አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም አክሲዮን ማኅበር በአዋጅ ቁጥር 40/1988 ዓ.ም. መሠረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት በስድስት የአክሲዮን ባለቤቶች የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ለመስጠት እ.አ.አ ጥር 27 ቀን፣ 2000 ዓ.ም. በከተማው ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍና ድህነትን ለመቀነስ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ተቋም ነው። በአሁን ሰዓት በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 626/2009 እየሠራ የሚገኝ እና የአክሲዮን ባለቤቶች አስራ አንድ የደረሱ ሲሆን 10 የአካባቢ ጽሕፈት ቤቶች ከፍቶ በሚሠራባቸው ከተሞች 21 ዲስትሪክት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በመክፈት አገልግሎቱን በስፋት በመስጠት የበኩሉን አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ ይገኛል።

አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም፦ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና ዓላማ

ራዕይ

እ.አ.አ በ 2024 በኢትዮጵያ ተመራጭና ሞዴል የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋም መሆን።

ተልዕኮ

በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ሆነው የመሥራት አቅም ላላቸው በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በገቢ ማስገኛ የሥራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ለሴቶችና ወጣቶች ትኩረት በመስጠት ብቃት ባለው ሰራተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ አገልግሎት በከተማና በገጠር በመስጠት የተቋሙን ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው።

ዓላማ

በአዋጅ ቁጥር 626/2001 አንቀጽ 3/1/ መሰረት ገንዘብ መሰብሰብ፣ በገጠር፣ በከተማ፣ በግብርና፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ መስኮች እንዲሁም በሌሎች መሰል ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ጣሪያው በብሔራዊ ባንክ የሚወሰን ብድር መስጠት ይሆናል።

ዝርዝር ዓላማ

    • ለጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት።
    • ለኅብረተ ሰቡ ዘላቂነቱ የተረጋገጠና አስተማማኝ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት በስፋትና በጥራት መስጠት።
    • የኅብረተ ሰቡ የቁጠባ እና የፋይናንስ አጠቃቀም ባህል እንዲጎለብት ማስተማርና መምከር።
    • ኅብረተ ሰቡበተለይም ወጣቱ በራስ የሚተማመን የራሱን የሥራ ዕድል የመፍጠር ልምድ እንዲያዳብር ማበረታታት።
    • ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በኢኮኖሚ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ድጋፍ ማድረግ።
    • ልዩ ድጋፍ የሚያስፍልጋቸው የኅብረተ ሰብ አካላትን ማሳተፍ።
    • የተቋሙ የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ማከናወን።

አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም፦ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለመጠየቅ ምን ምን ማሟላት ያስፈልጋቸዋል?

  • ሕጋዊ ሰውነት ማግኘት
  • ዋና ምዝገባ፣ የንግድ ፈቃድ፣ በንግድ ሕጉ ሥር ከተዘረዘሩት ዘርፎች በአንዱ መመዝገብ፣ እንዲሁም በጋራ ለተቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች የመመስረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ማቅረብ
  • የንግድ ዕቅድ ማቅረብ
  • የሃብት መግለጫ (financial statement) ማቅረብ
  • የታደሰ የኢንተርፕራይዞች የዕድገት ደረጃ
  • የመሥሪያ ቦታ ከመንግሥት፣ በኪራይ ወይም በግል ከሆነ የሚገልጽ ማስረጃ
  • ብድር መጠየቂያ (proposal)
  • ኢንተርፕራይዙ ቀደም ሲል ብድር ከወሰደ የአከፋፈል ስርዓቱ ጥሩ መሆን አለበት
  • ከብድር ነጻ መሆኑን የሚገልጽ የማረጋገጫ ደብዳቤ ከወረዳ ማምጣት

