መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ኤን ደብሊው አልሙኒየም እና ብረት ሥራ

ኤን ደብሊው አልሙኒየም እና ብረት ሥራ

ኤን ደብሊው አልሙኒየም እና ብረት ሥራ የተመሠረተው በ 2004 ዓ.ም. በሁለት መሥራች አባላት ነው። ድርጅቱ ሁለት ዓመታት በጥሩ ሁኔታ  ምርት ሲያመርት መቆየቱን የድርጅቱ መሥራች አባል የሆኑት አቶ ነጋሽ ወንድምአገኝ አስረድተዋል። የአቶ ነጋሽ በሙያው ተገቢ የሥራ ልምድ መኖር፣ እንዲሁም ከድርጅቱ ምሥረታ በፊት  የነበራቸው የስድስት አመት የሥራ ልምድ እና የቀለም እውቀት ተደምሮ ድርጅቱ ጠንካራ እና ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል።

 

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

 • የሕንጻ የውስጥ እና የውጭ መወጣጫ ደረጃዎች
 • የውስጥ እና የውጭ በሮች
 • የቤት እና የቢሮ ወንበር እና ጠረጴዛ
 • የመብራት ተሸካሚ ፖሎች
 • የትምህርት ቤት መቀመጫ ወንበሮች
 • የሕንጻ በር እና መስኮት አልሙኒየም ሥራ

ምሥረታ፣ ዕድገት እና መስፋፋት

ድርጅቱ ሥራ የሚያገኘው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ነው፤ ለምሳሌ ከወረዳ በሚመጡ ሥራዎች (ትስስሮች)፣ ክ/ከተማ የሚያወጣቸውን ጨረታዎች በመከታተል፣ ከኮንትራክተሮች ጋር ስምምነት በመግባት እና በሰው በሰው የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል።

ድርጅቱ የወረዳ ወይም ቀበሌ ሕንፃ የሚመስል አራት ፎቅ ሕንጻ መወጠጫ ደረጃ በአንድ ቀን የማጠናቀቅ አቅም አለው። እንዲሁም በቀን ሠላሳ በሮችን የማምረት አቅም አለው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለመኖሪያ የሚያገለግሉ ሥራዎችን ከአምስት ቀን እስከ ዐሥራ አምስት ቀን ድረስ እንደ ሥራው አይነት ጨርሶ ማስረከብ ይችላል። የድርጅቱ አቅም በመጠንከሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በሙያው ለሚሠለጥኑ ተማሪዎች የአፕረንቲስሺፕ (apprenticeship) አገልግሎት በመስጠት በሙያው ብቁ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎችን በማፍራት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

ድርጅቱ ሲጀመር ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ነበሩ፤ ለምሳሌ የመሥሪያ ቦታ አለማግኘት፣ ሥራዎችን ተጠናቀው ክፍያ በጊዜው አለመቀበል – ለምሣሌ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ የሰባት ፎቅ ሕንጻ ሥራ ሠርተው ክፍያ ገና አልተቀበሉም። ነገር ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ለእነዚህ ችግሮች መፍትኄ ሊያገኙ ችለዋል፤ የቦታ ችግሩን በወር በዐሥራ አምስት ሺህ ብር ቦታ በመከራየት እንዲሁም የክፍያ ጉዳይ አቅማቸው እየጎለበተ ሲመጣ ቅድመ ክፍያ በመውሰድ ሥራዎችን በመሥራት ችግራቸውን መፍታት ችለዋል። የድርጅቱ አባላት የስድስት አመት የሥራ ልምድ በጣም በጣም ብዙ ችግሮችን በሚገባ ለመቅረፍ እና ለወደፊቱም እንዲዘጋጅ አስችሎታል። ድርጅቱ በአጠቃላይ ለስምንት ሠራተኞች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ እድል ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ድርጅቱ ሲመሠረት በሃያ ሺህ ብር ካፒታል ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ አንድ ሚሊዮን  ብር (ብር 1,000,000) ካፒታል እና ብዙ ደንበኞችን ማፍራት ችሎአል። የሚሠራቸው ሥራዎች ጥሩ ስለሆኑ በሰው በሰው ብዙ ሥራዎችን ማግኘት ችሏል። በተጨማሪም የድርጅቱ ሠራተኞች መኪና እና ቤት መግዛት ስለቻሉ የግል ህይወታቸውን ለማሻሻል ችለዋል።

የኮቪድ ተጽዕኖ

ኮቪድ ከባድ ተፅዕኖ አላደረገም። እርግጥ እንደ ሁሉም ሰው ጉዳት ነበረው፣ የተቀነሱ ሠራተኞችም ነበሩ። ነገር ግን ድርጅቱ እየሠራው የነበረው ሥራ ስለነበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ በመጠቀም በጥንቃቄ ሲሠራ ነበር።

ምክር እና እቅድ

አዲስ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ሰዎች

 • ለሰው እና ለሥራው ጥሩ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል
 • በምንም አይነት ነገር ቢሆን ደንበኛን ማክበር ለቢዝነስ ማደግ ዋና መሰረት ነው
 • በሥራ ሰዓት ሥራ ብቻ
 • ከተቻለ ከምንም አይነት ሱስ የፀዳ መሆን አለበት
 • ሥራ ቦታ ላይ መናናቅ መኖር የለበትም፤ መከባበር መቻል አለበት
 • ደንበኛ እንዴት መያዝ እንደሚችል ማወቅ አለበት

አንድ ሰው ሥራው እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ አለበት። ሥራውን በሚገባ ካላወቀ ሠራተኛን በደንብ ማዘዝ አይችልም፣ የንብረት ብክነት ይኖራል። ደንበኛም ይማረራል፣ ተመልሶ አይመጣም ቀጥሎም ደንበኛው ሲቀር እሱ የሚያመጣቸው ሥራዎች አብረው ይቀራሉ። ሌላው በሥራ ሰዓት ጫት፣ ሲጋራ የመሳሰሉ ሱሶችን በሚገባ መተው። በሥራ ሠአት እነዚህ ነገሮች የሚያደርግ ከሆነ ደንበኛውም የደንበኛ አመኔታ ይቀንሳል። ጫት ይቅምበት ይሆን፤ ሥራውን ትቶ ጫት ሲቅም ነው የሚውለው እሱማ አይሠራም የሚል ዕሳቤ ስለሚኖረው በሥራ ሰዓት ምንም አይነት ሱስ አያስፈልግም። ቢቻል ሁል ጊዜ ከሱስ የፀዳ ቢሆን ይመረጣል።

የድርጅቱ ትልቁ ችግር የቦታ ችግር በመሆኑ ለወደፊት ቦታ በማግኘት የሚሠራቸውን ሥራዎች ለማስፋት አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

በ2merkato.com ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች የተዘጋጀውን የከፍታ ፖርታል ቴሌግራም ቻናልን በመጠቀም መረጃ ለመከታተል እና ምርቱን በማስተዋወቅ ለመጠቀም አቅዷል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …