መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ቢ ኤም ደብሊው (B.M.W) ሜታል ኢንጂነሪንግ

ቢ ኤም ደብሊው (B.M.W) ሜታል ኢንጂነሪንግ

ቢ ኤም ደብሊው ድርጅት የተመሠረተው ጥር 2009 ዓ.ም. በአቶ አምሃ ወንድሙ እና በሁለት መሥራች አባላት ነው። ድርጅቱ የተለያዩ ማሽኖችን የማምረት እና የመጠገን እንዲሁም ለማሽኖች የመለዋወጫ እቃዎችን በራሱ ፈጠራ ይሠራል። እኒዚህም እቃዎች በአገር ውስጥ የማይገኙ እቃዎች ሲሆኑ ለእነዚህ እቃዎች የመለዋወጫ እቃ እና የተለያዩ ሞልዶች ያመርታል።

ድርጅቱ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል

  • ጠቅላላ የቶርኖ ሥራ
  • ክሬሸር ማሽኖች ሥራ
  • የሚክሰር ሥራ
  • ሀይድሮሊክ ብሎኬት ማሽን
  • የእምነበረድ መቁረጫ ማሽን
  • የእምነበረድ መፍጫ ማሽን
  • ፓኔል ሥራ
  • የተለያየ መጠን ያላቸው የሻማ ማምረቻ ማሽኖች
  • ስካፎልዲንግ የግንባታ ሊፍት
  • የመኪና ቦዲና የቦቴዎች ታንከር ሥራ
  • የውሀ ቱቦ ሞልዶች
  • የቡና መቁሊያ፣ መፈልፈያ እና ማጠቢያ ማሽን
  • የእርድ መፍጫ ማሽን
  • የከብቶች መኖ ማቀላቂያ ማሽን
  • ተገጣጣሚ የብረት ህንጻዎች
  • ሴሎ ፓቺንግ ማሽን እና ማንኛውንም በሳምፕል እና በንድፍ የሚመጡ ሥራዎችን ይሠራል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ አምሃ ከድርጅቱ ምሥረታ በፊት በተመሣሣይ የሙያ ዘርፍ ተቀጥረው ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን በሙያው ከሃያ አምስት አመት በላይ የሥራ ልምድ ማካበት ችለዋል። አቶ አምሃ የሚሠሩበት ድርጅት አቅም እየደከመ ሲመጣ በራሳቸው ለመሥራት ወስነው ድርጅቱን ከሌሎች አባላት ጋር መሥርተዋል።  ቢ ኤም ደብሊዩ ድርጅት የብሎኬት ማምረቻ ማሽኖች ምርት ጥገና እና የተለያዩ ትልልቅ ማሽኖች ሞዲፊክ ሥራዎችን ይሠራል። በተጨማሪም ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ የሻማ ማሽን ይጠቀሳል፤ ለምሳሌ ስልሳ ሻማ የማምረት አቅም ያለውን ማሽን በሦስት ቀን፤ ሦስት መቶ ሻማ የማምረት አቅም ያለውን ማሽን በዐሥራ አምስት ቀን የማምረት አቅም አለው። ድርጅቱ የአንድን ማሽን ሥራ ከትንሽ እስከ ትልቅ እንደ ማሽኑ ቢለያይም ከሦስት ቀን እስከ ሦስት ወር በሚፈጅ ጊዜ ውስጥ አምርቶ የማስረከብ አቅም አለው። ድርጅቱ ለሚሠራቸው ማሽኖች የጥገና አገልግሎት ይሠጣል። ከዚህም ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ትልቁ ጥቅም ከውጭ የሚመጡ ማሽኖች ቶሎ ይበላሻሉ ድርጅቱ የሚሠራቸው ማሽኖች ግን ለረጅም ጊዜ ያገለግላሉ።

የድርጅቱ መሥራች ድርጅቱን ሲመሠርቱ ሁኔታዎችን ለማስኬድ የትምህርት ዝግጅታቸው እና ሲሠሩበት የነበረው ድርጅት ልምድ ብዙ ነገሮችን አንዳቀለለላቸው አስረድተዋል። ነገር ግን በሥራ ቦታ ላይ በነበሩበት ወቅት የቀሰሙት ልምድ ለድርጅቱ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።

ቢ ኤም ደብልዩ ድርጅት እዚህ ደረጃ ሲደርስ ብዙ ችግሮችን አልፎ ነው። ለምሳሌ ትልቁ የቦታ ችግር ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ ከማሽኖች የሚወጣው የድምጽ ብክለት እና የመብራት መቆራረጥ ናቸው። ይህን ሊያልፉ የቻሉት በታታሪነት እና በታጋሽነት ነው። አቶ አምሃ ተቀጣሪ በነበሩበት ወቅት  ከት/ቤት መልስ ከአሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ስምንት ሰዓት ድረስ ይሠሩ ነበር። ይህ ደግሞ ትልቅ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት በሰው በሰው ነው። ሰዎች ጥሩ ሥራ ከተሠራላቸው ይመሰክራሉ፤ ይህ ደግሞ ብዙ ሥራዎችን ያመጣል። ከመጡ ሥራዎች ለምሳሌ ከአየር ጤና፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ አቃቂ የሚመጡ ሰዎች አሉ። ሌላው የሥራ ማግኛ መንገድ ደግሞ 2merkato.com ለጥቃቅን እና አነሰተኛ ድርጅቶች ባዘጋጀው የከፍታ ፓኬጅ በመጠቀም ጨረታዎች ላይ ይሳተፋሉ። በዚህም ሁለት ጨረታዎችን አሸንፈዋል። የድርጅቱ መሥራች ማስተዋወቅን በተመለከተ ሌላው የተማሩት ነገር ቢዝነስ ካርድ ከመጠቀም ይልቅ ስልክ ላይ ማስመዝገብ የተሻለ ውጤት አለው ብለዋል። ምክንያቱም ቢዝነስ ካርድ ሰው ይጥለዋል፤ ስልክ ላይ ግን አይጠፋም ስልኩ ካልጠፋ በስተቀር። ለመደወልም ቀላል ነው በፈለጉት ሰዓት መደወል ይችላሉ ሲሉ አስረድተዋል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ጥቂቶቹ ዋጋቸው አንደሚከተለው ነው

  • የሽንኩርት መፍጫ፣ የስጋ መፍጫ ማሽኖችን  -ከሠላሳ አምስት ሺህ እስከ አርባ አምስት ሺህ ብር
  • የሻማ ማምረቻ ማሽን – ከሀያ አምስት ሺህ እስከ ሶስት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር
  • የብሎኬት ማምረቻ ማሽን – ከሀምሳ ስምንት ሺህ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ የብሎኬት ማሽን እና ማንኛውንም በሳምፕል እና በንድፍ የሚመጡ ሥራዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ይሠራል።

ድርጅቱ የተመሠረተው በዐሥራ አምስት ሺህ ብር ካፒታል ሲሆን አሁን ላይ  የድርጅቱ ካፒታል አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ደርሷል። እንዲሁም ለ ዐሥራ አምስት ቋሚ ሠራተኞት እና ሰላሣ ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። ድርጅቱ ጦርነቱ በጣም ጎድታል ምክንያቱም ወልዲያ ላይ የሚገኙ 80% በክሬሸር ሥራ የሚሠሩ ድርጅቶች የድርጅቱን አገልግሎት ነበር የሚጠቀሙት፤ በጦርነቱ ምክንያት ይህ ቆሟል።

ድርጅቱ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ይሠራል፤ እንደ አብነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ግሪን ቪን የቡና ማድረቂያ ማሽን ሲሆን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነበር። በዚህም የፈጠራ ችሎታ አንድ ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆኗል። ድርጅቱ በታታሪነቱ እና ጠንካራ በመሆኑ የተለያዩ ሰርተፍኬቶችን ተሸልሟል።

 

ቢ ኤም ደብልዩ ከትልልቅ ድርጅቶች ጋር አብሮ ሲሠራ ቆይቷል። እየሠራም ይገኛል፦ ለምሳሌ ካስማ ኢንጂነሪንግ፣ በርታ ኢንጂነሪንግ፣ መስኮን ኮንስትራክሽን፣ አሰር ኮንስትራክሽን፣ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን። እንዲሁም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ሰርቷል። ለምሳሌ የእርድ መፍጫ ማሽን ከህንድ ሃገር ነበር የሚመጣው፤ ይህንን ሃገር ውስጥ በመሥራት የውጭ ምንዛሬ ወጪን አስቀርቷል። ይህ ማሽን ረጅም ጊዜ እንዲሠራ እና ቢበላሽ ተጠግኖ ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታን ፈጥሯል።

ድርጅቱ ያመረታቸው የእርድ መፍጫ ማሽኖች

የኮቪድ ተፅዕኖ

የኮቪድ ተፅዕኖ በጣም ከባድ ነበር ምክንያቱም ቫይረሱ ብረት ላይ እስከ 72 ሰዓት ይቆያል የሚል ግንዛቤ ስለነበር የተወሰኑ ሥራዎችን ድርጅቱ እንዳይሠራ አግዶት ነበር። በዚህ ጊዜ ወደ ፊት ገበያ ላይ ያስፈልጋሉ የሚባሉ እቃዎችን በማምረት እና እና የጥገና ሥራ በመሥራት ነበር ያለፉት።

 

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ እቅድ አቅዶ ለማሳካት እየሠራ ነው።

የሁለት አመት እቅድ(የአጭር ጊዜ እቅድ)

ከህንድ ሃገር የሚመጡ የዘይት ማውጫ ማሽኖችን፤ የጥቁር አዝሙድ ማሽን በትንሽ ክፍያ ሁሉም ሰው ጋር እንዲደርስ ማድረግ ነው። ዲዛይኑ አልቋል ወደ ምርት መግባት ብቻ ነው የቀረው። የሸንኮራ ስኳር ሁሉም በየቤቱ ማምረት እንዲችል የሚያደርግ እና የሸንኮራ ጁስ መሸጥ እንዲችሉ የሚያስችል ሌላ ማሽን እይሠራ ነው።

የረጅም ጊዜ እቅድ

የተቃጠለ ዘይት ተብሎ ከሚጣለው ምርት ግሪዝ (ግራሶ) ማምረት መጀመር እና የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት። እንዲሁም የጎማ ተረፈ ምርቶችን ወደ ፈርነስ ኦይል መቀየር። ይህ ደግሞ አገሪቱ ዶላር እንዳታወጣ ያደርጋ ዶላር አታወጣም ማለት ደግሞ ዶላር አገኘች ማለት ነው።

 

አዲስ ለሚደራጁ ምክር

አንድ ሰው ሥራ ለመጀመር ሲደራጅ ሥራውን ማወቅ አለበት። ይህም እንዴት ነው የምሠራው? እንዴት ነው ድንበኞች ጋር መድረስ ያለብኝ? የሚለውን ከመለሰ በኋላ ነው ወደ ሥራ መግባት ያለበት።

አቶ አምሃ ስለ 2merkato.com የሚከተለውን ብለዋል “2merkato.com ጨረታዎችን በየቀኑ እየለቀቀልን ነው። እንዲሁም በከፍታ ፓኬጁ ጥቃቅንን እና አነስተኛ ድርጅቶችን ለመደገፍ ዋጋ መቀነሱ ለሃገር የሚያበረከተው አስተዋጽዖ ትልቅ ነው። ጋዜጣ ቢሮ ከሚከመር በስልክ በቀላሉ መከታተል እንዲቻል ማድረጉ የሚበረታታ የሥራ ፈጠራ ነው። በጣም አናመሰግናለን። እንዲሁም እዚህ ድርጅቱ ቦታ (አቃቂ) ድረስ ደረሰኝ ይዞ መምጣት እና መስጠት በጣም የሚገርም እና  የሚበረታታ ነው። ይህም ሥራን ማክበር 2merkato.com ጋር አለ ይህም ይበረታታል።” ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …