መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ዮብ ፈርኒቸር

ዮብ ፈርኒቸር

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ዮናስ ቢያድግልኝ በ2005 ዓ.ም. ነው። ይህ ድርጅት አጠቃላይ የእንጨት ሥራዎችን በጥራት ያመርታል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል

  • የተለመደው ቁምሳጥን እና የግርግዳ ላይ ተለጣፊ ቁምሳጥን
  • የህፃናት እና የአዋቂዎች አልጋ
  • የውስጥ እና የውጭ በሮች እና መስኮቶች
  • ድሬሲንግ ቴብል
  • የተለያየ ዲዛይን ያላቸው ሶፋዎች
  • የኪችን ካብኔቶች እና
  • ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የቤት እና የቢሮ እቃዎች

አቶ ዮናስ ወደ እንጨት ሥራ የገቡበት ዐብይ ምክንያት ለዘርፉ በነበራቸው ትልቅ ፍቅር እንደሆነ እና ይህንንም ፍቅራቸውን እውን ለማድረግ እስፈላጊውን ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ ሊገቡ እንደቻሉ ተናግረዋል። ከድርጅቱ ምሥረታ በፊት የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ቆይተዋል፤ ለምሳሌ በጋራዥ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ሠርተዋል።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በብዛት የሚያመርታቸው ምርቶች እጅ የማይዙ ምርቶች ሲሆኑ፤ እነዚህም ምርቶች እንደ በር እና አልጋ የመሳሰሉ የምርት ውጤቶች ናቸው። እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ የብረት ሥራዎችን ሲመጡ አብሮ ይሠራል፤ ለምሳሌ አልጋዎች እና የቢሮ እቃዎች ላይ አብረው የሚመጡ የብረት ሥራዎችን ይሠራል። ይህ ድርጅት አንድ የሶፋ ሴት በሁለት ሳምንት የማውጣት አቅም አለው፤ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ስልሳ በሮችንም እንዲሁ የማምረት አቅም አለው። የድርጅቱ መሥራች ልምድ እና መሠረታዊ ክህሎቶችን ያካበቱት በሥልጠና እና በጊዜ ሂደት ከልምድ በመማር ነው። ዮብ ፈርኒቸር የአራት ፎቅ ሕንጻ በር እና መስኮት አምርቶ እና ገጥሞ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የማስረከብ አቅም አለው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ መጠን በከፊል

  • አንድ ሜትር ከሃያ አልጋ ከሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር እስከ አሥራ አምስት ሺህ ብር ድረስ ያቀርባል።
  • በሮችን ከሰባት ሺህ ብር ጀምሮ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ድረስ ለገበያ ያቀርባል።

ይህ ድርጅት ለሦስት ቋሚ እና ለሁለት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ሲመሠረትም በስድስት ሺህ ብር ካፒታል ሲሆን አሁን ወደ ሶስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ደርሷል። በመሀል የሆነ ችግር አጋጥሞት ነው እንጂ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻል ነበር ብለዋል አቶ ዮናስ። በዚህም ችግር ምክንያት ከዜሮ እንደ አዲስ ሊጀምሩ ችለዋል፤ ነገር ግን ሲጀምሩም ከምንም ስላልነበረ አልከበዳቸውም እንደውም ከበፊቱ ቀሏቸው ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ እንደ አዲስ ሲጀምሩት ደንበኞች አሉ፣ ሥራው እንዴት መሠራት እንዳለበት ያውቁታል። ስለዚህ ይህ ነገሮችን አቅሎላቸዋል። ተስፋ ሳይቆርጡ መሥራታቸው አሁን ላሉበት ደረጃ ዋናው ተጠቃሽ ምክንያት ነው።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በሰው በሰው እና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ነው። አቶ ዮናስ አሁን ላይ በጨረታዎች ላይ ለመሳተፍ ዝግጅታቸውን እየጨረሱ ነው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ከእነሱ ድርጅት ጋር የሚሠሩ ሰዎች ሥራውን በጨረታ በማሸነፍ ነው እያመጡ ለእነ ዮናስ የሚሠጧቸው። ስለዚህ ራሳቸው ቢሠሩት ደግሞ በጣም ውጤታማ እንደሚሆኑ ስለሚያምኑ ወደ ጨረታ መግባት አስፈላጊ እንደ ሆነ አምነውበታል። “እኛ ራሳችን ብንጫረት ደግሞ በጣም ማደግ እንችላለን” ብለዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ነበሩት፤ አንዱ ብዙ ሥራ አይመጣም ነበር ። ሰው ቤቱ ብዙ የሚያሳስበው ነገር ስለነበር ለፈርኒቸር ሥራ ቅድሚያ አልሠጠም ነበር፤ የተለያዩ ጥሬ እቃዎች እጥረት ስለነበር ሥራ ለመሥራት በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። ሥራም ሲሠራ የነበረው ገባ ወጣ አይነት ነው ድርጅቱ እንዳይዘጋ ብቻ። በዚህም አጋጣሚ በማስተር ካርድ የመጣ የኮቪድ ብድር አገልግሎት በመውሰድ ድርጅቱ የኮቪድ ጊዜ ለማለፊያ ተጠቅሞበታል።

ምክር እና እቅድ

አዲስ ወደ እንጨት ሥራ ለሚገቡ ምክር “ሥራው ቀላል አይደልም ሙሉ ጊዜ ይፈልጋል፤ ነገሮችን የሚጀምሩበት አቅም ወሳኝ ነው፤ ይህም አስፈላጊ ማሽኖችን ይዞ መጀመር ግዴታ ነው። ምክንያቱም ጊዜ የውድድር ስለሆነ። እያንዳንዱን ሰዓት በአግባቡ መጠቀም እና ብክነትን በተቻለ መጠን መቀነስ ወይም ማስቀረት በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ አልጋ ሲሠራ የሚተርፉትን አጫጭር ጣውላዎች ለኮመዲኖ በማስቀመጥ መሥራት አለባቸው። ሥራው ብዙ ትኩረት ይፈልጋል፤ ቀጥሎ ደግሞ አቅም ያስፈልጋል ምክንያቱም ትዕዛዝ ሲመጣ የሚሰጠው ቀብድ በጣም ትንሽ ነው። ለምሳሌ የአንድ መቶ ሺህ ብር ሥራ ቢመጣ ቀብድ ሃያ ሺህ ብር ቢሆን ጥሬ መግዣ ገንዘብ ከሌለው አስቸጋሪ ነው ይህ ደግሞ ያጠፋቸዋል፤ ስለዚህ ጥሩ አቅም አስፈላጊ ነው” ብለው ምክራቸውን አስተላልፈዋል የድርጅቱ መሥራች።

ድርጅቱ ወደ ፊት በ2merkato.com በኩል የሚሠጠውን የጨረታ አገልግሎት ለመሳተፍ እና አንዳንድ አስፈላጊ ማሽኖችን ለመጨመር እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …