መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / “በጠባብ ማምረቻ በሰፊ ጭንቅላት ነው እየሠራን የምንገኝው” አሹ ኢንተርናሽናል የፈርኒቸር ዓለም
ashu-international-furniture

“በጠባብ ማምረቻ በሰፊ ጭንቅላት ነው እየሠራን የምንገኝው” አሹ ኢንተርናሽናል የፈርኒቸር ዓለም

አሹ ኢንተርናሽናል የፈርኒቸር ዓለም ድርጅት የተመሠረተው በአቶ አሸናፊ ንጉሴ በግል ኢንተርፕራይዝነት ነው። አቶ አሸናፊ ድርጅቱን በ2002 ዓ.ም ከመመሥረታቸው በፊት በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ በብዙ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ሲሠሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ሥራዎችን ቢሠሩም በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥን የመሠለ ነገር አንደሌለ በመገንዘብ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በማኑፋክቸሪንግ ሥራ ላይ ሊሠማሩ ችለዋል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አሹ ኢንተርናሽናል የፈርኒቸር ዓለም ድርጅት አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል። ድርጅቱ ባካበተው የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ እና በውስጡ በያዘው የሠለጠነ ብቁ የሰው ኃይል ከውጭ ሀገር የሚመጡ የፈርኒቸር ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በጥራት በማምረት ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬን ወጪ በማስቀረት ትልቅ አሥተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።

የሚያመርታቸው ምርቶች

  • ጠረጴዛዎች
  • ሶፋዎች
  • የቤት እና የቢሮ እቃዎችን ያመርታል

አቶ አሸናፊ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ሥራ ሊገቡ የቻሉት ዋናው ድህነትን ለማሸነፍ ሲሆን ይህንንም ለማሳካት የነበራቸውን አልጋ እና ቁም ሳጥን በመሸጥ በአምስት ሺህ ብር ካፒታል ነበር ድርጅታቸውን የመሠረቱት። የፈርኒቸር ሥራ በባህሪው የሚቆም ሥራ አይደለም የግድ ራስን ከዘመኑ ጋር ማሳደግ ያስፈልጋል፤ እሳቸውም ኢንተርኔት በመጠቀም ቀን በቀን አዳዲስ እና የተለያዩ ዘመናዊ ምርቶችን በማየት አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ጥረት ያደርጉ ነበር። አንድን አዲስ ምርት እንዴት ነው ከሀገራችን አኗኗር ጋር አግባብቼ ማቅረብ የምችለው ብለው እያሰቡ፤ እና እራሳቸው እያሳደጉ በመምጣታቸው ድርጅቱ ጠንክሮ እየሠራና እያደገ ይገኛል።

አቶ አሸናፊ ትልቅ የፈጠራ ችሎታ አላቸው። በዚህም የፓተንት ባለመብት ናቸው። የሚያመርቷቸው ምርቶችን የእሳቸውን ፈጠራ በመጨመር ነው የሚሠሩት፤ ለማኅበረሰቡ የሚመች አድርገው ያቀርባሉ። ከፈጠሯቸው ምርቶች መካከል አንድ ዘጠኝ ዓይነት የተለያዩ አገልግሎቶች መስጠት የሚችል፣ ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር የሆነ ሶፋ ሠርተው ተሸልመዋል። እንዲሁም ኮንዶሚኒየም ሕንጻዎች (ልደታ፣ የካ አባዶ እና ኮዬ ፈጬ) ሲመረቁ የተወሰኑ ብሎኮችን ፈርኒሽ የማድረግ ሥራ በመሥራት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

ድርጅቱ ምርቱን በቴሌግራም እና ፌስቡክ እያስተዋወቀ ይገኛል። እንዲሁም ደግሞ የራሱ ምርት ማሳያ ሱቅም አለው።

ድርጅቱ ዐሥራ ስድስት ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ አሁን ራሱን እያጠናከረ ይገኛል። ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞም በአሁኑ ጊዜ ትልቅ የድርጅቱ ችግር የቦታ ጥበት ነው። “በጠባብ ማምረቻ በሰፊ ጭንቅላት ነው እየሠራን የምንገኝው። ያለው ቦታ ከዚህ በላይ ሠራተኛም መያዝ አይችልም መንግሥት ሥራችንን አይቶ ቦታ ቢሰጠን ድርጅቱ ይበልጥ ማደግ ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል የድርጅቱ መሥራች።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ የራሱን ችግር ቢያመጣም አቶ አሸናፊ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት አልፈውታል፤ ለምሳሌ የፀረ ኮሮና ቫይረስ ኬሚካል መርጫ መሣሪያ፣ ከእጅ ንክኪ የጸዳ የእጅ መታጠቢያ ሠርተዋል።

 

ምክር እና እቅድ

አንድን ቢዝነስ የሚጥለውም የሚያነሳውም ባለቤቱ ነው። አቶ አሸናፊ ቻይና፣ ቱርክ እና ጀርመን ሀገር ያሉ ባለሙያዎች የሚጽፏቸውን ጽሑፎች በማንበብ ዲዛይኖችን እንዲሁም ቴክኒካል ነገሮችን መማር ችለዋል። እሳቸው ራሳቸውን በስልካቸው እና ኮምፒውተራቸውን በመጠቀም ነው የሚያሳድጉት ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

“መንግሥት የሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም አለበት፤ መንግሥት ከውጭ እያስመጣ የግሉን ሴክተር የሀገር ውስጥ ተጠቀም ቢል አይሆንም። የሥራ እድል ለመፍጠር አልባሳት የቢሮ እቃዎችን ከሀገር ውስጥ አምራች ቢገዛ እና ሀገር ውስጥ የማይሠሩ ነገሮችን ቢያስገባ ለኢንተርፕራይዙ ሥራ እድል ይፈጥራል እና ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ያስቀራል” ብለዋል አቶ አሸናፊ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ጎደለ ብሎ መጠየቅ፣ በዛ ሥራ ላይ ማየት እና መፈተሽ፣ የጎደለው ላይ መሠማራት ይችላል። ሰው ገንዘብ ከመያዝ ይልቅ እቅድ ያያዝ፤ ደግሞ እምነት ፣ድፍረት እና ጥበብ አስፈላጊ ናቸው። የማንም ሰው ካፒታል መጀመሪያ ከውስጡ ነው የሚጀምረው። ሥራ ለመጀመር ሃብታም መሆን ወይም ብዙ ገንዘብ መበደር አያስፈልግም ብለው ምክራቸውን አሥተላልፈዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …