መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / የድር እና ማግ ሥራ – ሪል ድር ማጠንጠኛ

የድር እና ማግ ሥራ – ሪል ድር ማጠንጠኛ

ሪል ድር ማጠንጠኛ የተመሰረተው 2005 ዓ.ም ሲሆን መስራቾቹም ሦስት  አባላት ናቸው። ድርጅቱ ሁለት ዓመታት ያህል በጥሩ ሁኔታ ሲያመርት መቆየቱን የድርጅቱ መስራች አባል የሆነው አቶ ሀብታሙ አስረድቷል። የአቶ ሀብታሙ በሙያው ተገቢ የሥራ ልምድ መኖር፣ እንዲሁም የእህቱ የቴክስታይል ተማሪ መሆን እና በኳሊቲ ኮንትሮል በፋብሪካ ውስጥ ለረጅም

ግዜ መሥራት ከባለቤቱ የሒሳብ ሥራ ክህሎት ጋር ተደምሮ ሪል ድር ማጠንጠኛ ሲመሰረት ከነበረው አስር ማሽኞች እና አስር ሠራተኞች አሁን ላለው ሰላሳ ማሽን እና አርባ አምስት ሠራተኞች መድረስ አስችሎታል።

አቶ ሀብታሙ የድር ማጠንጠኛ ዘርፍን ሊመርጥ የቻለበትን ምክንያት ሰዎች በድር ምርት ዘርፍ ችግሩ እንዳለ በተደጋጋሚ በመስማቱ እና አሳሳቢነቱን መገንዘቡ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የእህቱ በሙያው እውቀት እና የሥራ ልምድ መኖር ሥራው ሲጀመር ሠራተኛ በማሰልጠን እና የምርት ጥራት በመቆጣጠር እህቱ፤ እንዲሁም በሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥራ ባለቤቱ፣ እሱ ደግሞ የጥሬ እቃ አቅርቦት እና ገበያ ጥናት ሥራዎችን ተከፋፍለው መሥራታቸው ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ እንዳስቻለው ይናገራል።

ሪል ድር ማጠንጠኛ የሚሰጠው አገልግሎት ጥሬ ዕቃን (ክር) በኪሎ በመረከብ አጠንጥኖ ክሩን ወደ ቱባ (ድር እና ማግ) የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መቀየር ነው። ይህንንም ድር የሆነውን ምርት ለተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ለሚሠሩ አምራቾች ያስረክባል እንዲሁም ለማንኛውም አገልግሎቱን ለሚፈልግ ደንበኛ አገልግሎቱን ይሰጣል።

ምስረታና ዕድገት

ሪል ድር ማጠንጠኛ ከተመሰረተ ስምንት ዓመት ሆኖታል። ድርጅቱ ሲመሰረት ሁኔታዎች ከባድ ነበሩ ለምሳሌ “በወቅቱ ከነበረው የቤት ኪራይ ከባድ  ነበር፤ ቤቱ ከጣራው ዝናብ ከመሬት በኩል ጎርፍ ያስገባ ነበር። ሥራው በራሱ የተስተካከለ የአየር ሁኔታ ላይ እንኳን በጣም የሚያስቸግር በመሆኑ በተለይም ክሩ አየሩ ከቀዘቀዘ በከፍተኛ ሁኔታ ይበላሻል። ይህ ደግሞ ጥራቱ ላይ ችግር በመፍጠር እንቅፋት ይሆናል” ሲል አቶ ሀብታሙ አስረድቷል። ከላይ እንደተገለጸው ሥራው ሲጀመር በአስር ማሽኖች እና በአስር ሠራተኞች በመቀጠልም በሃያ ሠራተኞች ለረዥም ጊዜ ሲሠራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሠራተኞቹ አርባ አምስት ያህል ደርሰዋል። ድርጅቱ የያዘው የሰው ሀይል ብዛት ታይቶ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከመንግስት ሼድ ማግኘት ተችሏል። ድርጅቱ ሼድ ሲያገኝ አስር ተጨማሪ ማሽኖችን የገዛ ሲሆን በሼድ ላይ ሆኖ በማሽን ሊዝ ተጨማሪ አስር ማሽን አስገብቷል።

ሪል ድር ማጠንጠኛ ድርጅት አሁን ላለበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት የነበሩ ዋና ዋና ችግሮች አመቺ የስራ ቦታ አለመኖር እና የማቴሪያል (ጥሬ እቃ) አቅርቦት እጥረት ናቸው። የጥሬ እቃውን ችግር የሚፈታበት ላይ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ችግሩን ለመፍታት እንደሞከሩ እና የቦታው ችግር  ደግሞ ሼድ በማግኘታቸው እንደተፈታ አቶ ሃብታሙ አስረድቷል።

በሥራው ሂደት  ያልታሰበ ነገር ግን ድርጅቱ ተምሮ ያለፈበት ነገር ቢኖር እቃ ሲረከብ ስለ እቃ ርክክብ ሁኔታ፣ ስለ ማሽን ጥገና፣ ስለሂሳብ አያያዝ፣ ደንበኛ አያያዝ፣ የምርት ጥራት፣ የሠራተኛ አያያዝ  ከሚገጥሙ ችግሮች በመነሳት በመማር እዚህ ደረጃ መደረሱ ከፍተኛ እርካታ እንደፈጠረ አቶ ሃብታሙ ይናገራል።  ስለሆነም ሥራ ላይ ያልታሰቡ ችግሮች እንደሚኖሩ አውቆ መዘጋጀት ያስፈልጋል በማለት አቶ ሀብታሙ ተሞክሯቸውን አካፍሏል። “ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ለማንኛውም ሥራ መሠረታዊ እውቀት መኖር ግድ ነው፤ ለምሳሌ የኛ ሥራ በጣም ጥንቃቄ ይጠይቃል ከትንሹ ብንነሳ ፣ የክር ኳሊቲ ማወቅ አለብህ፣ ተገዝቶ ሲመጣ ራሱ ፖሊስተር ወይስ ኮተን ነው ወይ የሚለውን ለመለየት እውቀት ያስፈልጋል።”

ሪል ድር ማጠንጠኛ ሥራውን ለማቀላጠፍ አዲስ አበባ በሚገኝ ወጣት የፈጠራ ችሎታ የተሠራ ማሽን መግዛት ግዜ እና ገንዘብ ቆጥቦልናል ይላል። “ለምሳሌ ሌላ ቦታ እንድ ክር ነው የሚያደሩት ይህ ማሽን ግን አርባ ክር ነው የሚያደራው ይህ ደግሞ ትልቅ ጥቅም ነው። የተሻሻለ ቴክኖሎጂን መጠቀም የምርት ጥራትና ብዛት በመፍጥር የሥራ ሰዓት ይቆጥባል፣ ለሰራተኛ ቀላልና ተወዳጅ ነው፤ ስለዚህ ሥራው እያማረ እየወደድከው ትሔዳለህ። እኛ ራሱ እሁን ላለን ማሽን የክር ማሻሻያ ለመስራት እያሰብን ነው ክር ሲበጠስ ራሱ ማሽኑ ምልክት መስጠት ቢችል ብለን እየሰራን ነው። ይህ ስናስተካክል ትልቅ እርምጃ ወደፊት መራመድ ይሆናል” ሲል ስለዚህ በተቻለ መጠን የተሻሽለ ተክኖሎጂን መጠቀም ጥሩ እንደሆነ አቶ ሀብታሙ ይመክራል።

የኮቪድ ተፅእኖ

የኮቪድ ተፅዕኖ ከባድ እንደነበር አቶ ሀብታሙ በሚከተለው መንገድ አስረድቷል። “በፊት የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር ነበር አሁን ደሞ ኮቪድ ሲመጣ ይበልጥ ባሰ፤ ምክያቱም ጥሬ እቃ ይገባ የነበረው ከቻይና እና ከቬትናም ነበር። ለዚህም ችግር ሪል ድር ማጠንጠኛ አንደ መፍትሔ የወሰዳቸው ነገሮች  አንደኛ በፊት የማይጠቀሙባቸውን ማቴሪያሎች መጠቀም መጀመር፣ የተጣሉ እና የተበላሹ ክሮች እንዲሁም ትርፍ ተብለው የተቀመጡ ተረፈ ምርቶችን ሥራ ላይ ማዋል፣ አስቸጋሪ ክሮች የሚባሉትንም በሚገባ በማስተካከል ለችግሩ መፍትኄ በማበጀት ምርት ሊቀጥል ችሏል” ሲል አቶ ሀብታሙ ገልፆአል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት፣ ምክር

ሪል ድር ማጠንጠኛ ቢዝነስ ማስተዋወቂያ መንገድ አንድ እና አንድ ነው እሱም ሥራን በጥራት መሥራት ነው ብሎ የሚያምን ድርጅት ነው። ይህም ምርታቸውን በጥራት በማምረታቸው ከአንድ በጅምላ ከሚወስድ ደንበኛ ወደ አራት በጅምላ ወደሚወስዱ ደንበኞች አድጓል።

“አዲስ ቢዝነስ ሲጀመር ባለሙያዎችን ማማከር ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል” ይላል አቶ ሀብታሙ። ለምሳሌ ሪል ድር ማጠንጠኛ ከማሽን ጥገና፣ አስተዳደር ዙሪያ የተጠቀማቸው እና እየተጠቀማቸው ያሉ ባለሙያዎች እንዳሉ ገልጿል። ሪል ድር ማጠንጠኛ የቀጠራቸው ሠራተኞች በቅጡ የሠለጠኑ ባለመሆናቸው ለነሱ ሥልጠና እንዲሰጡ ባለሙያዎችን ይጠቀማል። ለክሩም አንዳንዴ ክሩ ሂደቱን ሳይጨርስ ስለሚመጣ ክሩ ተነክሮ ወደ ሚገባው ጥራት እንዴት መመለስ እንዳለበት ባለሙያ በማማከር ሥራው በተሳካ ሁኔታ ሊሄድ እንደቻለ አቶ ሀብታሙ ጨምሮ አስረድቷል።

ሪል ድር ማጠንጠኛ ለወደፊት የሚያመርተውን ምርት ለአምራች ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን በማምረት ቀጥታ ለተጠቃሚ ለማድረስ አቅዶ እየሠራ ነው።

አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ  በከፍታ በኩል የሚሰጠውን የ2merkato አገልግሎት መጠቀም ባያስፈልጋቸውም፤ ደንበኞች ሲያሰፉ ግን ለመጠቀም አቅደዋል።

“አንድ ስራ ወይም ቢዝነስ ለማደግ ዋና መነሻው ከዝቅተኛ ሁኔታ መነሳት ዝቅ ብሎ መሥራት ዋናው እና ወሳኝ ነው ሁለተኛ ከዓይን የራቀ ከሥራ እየራቀ ይመጣል ነው። ለምሳሌ ከሠራተኛ ጋር ያለው ግንኙነት በክብር ቤተሰባዊ ሲሆን ሰራተኛ ጥሩ ስሜት እንዲሰማችው የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህ ደሞ ሥራውን በፍቅር እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ ማንም ሰው ሥራ ሲጀምር ዝቅ ብሎ መሥራት መቻል አለበት ሲል አቶ ሀብታሙ ምክር አስተላልፏል። ማንኛቸውም አዲስ ቢዝነስ የሚጀምሩ ሰዎች በውስጣቸው የሚወዱትን ሥራ መሥራት፣ ማየት፣ መሞከር እና የሚያስከፍለውን ዋጋ መክፈል ሥራቸውን ያሳድጋል። ሥራን በውል ማወቅ፣ መግባባት፣ ገንዘብ አያያዝ እና ሥራ ክፍፍል ላይ መግባባት በጣም አስፈላጊ ነው። ከመነሻ ካፒታል በላይ የቢዝነስ ጀማሪው ፍላጐት እና ልብ አስፈላጊው ነገር ነው። በአንድ ማሽን መጀመር ይችላል ስለዚህ ዋናው ፍላጎት እና ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን ነው” ሲል አቶ ሀብታሙ ይመክራል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …