ድርጅቱ የተመሠረተው በወ/ሪት ኢየሩሳሌም ቱፋ እና ሦስት መሥራች አባላት በ2014 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶችን በጥራት ያመርታል።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች
- ቀበቶ
- የወንድ እና የሴት የኪስ ቦርሳ
- በጎን የሚንጠለጠል ቦርሳ (ሳይድ ባግ)
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ወ/ሪት ኢየሩሳሌም ራሳቸውን ለመለወጥ እና ብሎም ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስበው ወደ ዘርፉ እንደገቡ ይናገራሉ። የድርጅቱ መሥራች ወደ ቆዳ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በአካውንቲንግ ትምህርት ተምረው በባንክ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። እዛም በሚሠሩበት ጊዜ የቆዳ ሥራ፣ የልብስ ስፌት፣ እና የምግብ ዝግጅት ሥራ ሥልጠና እንዳለ መረጃው ይደርሳቸዋል። የቆዳ ሥራ ሙያውን ስለሚወዱት እና የግል ሥራ ደግሞ በደንብ ከደከሙበት ተቀጥሮ ከመሥራት የተሻለ እንደሚሆን በማሰብ የቆዳ ሥራ ትምህርት ለመማር ተመዘገቡ። ትምህርቱን ከተማሩ በኋላ ለአንድ ወር ለተለማማጅ ሥራ (apprenticeship) ወጡ። ለመለማመድ ሲወጡ የባንክ ሥራቸውን በማቆም ነበር። በዚህ የልምምድ ጊዜ የወጡበት ድርጅት በደንብ ብዙ ነገሮችን በሚገባ እንዳስተማራቸው ጠቅሰዋል።
የድርጅቱ መሥራች የልምምድ ጊዜአቸውን እንደጨረሱ ስድስት መሥራች አባላት በመሆን አንድ መቁረጫ እና አንድ መስፊያ ማሽን በመግዛት ድርጅቱን መሥርተዋል። በሂደት ሁለት መሥራች አባላት በግል የራሳቸውን ሥራ መሥራት በመጀመራቸው ድርጅቱን የለቀቁ ሲሆን ሥራዎች ሲመጡ ግን በመተጋገዝ እየሠሩ ይገኛሉ።
ድርጅቱ አሁን ላይ ያሉትን የማሽኖች ቁጥር ወደ አራት ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ለአራት ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ድርጅቱ ምርት የማምረት ሂደት ላይ በዲዛይን እና ፓተርን አወጣጥ በጣም ጥሩ የሚባል የጥራት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ወ/ሪት ኢየሩሳሌም ጠቅሰዋል። የድርጅቱ የማምረት አቅም እንደ ቦርሳው ዐይነት ቢለያይም በአማካይ በቀን ስድስት ቦርሳ የማምረት አቅም አለው።ቀበቶ እና ሌሎች ሥራዎችን ከጨመረ ግን በቀን እስከ ዐሥራ ዐምስት ይሠራል።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ እንደ ቦርሳው ትልቅነት እና የሚፈጀው የቆዳ መጠን እንዲሁም የቆዳ ጥራት ደረጃ ቢለያይም
- ቀበቶ ከብር 250 – ብር 350
- የሴት ቦርሳ ከብር 1000 – ብር 1500
- አነስተኛ የትከሻ (Shoulder) ቦርሳ ከብር 450 – ብር 600 ብር እየሸጠ ይገኛል።
ምክር እና ዕቅድ
ድርጅቱ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኘው በዋናነት ሶሻል ሚዲያ ሲሆን ይህም ፌስቡክ እና ቴሌግራም በዋናነት ሲጠቀም ቆይቷል። ይሁን እና በቅርብ በነበረው የኢንተርኔት መገደብ የድርጅቱ ሥራ ላይ በጣም ትልቅ ተጽእኖ በማድረግ ሥራው እንዲቀዛቀዝ አድርጓል። ከዚህ በመቀጠል ድርጅቱ ባዛር እና ኤግዚቢሽኖች ላይ በመሳተፍ ምርቱን ያስተዋውቃል።
ወ/ሪት ኢየሩሳሌም የግል ሥራ በራስ መተማመን ቢጨምርም ብዙ ኀላፊነቶች እንዳሉት አክለዋል። ለምሳሌ የቆዳ ሥራ ላይ የጥሬ እቃ ችግር፣ በየሳምንቱ የሚፈጠር የዋጋ ልዩነት እና ደንበኛ ማሳመን አስቸጋሪ የሚባሉት ነገሮች ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል። ሥራውን በፍላጎት እና በትዕግስት መሥራት ለእርሳቸው መፍትሔ እንደሆናቸው ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በዐጭር ጊዜ ዕቅድ በመጪው ስድስት ወራት ውስጥ አንድ የማሳያ ሱቅ የመክፈት ዕቅድ አለው። በረጅም ጊዜ ዕቅድ ደግሞ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ቢያንስ አንድ አንድ ሱቆች የመክፈት ዕቅድ አለው።