መነሻ / የቢዝነስ ዜና / በአዲስ አበባ 125 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ እንደሆነ ምክትል ከንቲባው ተናገሩ

በአዲስ አበባ 125 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ እንደሆነ ምክትል ከንቲባው ተናገሩ

በአዲስ አበባ ከተማ በተመጣጣኝ ዋጋ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ 125 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጅነር) ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 7ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን በዚህ ወቅት ምክትል ከንቲባው የ2012 በጀት አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።

በዚህ ሂደት ላይ ውዝፍ የባንክ ቤት እና የወሰን ማካለል ሂደቶች ችግር ቢፈጥሩም፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለዜጎች ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

በግንባታ ላይ ከሚገኙ የጋራ መኖርያ ቤቶች መካከል 95 ሺህ የሚሆኑት የ20/80 ቤቶች መሆናቸውን ያስታወቁት ኢንጅነር ታከለ ኡማ 29 ሺህ ቤቶች ደግሞ በ40/60 መርሃግብር በግንባታ ላይ ናቸው ብለዋል።

ምክትል ከንቲባው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፓርት ባለፉት ሁለት ዓመታት የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል። በተለይ ለበርካታ ዓመታት በከተማው አስተዳደር ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆዩ አርሶ አደሮችን በተለያዩ ዘርፎች የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በከተማዋ የሸገር ዳቦ፣ እንስራ የገበያ ማዕከል፣ የሸማ ማዕከላት፣ የትምህርት ቤቶች እድሳት እና የእንጦጦ መናፈሻን የመሰሉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል። ለዚህም የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበረ አንስተዋል።

ከተማዋ ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ፣ አቅመ ደካሞችን የማትዘነጋ፣ እና ተስፈኛ ተማሪዎችን ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው ተጠቁሟል።


የዜና ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

ይህንንም ይመልከቱ

kefta-care-training-2

ከፍታ ለ20 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ

ከፍታ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለ20 በሴቶች ለሚተዳደሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው ያተኮረው …