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የሚሰጣቸው አገልግሎቶች

  1. የቁጠባ አገልግሎት
  2. የብድር አገልግሎት
  3. የአነስተኛ መድህን አገልግሎት
  4. የሦስተኛ ወገን ገንዘብ ማስተዳደር አገልግሎት
  5. የምክር አገልግሎት
  6. የሞባይልና ወኪል ባንኪንግ አገልግሎት
  7. የሀገር ውስጥ የሃዋላ አገልግሎት
  • የግዴታ ቁጠባ (compulsory saving)
  • የፈቃደኝነት ቁጠባ (voluntary saving)
  • ቅድመ ብድር ቁጠባ
  • ከብድር ተመላሽ ጋር የሚቆጠብ ወርሃዊ ቁጠባ
  • የብድር ኢንሹራንስ ቁጠባ
  1. ቅድመ ብድር ቁጠባ
    • ለግል ቢዝነስ፣ ለቤትና ለተሽከርካሪ ግዥ፣ ለግል ጉዳይ ማስፈጸሚያ ብድር፣ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅብር ቅድመ ብድር ቁጠባ ፣ የኢንተርፕራይዞች ቅድመ ብድር ቁጠባ ፣ ኢንተርፕርነር ሴቶች ልማት ብድር /WEDP/፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ቅድመ ብድር ቁጠባ፤ ኢንተርፕርነር ወጣቶች ብድር ቅድመ ብድር ቁጠባ ሲሆን ቁጠባውም ከ5-30 በመቶ ይሆናል።
  2. ከብድር ተመላሽ ጋር የሚቆጠብ ቁጠባ
    • የብድር ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞች ለቅድመ ብድር ከሚቆጥቡት በተጨማሪ በተቋሙ በሚኖራቸው ክፍያ ቆይታ ከብድር ተመላሻቸው ጋር በመደበኛነት የግዴታ ቁጠባ በወሰዱት ብድር 0.2 በመቶ መቆጠብ አለባቸው።
  3. የፈቃደኝነት ቁጠባ
    • ይህ ቁጠባ ተበዳሪዎች ተበዳሪ ያልሆኑ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች በፈቃደኝነት የሚቆጥቡት ቁጠባ ነው። እነሱም የደብተር ቁጠባ፣ የጊዜ ገደብ፣ የሳጥን፣ የልጆች፣ የተማሪዎች፣ የኢንተርፕራይዞች፣ የሞባይል ገንዘብ፣ የጉብኝት፣ ወለድ አልባ፣ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ፣ የመጦሪያ፣ የሴቶች ቁጠባ ናቸው። ቆጣቢዎች በጊዜ ገደብ ከሚቆጥቡት የቁጠባ አይነት በስተቀር በፈለጉ ጊዜ ማውጣትና ማስገባት ይችላሉ።
  4. በቁጠባ ላይ የሚሰላ ወለድ
    • ለማንኛውም የግዴታ ቁጠባ 7% አመታዊ ወለድ ምጣኔ ይከፍላል። ለፈቃደኝነት ቁጠባ የሚከፈለው የወለድ ምጣኔ ዝቅተኛው 8% (ስምንት በመቶ) ሆኖ እንደገንዘቡ መጠን እና የቆይታው ጊዜ እስከ 12% (ዐሥራ ሁለት በመቶ) የሚታሰብ ይሆናል።
    ተቋሙ የሚሰጣቸው የብድር አገልግሎቶች
  1. የቡድን ብድር
  2. የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ብድር
  3. የጥቃቅን ብድር እና የአነስተኛ ብድር
  4. የመካከለኛ ብድር እና SME ፋይናንስ ፕሮጀክት ብድር
  5. የቢዝነስ ብድር፦ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ብድር
  6. የግል ጉዳይ ብድር
  7. የመንግስት ሠራተኞች እና የሌሎች የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ብድር
  8. የተሽከርካሪ ግዥ ብድር
  9. የቤት ብድር
  10. የቤት ግዢ፣ ግንባታና እድሳት ብድር
  11. የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ብድር
  12. የኅብረት ሥራ ማኅበርና ዕድር ብድር
  13. ኢንተርፕረነር ሴቶች ብድር (WEDP)
  14. ኢንተርፕርነር ወጣቶች ብድር (YEDL)
  15. ወለድ አልባ ብድር
  16. ልዩ ፈንድ ብድር
  • ቅርንጫፉ በሚሠራበት አካባቢ የተሰጠ የታደሰ የነዋሪነት መታወቂያ
  • የነዋሪነት ማረጋገጫ ደብዳቤ
  • ከዕዳ እና ከብድር ነጻ ስለመሆኑ ማረጋገጫ
  • የጋብቻ ሁኔታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት
  • እድሜው ከ18 ያላነሰ እና ከ60 ያልበለጠ
  • በቡድን ብድር የሚጠይቁ ከሆነ፣ የቡድኑ አባላት ቁጥር ከአምስት እስከ ሰባት የሆነ፤ ተቋሙ ጽሕፈት ቤት ከፍቶ በሚሠራበት አካባቢ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ ያላቸው (በራሳቸው ቤት ወይም ከመንግሥት በተሰጣቸው ኪራይ ቤት ውስጥ ነዋሪ የሆኑ)
  • የተሰማሩበት ሥራ ሕጋዊ የሆነና ንግድ ፈቃድ ያለው። ሆኖም የቡድን ብድር፣ የቤት ብድር፣ የተሽከርካሪ ግዥ ብድርና የግል ጉዳይ ብድር ንግድ ፈቃድ የማይጠየቅባቸው የብድር ዓይነቶች ናቸው
  • በጥቃቅን አነስተኛ የተደራጁ ከሆነ ይህኑኑ የሚገልፅ ማስረጃ
  • እንደየብድሩ ዓይነት ቅድመ ብድር ቁጠባ መቆጠብ፦ ከ5 እስከ 30 በመቶ መቆጠብ
  • ደንበኞች ለሚበደሩት ብድር ተመጣጣኝ ዋስትና ማቅረብ
  • የብድር ደንበኞች ከ6 ወር ወዲህ የተነሱት 2ጉርድ ፎቶ
  • አዋጭ የሆነ የሥራ ዕቅድ ሞልቶ ማቅረብ
  • ሕጋዊ የሆነ ቋሚ የሥራ ቦታ ያላቸው የባለቤትነት ማረጋገጫ ወይም በኪራይ የተያዘ ቤት ከሆነ የኪራይ ውል እስከ ብድር ውል ዘመን ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ፤ ሆኖም ነባር ደንበኞች 2 ወር የኪራይ ዘመን የቀረው
  • ጥቁር መዝገብ ውስጥ የሌሉ
  • የተቋሙን ደንቦች፣ መመሪያዎችና ፓሊሲዎች ተቀብለው ለመተግበር ዝግጁ የሆኑ።
  • መደበኛ ብድሮች የመክፈያ ጣሪያ የሚወሰነው ደንበኞች የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ወይም ንግዱ/ ቢዝነሱ የሚያስገባውን የገቢ ሁኔታ እንዲሁም የተበዳሪውን የመክፈል አቅም ታሳቢ ያደረገ ሆኖ ነው
  • የቡድን፣ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና የአጭር ጊዜ ቢዝነስ ብድር እስከ 1 ዓመት ድረስ
  • ሌሎች የኅብረት ሥራ ማህበራት እና የዕድሮች ብድር እስከ 2 ዓመት ድረስ
  • የግል ጉዳይ ፣ የኢንተርፕረነር ወጣቶች/YEDL/ ብድር እስከ 3 ዓመት ድረስ
  • የጥቃቅን፣ አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ቢዝነስ የተሽከርካሪ ግዥ፣ የሴቶች ሥራ ፈጠራ ልማት ፕሮግራም /WEDP/፣ SME ፈንድ ፕሮጀክት ብድር እስከ 5 ዓመት ድረስ
  • የቤት ብድር እስከ 10 ዓመት ድረስ ይሆናል።
  • የልዩ ፈንድ የብድር ዓይነቶች የብድር መመለሻ ጊዜ ከፈንዱ አቅራቢዎች ጋር በሚኖረው ስምምነት የሚወሰን ይሆናል።
  • ተቋሙ በሁሉም የብድር ዓይነቶች የአገልግሎት ክፍያ የሚጠይቅ ሲሆን ይህም ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ታሳቢ በማድረግ በሚሰጠው የብድር መጠን ላይ 2 በመቶ ከብድሩ ይቆርጣል።

የእፎይታ ጊዜ

  • አዲስ ሥራ ለሚጀምሩ ሥራውንና የገበያ ሁኔታ እስኪለማመድ እንደተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ የሚለያይ ሆኖ ከ2 ወር እስከ 6 ወር የሚሰጥ ጊዜ ነው። የእፎይታ ጊዜው ወለድ የሚታሰብበት ይሆናል። ሆኖም ለአጭር ጊዜ ብድርና ለነባር ቢዝነስ የእፎይታ ጊዜ የላቸውም።

የቡድን ዋስትና

የቡድን አባላት ለሚውስዱት ብድር በጋራ ያልተነጣጠለ የአንድነትና የነጠላ ኃላፊነት ያለበት አንዱ ለሁሉም ሁሉም ለአንዱ የዋስትና ኃላፊነት የሚወስዱበት የዋስትና ዓይነት ነው። ይህም ለቡድንና ለኢንተርፕራይዝ ብድር በቡድን ዋስትና የሚጠቀሙበት የዋስትና አማራጭ ነው።

የቡድን ዋስትና ቅድመ ሁኔታ

    • የቡድን አባላት ከ5 እስከ 7 ሆነው የሚተዋወቁ፣ በራሳቸው ተመራርጠው ቡድን የመሠረቱና የአንድነትና ያልተነጣጠለ ኃላፊነት ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆኑ
    • በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ፅ/ቤት የተደራጁ ከሆኑ እና ሌሎች የዋስትና አማራጮችን ማቅረብ የማይችሉ ከሆነ እንዲሁም ኢንተርፕራይዙ ለሚወስደው ብድር አባላቱ በቡድንም ሆነ በተናጠል ዋስትና ለመውሰድ ፍቃደኛ የሆኑ።

የንብረት ዋስትና

በንብረት ዋስትናነት የሚያዘው ቤትን፣ ተሽከርካሪን፣ ማሽንን፣ ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችንና ጌጣ ጌጦችን ያጠቃልላል።

የደመወዝተኛ ዋስትና

የደመወዝ ዋስትና ማለት ወርሃዊ ደመወዝ እያገኙ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ኩባኒያዎች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ በመንግሥታዊና በህዝባዊ ማኅበራት እና በተቋሙ ለዋስትና ብቁ ተብለው የተለዩ፤ በአክሲዮን ማኅበር፣ በሽርክና ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና የግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በሚያገኙት ደመወዝ ለብድር ጠያቂዎች ዋስ የሚሆኑበት ነው።
    • የጊዜ ገደብ ቁጠባ ዋስትና
    • የአለኝታ ገንዘብ (receivables) ዋስትና
    • የቤት እንስሳት ዋስትና
    • የትምህርትት ማስረጃ በቤተሰብ ጣምራ ዋስ
 
የተቋሙ የብድር ደንበኞች በብድር ዘመን በሚያጋጥማቸው የህይወትም ሆነ የንብረት አደጋ የተነሳ በቤተሰብና በዋሶቻቸው ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ስጋት ለመጋራት እና የተቋሙን ወጪ የሚገኘውን ገንዘብ ጥራት ለማስጠበቅ እንዲቻል ደንበኞች የመድህን ሽፋን የሚገዙበት አገልግሎት ነው። የህይወት ኢንሹራንስ (Credit Life Insurance) ይህ የመድህን አይነት ከተቋሙ ደንበኞች ከተቋሙ በግልና በቡድን የብድር አገልግሎት አግኝተው በመሥራት ላይ እያሉ በህይወታቸው ላይ ለሚያጋጥማቸው አደጋ የመድህን ሽፋን የሚያገኙበት አሠራር ሆኖ የብድሩን 1% በአረቦን መልክ በየዓመቱ እንዲከፍሉ ይደረጋል። የንግድ ኢንሹራንስ (Business Insurance) ይህ የመድህን ዓይነት የሚያገለግለው ከተቋሙ በሽርክና ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በኅብረት ስራ ማኅበር ወይም በሌላ አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና አግኝተው ብድር ወስደው የብድር ገንዘብ ለአንድ የሥራ ዘርፍ የሚውል ሆኖ ሲገኝ ፤በድርጅቱ ስም የተመዘቡ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች አስቀድሞ መዝግቦ በመያዝ በንብረቶቻቸው ላይ የሚደርሰን አደጋ የብድሩን 1% በአረቦን መልክ በየዓመቱ እንዲከፍሉ በማድረግ ያለባቸውን ቀሪ ዕዳ በኢንሹራንስ እንዲሸፈን የሚያስችል አሠራር ነው። የንብረት ኢንሹራንስ (Property Insurance) ይህ የመድህን አገልግሎት የሚያገለግለው ከተቋሙ በግል፣ ሽርክና ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በኅብረት ሥራ ማኅበር ወይም በሌላ ሕጋዊ አደረጃጀት መሠረት ለቤት ግዥ ግንባታና እድሳት ብድር የወሰዱ ደንበኞች ብድር ለተወሰደበት ቤት መድህን በቤቱ ላይ ለሚደርስ አደጋ አረቦን የብድሩን አንድ በመቶ እና ለብድር ደንበኛው ህይወት መድህን ሌላ አንድ በመቶ አረቦን በአጠቃላይ የወሰዱትን የብድር መጠን 2 በመቶ በአረቦን መልክ እንዲከፍሉ በማድረግ ያለባቸው ቀሪ እዳ በኢንሹራንስ እንዲሸፈን የሚያችል አሠራር ነው።
የተቋሙ አገልግሎት ለማግኘት የመጡ አዲስና ነባር ደንበኞች በተቋሙ አሠራር፣ ደንብና መመሪያዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ከብድር በፊት እና ከብድር በኋላ ስለ ንግድ እና ፋይናንስ መረጃ አያያዝ ድጋፍ እና ምክር ይሰጣል።
በሚያደርገው የውል ስምምነት መሠረት የሚፈጸም ይሆናል።
ኤም ብር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጥ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ነው። በአዲስ አበባ ውስጥ አገልግሎቱን የሚሠጠውም በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም አማካኝነነት ሲሆን አገልግሎቶቹም
  • ለጓደኛ ወይም ለዘመድ ገንዘብ ማስተላለፍ
  • በሞባይል የቁጠባ ሒሳብ መክፈት
  • ለገዙት እቃ ወይም አገልግሎት ክፍያ መፈፀም
  • የድርጅቶች ደመወዝ ክፍያ መፈጸም
  • ብድር መክፈል
  • የሃዋላ አገልግሎቶችን መስጠት ያካትታሉ።

አዲስ ብድርና ቁጠባ አድራሻ

ዋና መሥሪያ ቤት፦ ቴዎድሮስ አደባባይ ሀሮን ታወር ፊት ለፊት

    ስልክ ቁጥር፦ 011 1 57 27 20፣ 011 1 11 14 24

ተ.ቁጽ/ቤትየቢሮ ስልክ ቁጥርየሞባይል ስልክ (የቢሮ)
1አራዳ አካባቢ ጽ/ቤት011 81261280929 172169
2አዲስ ከተማ አካባቢ ጽ/ቤት0904 032701
3ልደታ አካባቢ ጽ/ቤት011 5579218
4ቂርቆስ አካባቢ ጽ/ቤት0929 172167
5የካ አካባቢ ጽ/ቤት0929 172165
6ቦሌ አካባቢ ጽ/ቤት011 84012490929 172168
7ጉለሌ አካባቢ ጽ/ቤት0953 968765
8ኮልፌ አካባቢ ጽ/ቤት011 8200941
9ንፋስ ስልክ አካባቢ ጽ/ቤት011 84012490929 172170
10አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ ጽ/ቤት0953 968763

ማስታወሻ፦ ይሄ መረጃ የተዘጋጀው አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአካል ሄዶ በመጠየቅ በተገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች በሚጠቅም መልኩ ተቀናብሮ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ.

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባገኘው ፈቃድ መሠረት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ …