መነሻ / የቢዝነስ ዜና / የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንትን የሚከለክለው ሕግ ሊነሣ ነው

የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንትን የሚከለክለው ሕግ ሊነሣ ነው

የሲሚንቶ እጥረትን ለማሻሻል እና እያደገ የመጣውን የሲሚንቶ ፍላጎት ለማሟላት በማሰብ፣ መንግሥት የአዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንቶችን የሚከለክለውን ሕግ ሊያነሣ መሆኑ ተገለጸ።

ይህንኑ የሚያስረግጥ ማሻሻያ ደንብ ረቂቅ ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቀረቦ ውይይት እንደተደረገበት ተነግሮኛል ሲል አዲስ ማለዳ ዘግቧል። በኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብዓት የኢንዱስትሪ ልማት ተቋም የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ጥናት እና ቴክኖሎጂ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ስመኝ ደጉ፣ ረቂቅ ሕጉ በቅርቡ በሚወጣው አዲስ የኢንቨስትመንት ደንብ ላይ እንዲካተት እየተሠራ ነው ማለታቸውም ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሲሚንቶ ምርት በቅቷት አቅርቦቱም አርክቷት የነበረ ቢሆንም፣ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በሲሚንቶ እጥረት እና ተያይዞ በመጣ ዋጋ ጭማሪ ስትቸገር ከርማለች። ይህንንም የመብራት አቅርቦት በፈረቃ መሆን፣ የፋብሪካ መለዋወጫ እቃዎች እጥረት፣ የውጭ ምንዛሬ መታጣት እና የምርት ማጓጓዣ ችግር አባብሰውታል ይላሉ – አቶ ስመኝ።

የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ዋጋን አረጋጋለሁ በሚል ከባለፈው ወር ጀምሮ የዋጋ ገደብ ጥሎ እንዲሁም አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሲሚንቶ ገበያውን እንዲቀላቀሉ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ መፍትሔው ዘላቂ እንዳልሆነ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ 14 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እያመረቱ ሲገኙ፣ አሥሩ “የክሊንከር ሲሚንቶ” ያመርታሉ፤ አራቱ ደግሞ ክሊንከሩን ገዝተው ይፈጫሉ።

ይህም ሆኖ፣ 14ቱ ፋብሪካዎች ካላቸው 17.2 ሚሊዮን ቶን ዓመታዊ የማምረት አቅም ውስጥ 57.8 በመቶውን ብቻ በመጠቀም 8.4 ሚሊዮን ቶን ብቻ እያመረቱ እንዳሉም ተወስቷል። የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍላጎት ደግሞ 10 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ ደግሞ ይህም በእጥፍ ይመነደጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ደርባ እና ዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አሁን ያላቸውን 2.5 ሚሊዮን ዓመታዊ የምርት አቅም በእጥፍ ለማሳደግ የማስፋፊያ ፕሮጀክት እቅድ እንዳላቸው የገለጹት አቶ ስመኝ፣ ይህ ብቻውን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ በዓመት እፈልገዋለሁ ከሚለው ሲሚንቶ ውስጥ እስከ 85 በመቶ ለማሳካት ያስችላል ይላሉ።

የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ምርትን እናሳድጋለን እንጂ ከውጪ ሲሚንቶ ማስገባትን አልጀመርንም፤ አላሰብንምም ሲሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

 

ይህንንም ይመልከቱ

kefta-care-training-2

ከፍታ ለ20 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ

ከፍታ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለ20 በሴቶች ለሚተዳደሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው ያተኮረው …