መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ኢኤምቲጂኤም (EMTGM) ጄነራል ትሬዲንግ
EMGTM-general-trading

ኢኤምቲጂኤም (EMTGM) ጄነራል ትሬዲንግ

ኢኤምቲጂኤም (EMTGM) ጄነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ ማኅበር ከመመሥረቱ ሃያ አመት በፊት ማህደር ተሰማ ብረታ ብረት በሚል ስያሜ ነበር በአቶ ማህደር ተሰማ የተቋቋመው። አቶ ማህደር በድርጅቱ እየሠሩ በነበረበት ወቅት አቶ ኢዩኤል ግርማቸው (አሁን በድርጅቱ ውስጥ በማናጀርነት እያገለገሉ የሚገኙ አባል) ትምህርታቸውን ጨርሰው በ1997 ዓ.ም ወደ ድርጅቱ ተቀላቀሉ። በ2000 ዓ.ም ድርጅቱ ወደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (Private Limited Company) ቢለወጥ ጥሩ የተሻለ ውጤታማ ይሆናል ብለው ድርጅቱ ወደ PLC ተቀይሯል። ድርጅቱ ከተቋቋመ ሃያ አመት ቢሆነውም በPLC ደረጃ አሥራ አንድ አመታትን አስቆጥሯል።

ድርጅቱ የሚሠራቸውን ሥራዎች በሶስት መንገድ ከፍሎ እየሠራ ይገኛል እነዚህም

  1. ኅብረተሰቡ የሚገለግልባቸው ምርቶች ማምረት፦ የአልሙኒየም ሥራዎች፣ በር፣ መስኮት እና ሌሎችም
  2. ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶች እንደ ከንቾች እንዲሁም ሙሉ የኢንዱስትሪዎችን እቃ ማምረት
  3. የኮንስትራክሽን ሚክሰሮች እና ተያያዥ የኮንስትራክሽን ማሺነሪ ሥራዎች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ በአንድ መሥራች አባል ተመሥርቶ የነበረው ወደ ሁለት መሥራች አባላት ሲያድግ የተለያዩ የሥራ አማራጮች መፍለቅ ጀመሩ። እነዚህን ሀሳቦች ለማሳካት አዳዲስ  ማሽኖችን ማስገባት የሚለው የመጀመሪያ እርምጃ ነበር። ይህንንም ሥራ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ አዲስ ተጨማሪ ማሽኖችን ማስገባት፣ በቀጣይም በሀገር ውስጥ መመረት የማይችሉ እቃዎች በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ገቢ እቃ ለመቀነስና የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለማስቀረት እየሠራ ይገኛል። ከነዚህ ምርቶች ውስጥ የባጃጅ ቦዲ መሥራት፣ ሚክሠሮች፣ የብረት እስካፎልዶች ከውጭ ሀገር ነበር የሚመጡት ይህን ለማስቀረት እነዚህን ምርቶች አገር ውስጥ በማምረት ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

አቶ ኢዩኤል ግርማቸው ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን የመረጡበት ምክንያት የአቶ ማህደር ተሰማ ብቃትና ስኬት ተፅዕኖ ስላሳደረባቸው ነው፤ ስለሆነም በዚህም ሙያዊ ተፅዕኖ ወደ ዘርፉ ገብተዋል። በተጨማሪም አቶ ኢዩኤል ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን ልምድ እና መሠረታዊ ክህሎቶች በሙያው ከፍተኛ ብቃት ካዳበሩ የሥራ ባልደረቦች በመማርና የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ እውቀታቸውን ገንብተዋል።

ኢኤምቲጂኤም (EMTGM) ከቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ቤት የሚላኩ ተማሪዎችን በማሠልጠን አገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ተማሪዎች ለሙያው ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም በሙከራ  በማበረታታት ብዙ ተማሪዎችን አብቅቷል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት በሰው በሰው ነው የሚሉት አቶ ኢዩኤል “ጥሩ ነገር ከተሠራ ደንበኛው ጥሩ ነገር ይናገራል፣ ይመሰክራል፤ መጥፎ ከተሠራም እንዲሁ ነው ይህ ደግሞ የሥራ ውጤትን ይቀንሳል። ስለዚህ አንድ ደንበኛ በተሠራለት ሥራ ካልተደሰተ ድርጅቱ ምኑ ጋር ነው ያጠፋነው እንዴት ይስተካከል በማለት ቀን በቀን ራሱን ያሻሽላል። በተጨማሪም ቴክኖሎጂን ይጠቀማል ድሮ እያንዳንዱ ደንበኛ ጋር በመሄድ በማናገር እንዲሁም ጨረታ ጋዜጣ በማንበብ በማገላበጥ አንዱ ጋር ከሌለ ሌላ ጋር በመሄድ ነበር አሁን ግን ሁሉንም በዲጂታል መረጃ ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ እንደ ግዢ፣ ጨረታ፣ ደንበኛ ድረስ መሄድ ሳያስፈልግ ብዙ ሥራን መሥራት ይቻላል ጊዜን ይቆጥባል።” ድርጀቱ የ2merkato.com የጨረታ አገልግሎት የረጅም ጊዜ ተጠቃሚ ነው።

“ኢኤምቲጂኤም (EMTGM) ጄኔራል ትሬዲንግ በተለያዩ መንገዶች ራሱን ያሳድጋል ለምሳሌ ክፍያዎችን በመክፈል ለሠራተኞች የተለያዩ ሥልጠናዎችን  ያመቻቻል። ሠራተኞች በሚያሳዩት የሥራ ብቃት ድርጅቱ ሌሎች ከፍተኛ ትምህርቶችን የሚማሩበት መንገድ ያመቻቻል። ብዙ ሥራ መሥራት የሚችሉ ነገር ግን በወረቀት ምክንያት የሥራ እድል ያላገኙትን ሠራተኞች ድርጅቶች እድል ቢሰጧቸው ለድርጅቱም ለሠራተኞቹም ይጠቅማል።

ድርጅቱ የዐጭር እና የረጅም ጊዜ እቅዶች አሉት፤ እነዚህ እቅዶች ካልተሳኩ ምንድን ነው ችግሩ? ምኑጋ ነው የተሳሳትነው የሚለውን ነገር በማስተካከል ይሠራል። ግብ በጣም ያስፈልጋል ከምንም በላይ እግዚአብሔር እርዳታ ያስፈልጋል።” ይላሉ አቶ ኢዩኤል።

ድርጅቱ ስኬታማ ሊሆን የቻለው የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ነው። እነዚህም ችግሮች አመቺ ያልሆነ የሥራ ቦታ፣ የእቃዎች ዋጋ መናር፣ እቃ በወቅቱ አለመገኘት፣ ሠራተኛን በወቅቱ አሠልጥኖ ወደ ሥራ አለማስገባት ሲሆኑ፣ ለችግሮቹ የተለያዩ መፍትኂዎችን በመፈለግ በሁደት ሊፈቱ ችለዋል። ለምሳሌ የሚቀበሉት ሥራ ትርፍ ባይኖረውም ሠራተኛ እንዳይቀመጥ ሥራ ይሠራል። አንዳንድ እቃዎች ቶሎ አይገኙም ትዕዛዝ ቶሎ አይመጣም ገንዘብ ሊዘገይ/ሊቀር ይችላል፤ ብዙ ችግሮች ሲደራረቡ ተስፋ ሊያስቆርጡ ይችላሉ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ዓላማን ማየት፣ መታገስና ጥረትን መቀጠል ያስፈልጋል። በዚህም የድርጅቱ እድገት ከዌልዲንግ ማሽን ተነስቶ ትልልቅ ማሽኖችን እስከ መግዛት፤ ሥራውን አስፍቶ በፋብሪካ ወይም በኢንዱስትሪ ደረጃ ለመሥራት ከመንግሥት አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ወስዶ ፕላን አዘጋጅቶ በማስፋፋት ላይ ነው። በዚህ ሂደት ከዐሥር በላይ ሠራተኞች ራሳቸውን ችለው ወጥተው ድርጅት ከፍተው እያደጉ ነው፤ ይህም ሥራውን ላስጀመራቸው ለድርጅቱ ትልቅ ስኬት ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ድርጅቱ ላይ ያመጣው ችግር ቢኖርም ድርጅቱ የሚገባውን ጥንቃቄ በማድረግ ምርት ማምረት የቀጠለ ሲሆን ነገር ግን የተመረተውን ምርት ወደ ኅብረተሰቡ ለማድረስ ጊዜ ይፈልግ ነበር። አንዱ ችግር የነበረው ምርት እንደ በፊቱ ቶሎ ቶሎ አልመሸጡ ነበር። አቶ ኢዩኤል “ከሥራ ባልደረቦች በበሽታው የተጠቁ ነበሩ ነገር ግን ቅዱስ እግዚአብሔር ይመስገን የከፋ ነገር የድርጅቱ አባላት ላይ ሳይደርስ አልፈነዋል” ብለዋል።

ምክር እና እቅድ

ወደ ሥራ ለሚገቡ ሰዎች የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል። “አንድ ሰው አንድ ሥራ ሲጀምር ከምንም በላይ ፈሪሃ እግዚአብሔር ሊኖረው ይገባል። ለምን? ለሚመጣው ሰው (ለደንበኛው) ሁልጊዜ  ለራሱ እንደሚሠራው አድርጎ በጥራት መሥራት አለበት፤ ይህ ደንበኛ ለፍቶ ጥሮ ባመጣው ገንዘብ ሥራ እንዲሠራለት ሲመጣ በጥራት ሊሠራት ይገባል።  በመቀጠል አንድ ሥራ ሞክሮ በአጭር ጊዜ ወደ ሌላ ሥራ መሄድ አይገባም፤ አንድ ሥራ ይሳካል ብሎ አእምሮውን ማሳመን አለበት። ሥራው ላይ ፕሮፌሽናል መሆን መቻል እና እስከ መጨረሻው ሠርቶ ውጤት ካጡ መቀየር እንጂ ይሄ ነገር አያዋጣም በማለት በዐጭር ጊዜ ዝም ብሎ መተው ተገቢ አይደለ። አያዋጣም ከማለት በፊት ምን ያህል እና እንዴት ተሠርቷል ተብሎ ችግሩ ምን እንደሆነ በዝርዝር መታወቅ አለበት።”

እንደ ተጨማሪ አቶ ኢዩኤል ስለ ራስ ሥራ ጥቅሞች የሚከተለውን ብለዋል። “እንደ ራስ ሥራ በደንብ የሚሠራ ሥራ የለም፤ በራስ ሥራ ላይ ምን ያህል ሰው አፍርቻለሁ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ገንዘብ ሲጨምር ስንት ሰው አብሮ ተለውጧ፣ ለምሳሌ ምን ያህል ሰዎች በሙያ ሠልጥነው ወጡ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። የራስ ሥራ እቅድ የሚቻለው ከቅዱስ እግዚአብሔር እርዳታ ቀጥሎ ራሱ ባለቤቱ ነው። የራስን ሥራ መሥራት ከአገሪቷ ላይ የሥራ አጥ ጫና ይቀንሳል፤ የሥራ እድል መፍጠር መቻል ትልቅ የመንፈስ እርካታ ይሰጣል።”

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …