደፊት አሁን በጊዜ እና በደንበኛ ትዕዛዝ የሚሠራቸውን ሻማዎች ሁልጊዜ ዘወትር ለማምረት እቅድ አለው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ድርጅቱ የተሰጣቸው ሼድ ላይ ብዙ ሠራተኞችን በመቅጠር አቅሙን አሳድጎ፣ ከአምስት ዓመት በኋል ጊዜው ሲደርስ በሰፊው የራሱን ቦታ በማዘጋጀት የመሥራት እቅድ አለው።

“አዲስ የግል ሥራ ለሚጀምሩ ምክር፦ በግል ሥራ ብዙ መሥራት ይቻላል አይሆንም ቢባል ራሱ ልሞክረው ብለው መሥራት ይችላሉ። የጊዜ ነጻነት አለው። ነገር ግን ሥራውን የሚወዱት እና በደንብ ፍቅር ያላቸው እና የማይሰለቻቸው ሰዎች ሥራውን መርጠው መግባት አለባቸው” ሲሉ የድርጅቱ መሥራች ይመክራሉ።

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …