መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / የትጋት ውጤት – ኤርሚያስ ከበደ ጠቅላላ የእንጨት ሥራ ድርጅት

የትጋት ውጤት – ኤርሚያስ ከበደ ጠቅላላ የእንጨት ሥራ ድርጅት

ኤርሚያስ ከበደ ጠቅላላ የእንጨት ሥራ ድርጅት የተመሠረተው በ2000 ዓ.ም በአቶ ኤርሚያስ ከበደ ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የቤት እና የቢሮ እቃዎችን በጥራት ያመርታል። ድርጅቱ  ከሶስት እስከ አምስት የሚደርሱ ፎቆችን (የወረዳ ህንጻ አይነቶችን) ሙሉ በሮች እና መስኮቶች ከዐሥራ አምስት እስከ ሀያ ቀን ድረስ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ከአምስት እስከ ስምንት የሚደርሱ በሮች እና ዐሥር ድረስ የሚደርሱ መስኮቶችን ደግሞ ከዐሥር ቀን እስከ ዐሥራ አምስት ቀን አምርቶ የመግጠም አቅም አለው።

ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ

  • የውስጥ እና የውጭ በሮች
  • የህፃናት እና የአዋቂዎች አልጋዎች
  • ኖርማል እና የግድግዳ ቁም ሳጥን
  • ወንበር እና ጠረጴዛ
  • የመጻሕፍት እና የጫማ መደርደሪያ ሼልፍዎች

ምሥረታና ዕድገት

አቶ ኤርሚያስ ድርጅቱን ሊመሠርቱ የቻሉበት ዓላማ ሙያው በጣም ስለሚያስደታቸው እና ራሳቸው በሚፈልጉት መንገድ ሙሉ ሥራውን ለመሥራት ካላቸው ፍላጎት ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ ለሌሎች ዜጎች የሥራ አድል በመፍጠር ሀገራቸውን ለመጥቀም ነው።

ኤርሚያስ ከበደ ጠቅላላ የእንጨት ሥራ ድርጅት ከመመስረቱ በፊት አቶ ኤርሚያስ በረዳትነት ተቀጥረው ለሦስት አመታት ሲሠሩ ቆይተው አስፈላጊውን ልምድ ካካበቱ በኋላ የግላቸውን ድርጅት መሠረቱ። ከድርጅቱ ምሥረታ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዙኦሎጂካል ሳይንስ በዲግሪ  እና በፔዳጎጂ በዲፕሎማ ፕሮግራም ትምህርታቸውን ተምረዋል። ነገር ግን በዚሀ ሙያ ሥራ ቢጀምሩም ሥራው የሚፈልጉትና የሚያስደስታቸው ሙያ አልነበረም። እሳቸው የሚያስደስታቸው የነበረው የእንጨት ሥራ ስለሆነ ይህንም በመሥራታቸውና ውጤታማ ሊሆኑ ችለዋል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ለሃያ አንድ ቋሚ እና ለሁለት ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።  በዚህም ጊዜ ውስጥ የድርጅቱን አቅም የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎችን የገነቡ ሲሆን ከሚጠቀሱት መካከል ለምሳሌ ኖርማል ማጠፊያ ይጠቀሙ የነበረው አሁን ሰስንፔሽን መጠቀም እና የበር መዝጊያ (እጀታ) ብዙ ዘመናዊ ማሽኖች በመምጣታቸው ማሽኖቹን መጠቀም ጀምሯል። እንዲሁም ምርት ለማምረት ይጠቀምበት የነበረውን የሀገር ውስጥ ምርት እጅግ በተሻለ ከውጭ በሚመጡ የጥሬ እቃዎች ተክቶ ማምረት ጀምሯል። እንዲሁም አዳዲስ ዲዛይኖችን በማምረት እየተማረ፣ እያደገ ነው። አዳዲስ እና ዘመናዊ ማቴሪያሎችን ድርጅቱ ዘወትር ይጠቀማል።

ድርጅቱ ሲመሰረት አንድ ብቻ የነበረው የማምረቻ ቦታ አሁን ሁለት የማምረቻ ቦታ ያደረሰ ሲሆን፣ እንዲሁም ምንም የምርት ማሳያ ሱቅ ያልነበረው በአሁኑ ጊዜ ሁለት የማሳያ ሱቆችን ሊከፍት ችሏል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጽዕኖ ከባድ ስለነበር ተጠናቀው ማለቅ ያለባቸው ሥራዎች ለአንድ ወር እና ሁለት ወር ተጓትተው ነበር፡፡ ይህ አንዱ ማሳያ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የደንበኛ የማሠራት ፍላጎት ቀንሶ ነበር። እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ድርጅቱ አጢኖ የመሻገሪያ መፍትኄ በመፈለግ ረገድ በአቶ ኤርሚያስ የፈጠራ ሥራ እጅዎትን በአግርዎት ይታጠቡ የሚል ጊዜውን ያገናዘበ የፈጠራ ውጤት በመጠቀም ማንም ሰው ያለምንም አጅ ንክኪ እጅን ማስታጠብ የሚያስችል ማሽን ዲዛየን በመንደፍ በቀን አምስት ምርት እያመረተ ለገበያ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህንንም ምርት ለቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ ጃክሮስ፣ ቦሌ ክ/ከተማ ግቢ ውስጥ፣ በንግድ ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ፣ በንብ ባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ለኮሮና ወረርሽኝ መዋጋት የራሱን ኃላፊነት በመወጣት እና ገቢ በማግኘት ራሱንም ሊጠቅም ችሏል።  ከዚህም የተነሳ ችግር ሲኖር መሸሽ ሳይሆን መፍትኄ መፈለግ እንደሚገባ አቶ ኤርሚያስ ምክር ለግሰዋል።

ድርጅቱ ምርቱን በቴሌግራም እና በሁለት ማሳያ ሱቆች ጃክሮስ እና ገርጂ አካባቢ በመጠቀም ምርቱን ያስተዋውቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጀቱ ብዙ ደንበኞች ያሉት ሲሆን በሥራው የረኩት ደንበኞች እነሱም ለሥራው ሰው በሰው ያመጣሉ። እንዲሁም የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ  ስድስት መቶ የተማሪዎች ዶርም በር፣ የላብራቶሪ ዶርም እና ቢሮዎችን ከኮንትራከተሮቹ ጋር በመነጋገር ሠርቶ አስረክቧል።

ቴክኖሎጂ መጠቀም በጣም ጠቃሚ ነው ለምሳሌ ድሮ ቀለም ለመቀባት በአጅ ነበር አሁን በኮምፕረሰር ነው የሚጠቀሙት እንጨት መቁረጫ በመጋዝ ነበር አሁን ማሽኖች ሥራ ላይ አውለዋል። የቴሌግራም ቻናል  በጣም ጠቃሚ ነው።  እነዚህ ሁሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሲሆኑ በሥራ ወቅት የሚባክን ብዙ ጊዜን ሊቀንስና ደንበኛን በቀላሉ ለመድረስ አስችሏል።

ድርጅቱ ውጤታማ ሊሆን ያስቻለው ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ስነ-ምግባር ነው። አንድ ሥራ የግሌ ብለህ መኩራራት ተገቢ አይደለም ይልቁንም በመልካም ዲስፕሊን የሥራ ሰዓት ማክበርና ይልቁንም ረዘም ላለ ሰዓት መሥራት፣ ውጤታማነት፣ ለደንበኛ ፍላጎት ተገቢ ትኩረት በመስጠት ምርትና አገልግሎት በመስጠት ረገድ ምርታማነትን ማሳድግ ይገባል። የሥራ ሰዓትና ምርት ብክነት በድርጅት እድገት ላይ ጉዳት ያስከትላል። ይህ ደግሞ አንዳይሆን ሁል ጊዜ በሥራ ቦታ መገኘት ተገቢ ነው። በጧት ሥራ መጀመር እንዲሁም ማታም ማምሸት እንደ አ

ስፈላጊነቱም ሌሊትም መሥራት ለውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። ተቀጣሪ ከሆንክ  ልሥራ ብትል እ

ንኳን እስከተወሰነ ሰዓት ድረስ እንጂ ማምሸት አትችልም። የግል ሥራ ሲሆን ካለህ ነጻነትና ፍላጎት አንጻር መሥራት ትችላህ ሲሉ ተናግረዋል።

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ ለወደፊት እቅድ ብድር በመበደር ማሽን በመግዛት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብድሩን በመመለስ ቀጥሎ ደግሞ በመበደር ሌላ ቅርንጫፍ ለመክፈት አቅዷል አሁን ሥራው የተቀዛቀዘ በመሆኑ እቅዱን ለማሳካት እየተቀሳቀሰ ይገኛል።

ድርጅቱ ጨረታ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ አይጠቀምም። በአሁኑ ጊዜ ግን በ2merkato.com ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች የተዘጋጀውን ከፍታ የቴሌግራም ቻናልን በመጠቀም ምርት እና አገልግሎቱን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።

አቶ ኤርሚያ አዲስ ወደ ግል ሥራ ለሚገቡ ሰዎች የሚሰጡት ምክር የሚወዱትን ሥራ እንዲሠሩ ይመክራሉ። ውጤታማ ለመሆን የሚወዱትን ሥራ ከሆነ የሚሠሩት ምንም ቢፈጠር ስለማይሰላቹ  እና ሥራውን ስለሚወዱት ይህ ደግሞ ሥራውን በትጋት እንዲሠሩ በጣም ይጠቅማቸዋል። ይሄ ደግሞ ስኬታማ ያደርጋል።

ወደ  እንጨት ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

የእንጨት ሥራ ቀላል አይደለም ቋሚ ደንበኛ ለመያዝ ብቻ ከአምስት እስከ ስምንት ዓመታት ሊፈጅ ይችላል፡፡ የራስ ሥራ መስራት ጥቅም አለው ሆኖም ግን በቂ እውቅና ለማግኘትና ደህና ቦታ ላይ ለመድረስ ትዕግሥትና ትጋት ይጠበቃል ።

 

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …