እንስራ የሸክላ ማዕከል ለሸክላ ሠሪዎች ምቹ የሥራ ቦታ መሆኑን የጉለሌ ክ/ከተማ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ገለጸ፡፡
የጉለሌ ክ/ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀይለማርያም አባይነህ እንደተናገሩት የከተማው ከንቲባ፣ የክ/ከተማ አስተዳደር እና የሚመለከለታቸው የቢሮ ኃላፊዎች ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ማእከሉን በሚመች መልኩ በመገንባት ለ23 ሸክላ ሠሪ ኢንተርፕራይዞች ያስረከቡ ሲሆን ማዕከሉም የሸክላ ማቃጠያ፣ የምርት ማሳያ ቦታ፣ የህጻናት ማቆያ፣ የእናቶች ማረፊያ ክፍል እና ካፍቴሪያ ክፍሎች እንዳሉት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በማእከሉ ያገኘናት የሰላምና ፍቅር ሸክላ ማህበር አባል ወጣት ገነት አሰፋ እንደተናገረችው በፊት ሸክላ ያመርቱበት ከነበረበት ቦታ ማእከሉ ሲነጻጸር ለሥራ ጥሩ መንፈስ ያለው የግቢ ሁኔታ መፈጠሩ፣ ጤናን ለመጠበቅ ምቹ የሆነ አካባቢ መሆኑ እንዲሁም አጠቃላይ የግቢው ጥበቃ ሥራውን ለመስራት ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው በመናገር ግብዓቱም ራሳቸውን ችለው ከተደራጁ ማህበራት ጥሬ እቃ እንደሚረከቡ ገልጻለች፡፡
በቀጣይም የሸክላ ውጤቶቹን ሽያጭ ከሀገር ውስጥ ገበያ ትስስር በዘለለ ለውጪ ገበያ አቅርቦት እና ትስስር እንዲኖር የሚመቻችላቸው ሲሆን ሥራውን ለማዘመን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት፣የገበያ ትስስር በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ መንግስታዊ ድጋፎች በመስጠት እገዛ እንደሚደረግላቸው አቶ ሀይለማሪያም አባይነህ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ማህበረሰቡ ስለ ሸክላ ሠሪዎች ያለውን የተዛባ አመለካከት በመቀየር፣ ለቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ማዕከሉን በመጎብኘት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ሲሉ አቶ ሀይለማሪያም አባይነህ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የዜና እና የምስል ምንጭ፦ የአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የፌስ ቡክ ገጽ