መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / መተውን እንደ አማራጭ አልወስድም – ረሒማ ባልትና
ባልትና

መተውን እንደ አማራጭ አልወስድም – ረሒማ ባልትና

ረሒማ ባልትና የተመሰረተው በወ/ሮ ረሒማ ንዳ 2007 ዓ.ም. ላይ በግል ኢንተርፕራይዝነት ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የባልትና ውጤቶችን ከደንበኛ ትዕዛዝ ተቀብሎ በማምረት እንዲሁም ሂደታቸውን የጨረሱ የባልትና ውጤቶችን በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ አገልግሎት ይሰጣል።

ረሒማ ባልትና የሚያመርታቸው ምርቶች

  • አንደኛ ደረጃ በርበሬ
  • አንደኛ ደረጃ ምጥን ሽሮ
  • አንደኛ ደረጃ ነጭ ሽሮ
  • አንደኛ ደረጃ ሚጥሚጣ
  • አንደኛ ደረጃ አጃ
  • አንደኛ ደረጃ በሶ
  • አንደኛ ደረጃ ቆሎ እና ዳቦ ቆሎ
  • አንደኛ ደረጃ ኩኪስ እና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች

ምሥረታና ዕድገት

ወ/ሮ ረሒማ እንዴት ወደ ባልትና ሥራ እንደተሰማሩ ሲያስረዱ የቤት እመቤት ነበሩ፤ መሥራት ስላለባቸው እና የባልትና ሥራን ጠንቀቀው ስለሚያውቁ ወደ ባልትና ሥራ ገብተዋል። እንዲሁም አንዳንዴ ከወረዳው ቢሮ የሂሳብ አያያዝ ሥራ እና የባልትና ሥራ እንዴት መሠራት እንዳለበት፣ ሥራው በሚገባ ስለሚታወቅ ብቻ ሳይሆን እንዴት ባልትና በተለየ መልኩ ለገበያ እንዲመች አድርገው ማቅረብ እንደሚችሉ የሚረዱ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። የድርጅቱ የማምረት አቅም እንደየምርቱ ቢለያይም በቀን እስከ ሃምሳ ኪሎ ሽሮ፣ በርበሬ፣ በሶ የማምረት አቅም አለው።

ወ/ሮ ረሒማ ባልትና ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ሌሎች ሥራዎችንም ሞከረው ነበር። አትክልት መሸጥ ሞክረው ነገር ግን ብዙ ገዢ ካልመጣ ስለሚበላሽ ኪሳራ ሲሆንባቸው ወደ ባልትና መስክ ተሰማርተዋል። በዚህም መልካም ነገር አይተውበታል፤ ምክንያቱም የባልትና ውጤቶች የሚበላሹ አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪ ጊዜ የሌላቸው ሰዎች (ራሳቸው ማዘጋጀት የማይችሉ ሰዎች) ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የባልትና ውጤት ተፈላጊነት ከአትክልቱ የተሻለ ነው ብለዋል።

ወ/ሮ ረሒማ ስለባልትና ሥራ የሚከተለውን ብለዋል “የባልትና ሥራ ትጋት ይፈልጋል። በጣም ከባድ ነው ነገር ግን ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ላለማቋረጥ ብዙ ዋጋ ከፍዬበታለሁ። መተውን እንደ አማራጭ አልወስድም፣ አላስብምም፤  ለዚህም ነው ረሒማ ባልትና ውጤታማ ሊሆን የቻለው።”

የኮቪድ ተጽዕኖ

ኮቪድ ከባድ ተፅዕኖ ነበረው፤ በነበረው የእንቅስቃሴ መቆም አቅርቦት እንዳይኖር አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ሰው መጥቶ መግዛት አቁሞ ነበር። ይህ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ አሁን ደግሞ ያለው የምርቶች ዋጋ መጨመር ለሥራው በጣም አደገኛ ተግዳሮት ነው።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ድርጅቱ ሲጀመር በመነሻ አምስት መቶ ብር (500) ነበር አሁን ባለው ሁኔታ ሀምሳ ሺህ ብር (50,000) ካፒታል ደርሷል። አንድ ጊዜ ከብድር እና ቁጠባ ተቋም ብድር በመበደር ሙሉ ከፍለው (መልሰው) ጨርሰዋል። ብድር ላይ ያለው ችግር ደግሞ ወለድ እና ዋስ የሚባለው ነገር ነው። ይህ አሠራር ቢሻሻል ጥሩ ነው፤ የምሠራው ሥራ ታይቶ በዛ አማካኝነት ብድር የሚመቻችበት መንገድ ቢኖር የሚል አስተያየት አክለዋል።

ድርጅቱ ምርቱን ባዛር ላይ አንዳንዴ ያስተዋውቃል፤ የባዛር ትልቁ ጥቅም ልምድ እና ተሞክሮ ለመቀያየር በጣም ይጠቅማል። ለምሳሌ ይህን እንዲህ ብሠራው ይጠቅማል ለካ ይህም ሥራ እንዲህ ይሠራል የሚሉ ነገሮችን ለመነጋገር በጣም ተቃሚ ነው።

በ2merkato የሚሰጠውን የከፍታ አገልግሎት ተደውሎላቸው ያውቁታል። አሁን ያላቸው አቅም ግን ዝቅተኛ ስለሆነ አቅማቸው ሲጠነክር ለመጠቀም እንደሚያስቡ ገልጸዋል። የቴሌግራም ቻናሉን ግን በልጆቻችው አማካኝነት እከታተላለሁ ብለዋል።

ምክር እና እቅድ

ረሒማ ባልትና ወደ ፊት ከትልልቅ ድርጅቶች ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ አላቸው። በስልክ ከውጭ ተደውሎላቸው የኔ ሥራ ያን ያህል አይደለም በሚለው ትተውታል። እንደእቅድ ሥራውን ሰፋ አድርጎ ተረካቢ ወደ ውጭ በማግኘት ሥራውን ማስፋፋት ነው አላማቸው።

አዲስ ለሚገቡ  የሚሰጡት ምክር “የባልትና ሥራ ከባድ ነው። ለሰው እንደምግብ የሚቀርብ እንደመሆኑ ሲገቡበት በቅድሚያ ራሳቸው ሙያውን መቻል አለባቸው፤  ቀጥሎ የሚያቀርቡትን ምርት ልክ እንደ ራሳቸው አድርገው በጥራት ማቅረብ አለባቸው።”

የባልትና ውጤቶች ምግብ ነክ ስለሆኑ ትልቅ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ በዚህም ምክንያት ለጥራት ቅድሚያ መስጠት ትልቅ ቦታ ይይዛል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …