ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ሚካኤል ውድነህ እና በጓደኞቻቸው በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ የብረት እና የእንጨት ምርቶችን የሚያመርት ድርጅት ነው።
የሚያመርታቸው ምርቶች
- ቁም ሳጥን
- አልጋ
- ሶፋ
- የቴሌቪዥን ማስቀመጫ
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ድርጅቱ በዋናነት የሚሠራው የእንጨት ሥራ ሲሆን ምርቶቹንም በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ እንደ አዳማ፣ ባሕር ዳር ውስጥ ለሚገኙ የፈርኒቸር ቤቶች ያስረክባል። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ኮንዶሚኒየሞች ላይ የእንጨት ሥራዎች ሠርቷል፤ ለአብነትም ቦሌ ቡልቡላ 40/60 ኮንዶሚኒየምን መጥቀስ ይቻላል።
አቶ ሚካኤል ከእንጨት ሥራ ጋር የተዋወቁት ገና በዐሥራ ሦስት ዓመታቸው ነበር። በወቅቱ ትምህርታቸውን እየተማሩ ጎን ለጎን የእንጨት ሥራ በመሥራት ቆዩ። ከዚያም በኋላ በእድሜአቸው ሲያድጉ፣ ተደራጅቶ መሥራት የሚቻልበት አጋጣሚ ሲፈጠርና ሁኔታዎች ሲመቻቹ ከአራት መሥራች አባላት ጋር በመሆን ድርጅቱን መሠረቱ። ይሁንና አንድ መሥራች አባል ድርጅቱ እንደተመሠረተ የወጣ ሲሆን የተቀሩት አባላት አሉ፤ ነገር ግን የድርጅቱን ሥራ ማስኬድ ሥራ እየሠሩ የሚገኙት አቶ ሚካኤል ናቸው።
የድርጅቱ መሥራች ከመንግሥት ለሥራ የተሰጣቸው ቦታ (ሼድ) አካባቢ ሌላ የመሥሪያ ሼድ ባለመኖሩ በዕጣ የደረሳቸውን የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤት በመሸጥ ለድርጅቱ ማስፋፊያ ተጠቅመውበታል። በዚህም የድርጅቱ አቅም በማደጉ በውስጡ ለሃያ ስምንት ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። የመሥርያ ቦታው (ወርክሾፑ) በውስጡ የሠራተኞች አልጋ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አካቶ የያዘ ነው፤ ይህም ለድርጅቱ እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገ የድርጅቱ መሥራች ተናግረዋል። ድርጅቱ የነበረው መነሻ ካፒታል ብር 4,000 (አራት ሺሕ ብር) የነበረ ሲሆን አሁን አድጎ ብር 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን ብር) መድረስ ችሏል።
ድርጅቱ በሳምንት ቢያንስ ስልሳ ነጠላ ዕቃዎችን የሚያወጣ ሲሆን ይሄም እንደ ጠረጴዛ፣ ቲቪ ማስቀመጫ የመሳሰሉ ዕቃዎችን ያካትታል። ድርጅቱ የሚሠራቸውን ሥራዎች በራሱ ፈጠራ እና ውጪ ሃገር የሚገኙ የተለያዩ ዲዛይኖችን ኮፒ በማድረግ ይሠራል። ከነዚህ ዕቃዎች በተጨማሪ ለተለያዩ አፓርታማዎች በቅብ እና በላምኔት የተለያዩ የብረት እና የእንጨት ውጤቶችን በመሥራት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። አሁን ደግሞ በቅርቡ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት እየተጠቀመ ሲሆን በዚህም ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ የበለጠ ብዙ ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድ አለው።
ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው አንድ በራሱ ዕቅድ የሚያመርታቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በነጋዴዎች ፍላጎት የሚመጡ ትዕዛዞችን በመረከብ ይሠራል። በዚህም ሥራ በሳምንት ሦስት አይሱዙ ጭነት ሙሉ ዕቃዎችን አምርቶ እያስረከበ ይገኛል። ይህንንም ተዓማኒነት ለማግኘት የሃያ ዓመት የሥራ ልምድ ትልቁን ሚና እንደሚጫወት የድርጅቱ መሥራች ተናግረዋል። ድርጅቱ ዘጠና የሚጠጉ ነጋዴ ደንበኞች አሉት።
ስለድርጅቱ የሥራ ባሕል መሥራቹ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል “ሁሉም አብረው እኩል ይሠራሉ፤ አመጋገብም ላይ አብረው ይበላሉ ይጠጣሉ፤ ሥራ በጣም ከበዛ ደግሞ ምግብ ይመጣና ተከፋፍሎ እዛው አንድ ላይ በልተው ወደ ሥራ ይገባሉ። ቀለም የሚቀባው ቀቢ ሠራተኛ ቢቀር ሌላው የቀረውን ሥራ ተክቶ ይቀባል እንጂ ይህ እገሌ ነው የሚሠራው የሚል ነገር የለም።”ሥራ ተተካክቶ የመሥራት ባሕል በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረዋል የድርጅቱ መሥራች። አቶ ሚካኤል ከኮቪድ በኋላ ባለው ዐጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ለውጥ አለ ብለዋል ።
የኮቪድ ተፅዕኖ
በኮቪድ ጊዜ ድርጅቱ ሥራ አቁሞ ነበር፤ ይህም ወረርሽኙ እንደተከሰተ የነበረው ፍርሃት ከፍተኛ በመሆኑ ሥራ በጣም የለም እስከሚባል ደረጃ ቀንሶ ነበር። ይህንንም ለመቋቋም ትእዛዝ ተቀብሎ እየሠራቸው የነበሩትን ሥራዎች ካጠናቀቀ በኋላ ተዘግቶ ነው ያሳለፈው።
ምክር እና ዕቅድ
ድርጅቱ አሁን ያለበትን የቦታ ችግር በመቅረፍ የሠራተኞቹን ቁጥር በእጥፍ በመጨመር የመሥራት ዕቅድ አለው።
ድርጅቱ ባለው ተሞክሮ ከአጋጠሙት ችግሮች ውስጥ አንዱና ፈታኙ የነበረው የሚከተለው ነበር፦ ድርጅቱ ተመሥርቶ በነበረበት ወቅት ይሠራ የነበረው ሥራ የሸራተን ወንበር የሚባለውን ወንበር በማምረት ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ ሆቴሎች እና ድርጅቶች ማቅረብ ሲሆን፣ ይህ ሥራ እንደሚያዋጣ የተመለከቱ ባለሀብቶች ዘመናዊ እና ትላልቅ ማሽኖችን በመያዝ እና ብረቱንም በጣም በርካሽ ዋጋ በማምጣት በርካሽ ዋጋ በማምረትና በመሸጥ ሙሉ በሙሉ ገበያውን ተቆጣጠሩት። በዚህ ወቅት አቶ ሚካኤል ወደ እንጨት ሥራ ለመግባት ተገደዱ። ይህም ሥራው ብዙ ካፒታል ስለማይጠይቅ እና በቀላሉ መሥራት ስለሚቻል የእንጨት ሥራ በስፋት መሥራት ጀመሩ። ተፎካካሪ የበዛበትን ሥራቸውን መቀየራቸውና የእንጨት ሥራ ላይ ማተኮራቸው አሁን ላሉበት የእድገት ደረጃ እንዳደረሳቸው ተናገረዋል።
አዲስ ሰዎች ሊኖራቸው ሰለሚገባ የሥራ ሥነ ስርዓት ሲናገሩ ሥራ መዘግየት የለበትም በተቻለ መጠን መሥራትና በተባለው ጊዜ ማድረስ አለባቸው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ።