taf-leather

ታፍ ሌዘር

ታፍ ሌዘር የተመሠረተው በ 2004 ዓ.ም. በወይዘሮ ትዝታ አሰፋ እና በስድስት ሴት መሥራች አባላት ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የቆዳ ውጤት የሆኑ ምርቶችን ያመርታል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የሌዘር ጃኬቶች
  • የቆዳ ቦርሳዎች
  • ከቆዳ የሚሠሩ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ጓንቶች
  • ለተለያየ ሥራ የሚሆን የቆዳ ሽርጥ (Apron)
  • ጫማ እና አጠቃላይ ማንኛውም ከቆዳ የሚሠራ ነገር በደንበኛው ፍላጎት መሠረት በጥራት ሠርቶ ያስረክባል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ ትዝታ ወደ ቆዳ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የኮንስትራክሽን ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል። ይሁን እና ኮንስትራክሽን እየሠሩ በነበረት ጊዜ የተለያዩ ሥራዎችን የማየት አጋጣሚ ነበራቸው። የነበራቸው የቆዳ ውጤቶች ላይ የመሥራት ፍላጎት ከሚያጠኑት የገበያ ጥናት ጋር ተደምሮ፤ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ሥራው ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር የመገናኘት እድል ፈጥሮላቸው፤ እነኝህን አጋጣሚዎች በመጠቀም እና የተፈጠረላቸውን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የገበያ ዕድል እንዲሁም ያለውን የቆዳ ሀብት በማየት ወደ ቆዳ ሥራ ገብተዋል።

የድርጅቱ መሥራች አባላት በሴቶች ላይ መሥራት እና ሴቶችን ማብቃት ዐላማቸው ስለነበር ነው ሁሉም የድርጅቱ አባላት ሴቶች የሆኑት። ሥራው ያለውን ውጤታማነት በማየት ስለ ሥራው አስፈላጊውን ክህሎት ለመቅሰም የሚያስፈልገውን ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ቆዳ ሥራ ገብተዋል። እንደ ድርጅቱ መሥራቾች የቆዳ ሥራ ገና አልተሠራበትም ብዙ ሀብት እንዳለ እና ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር መሥራቾቹ የሚስማሙበት ነገር ነው።

እነ ወሮ ትዝታ ድርጅቱን ሲመሠርቱ የነበረው ከባድ ነገር ያለውን ስጋት (risk) ተመልክቶ ጨክኖ ወደ ሥራ መግባት እንደነበረ ይገልጻሉ። ገበያ ማግኘት፣ ጥሬ እቃ አቅራቢ ድርጅት ጋር መዋዋል እና በተገቢው ጊዜ ጥሬ እቃ መቀበል ቀጥሎ የሚጠቀሱ ችግሮች ነበሩ።

ድርጅቱ ሲመሠረት እንዳንድ ሥራዎችን ቀድሞ መጀመሩ እና የሚያሳካው ግብ ማስቀመጡ ነገሮችን ጥቁር እና ነጭ አድርጎ ማየት እንዲችል እና ሥራውን በተገቢው ዕቅድ እንዲመራ እንዳስቻለው የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል። ድርጅቱ አሁን ያለውን ገናና የጥራት ስም ያገኘው ገና በምሥረታ ላይ እያለ በጥራት (quality) ላይ በጥልቀት ማተኮሩ እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል።

የድርጅቱ ምርት የማምረት አቅም፡- ድርጅቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከቆዳ የሚሠሩ ሁለት ሺሕ ጓንቶች፣ ሠላሳ ጃኬቶች እና ሦስት መቶ ጫማዎችን በአንድ ቀን የማምረት አቅም አለው። ታፍ ሌዘር አሁን እየሠራ የሚገኘው የብዛት ሥራ ሲሆን ደንበኛ ማሠራት ከፈለገ ትንሹ ማዘዝ የሚችለው መጠን ለምሳሌ ጓንት አምስት ሺሕ እና ከዛ በላይ ነው። ለጫማ ደግሞ ትንሹ መጠን ሁለት መቶ እና ከዛ በላይ ነው። ጃኬት እና ቦርሳ ላይ ይህ ነው የተባለ ገደብ የለውም ግን የሚሠራው ምርት ቁጥር ሲቀንስ ወይም ከሃምሳ በታች ከሆነ ዋጋው ይወደዳል፤ ብዛቱ ሲጨምር ደግሞ ዋጋው ይቀንሳል። የሚመጣው ሥራ ልዩ ከሆነ ተነጋግሮ በመግባባት ማሠራት ይቻላል። በችርቻሮ መግዛት የሚፈልጉ ደንበኞች የማሳያ ሱቅ በመሄድ መግዛት ይችላሉ።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሲሆን ተጠቃሾቹ የድርጅቱ ሠራተኞች ራሳቸው በተለያየ ምክንያት ከሀገር ውጭ ሲሄዱ በሚያመጧቸው ሥራዎች ነው። ሁለተኛ ድርጅቱ በሥራው የሚታወቅ ስም ስላለው በሰው በሰው በሚመጣ ብዙ ሥራ ነው። ሌላው ደግሞ የምርት ማሳያ ሱቅ ለቡ አካባቢ አለው፤ እዛም በመሄድ ከሚሸምቱ ደንበኞች እንዲሁም ደግሞ በተለያዩ ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ ምርት እና አገልግሎቱን ለተገልጋዮች እያቀረበ ይገኛል። ከዚህ በጨማሪ በድረ-ገጹ በኩል (tafleather.com) እና ከማኅበራዊ ሚዲያ ደግሞ ኢንስታግራምን በመጠቀም ምርቱን ያስተዋውቃል። በውጭ ሀገር አራት ደንበኞች ያሉት ሲሆን፤ አንድ ደቡብ አፍሪካ፣ ሌላ ከዛምቢያ፣ እንዲሁም አሜሪካ እና ፈንሳይ ይገኛሉ። በሀገር ውስጥ ደግሞ ለሦስት ቋሚ ድርጅቶች ጓንት እያቀረበ ይገኛል። በጠቅላላው ድርጅቱ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የብዛት ሥራዎች ሠርቶ አስረክቧል። ታፍ ሌዘር ከሌሎች ድርጅቶች የሚለው በሀገሪቱ በድርጅቱ ደረጃ በዚህ ስፋት የሚያመርት ድርጅት አለመኖሩ ነው።  እንዲሁም 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመገንዘባቸው እና እነሱን እንደሚጠቅም ስለተረዱ ከፍታ ለኢንተርፕራይዞች ባዘጋጀው ፓኬጅ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።

ድርጅቱ ሲመሠረት የነበረው መነሻ ካፒታል ሦስት መቶ ሺህ ብር እና ሥራውን የሚሠራው ድግሞ በመኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ነበር። በሂደት በነበራቸው የሥራ ጥራት እና አፈፃፀም ተመርጠው አሁን ያሉበት የማምረቻ ቦታ (ሼድ) ተሰጥቷቸዋል። የካፒታላቸው መጠንም ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ማደግ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ለሃያ ስምንት ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ሥራ ሲበዛ ደግሞ እንደ ሥራው ዓይነት በጊዜያዊ እና ቋሚነት ይህ ቁጥር ወደ ሰባ ከፍ ይላል።

ድርጅቱ በተሞክሮ የተረዳው ያመጣለት ነገር ሥራ በማታ (ሌሊት) መሥራት ጥሩ እንደሆነ ነው፤ ውጤትም አምጥቶለታል። በዚህም ሠራተኞች ሀሳባቸው አይከፋፈልም፤ የሚረብሽ ነገር የለም እና በቂ የሆነ የኤሌክትሪክ ኅይል ስለሚኖር ውጤታማ የሆነ ሥራ እንዲሠራ ያደርጋል። ድርጅቱ ከተቸገረበት ነገር አንደኛው በቆዳ ዘርፍ ብቁ የሆነ ባለሙያ ማነስ እንደሆነ የድርጅቱ መሥራች ገልጸዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ጊዜ ድርጅቱ በጣም ተቸግሮ ነበር ምክንያቱም የሚያመርታቸውን ምርቶች በይበልጥ በውጭ ገበያ ላይ ያቀርብ ስለነበር በኮቪድ ጊዜ ደግሞ እቃ መላክ እንዲሁም እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ገበያ ማግኘት ባለመቻሉ ተፅዕኖ ነበረው። ይሁን እና በጊዜው የነበረውን ችግር ወደ ዕድል በመቀየር የፊት መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ለሦስት ድርጅቶች በማምረት ኪሣራ ውስጥ ሳይገባ ማለፍ ችሏል።

ምክር እና ዕቅድ

ድርጅቱ ወደ ፊት ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ ለመዘዋወር፣ የበለጠ በሴቶች ላይ የሚሠራ ድርጅት ሆኖ ሴቶች በኢኮኖሚ መጠንከር የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ እና በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ አንድ የምርት ማሳያ ሱቅ ከሀገር ውጭ የመክፈት ዕቅዶች አሉት።

አዲስ ሥራ የሚጀምር ሰው የሚጀምረውን ሥራ ለምዶ ቢገባ (ቢያንስ ሁለት ዓመት ልምድ ቢኖረው)፣ እንዲሁም ደግሞ ገበያውን አጥንቶ ለማን ነው የማስረክበው የሚለውን ተዘጋጅቶበት ቢገባ መልካም ነው ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …