መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / አልአዛር እና ሄኖክ እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

አልአዛር እና ሄኖክ እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ አልአዛር ዓለም እና በአቶ ሄኖክ በ1996 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የእንጨት እና የብረታ ብረት ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ሲሆን በነዚህ ሥራዎች ውስጥ ውስጥ የዲዛይን እና ፈኒቸር ሥራዎች ይካተታሉ።

የሚያመርታቸው ምርቶች

  • አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎች
  • የቤት እና የቢሮ እቃዎች
  • በር እና መስኮቶች
  • የኪችን ካቢኔት
  • ቁምሳጥን እና
  • የፐርኬ ሥራዎች

 

 

 

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ አልአዛር ድርጅቱን ሲመሠረቱ ዓላማቸው የነበረው ራስን ለመቻል እና ብሎም አካባቢን ለመቀየር በማሰብ ነው ይህንንም በሚገባ አድርገዋል። ይህን ዘርፍ የመረጡበት ምክንያት ደግሞ ሥራውን ከልጅነታቸው ጀምሮ ከቤተሰብ ጋር በመሆን አብረው እየሠሩ ስላደጉ በሙያው በቂ እውቀት ስላላቸው ነበር። ይህን ሥራ ብንሠራ ያዋጣናል ብለው በአምስት ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የመሠረቱት ድርጅት አሁን አቅሙን በማሳደግ እና በማስፋት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያለው ሲሆን ለአምስት ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።

ድርጅቱ በሃያ ቀን ውስጥ 140 በሮችን በጥራት አጠናቆ የማስረከብ አቅም አለው፤ ይህንም ለማሳካት ባስገባቸው በቂ እና ዘመናዊ ማሽኖች በመጠቀም እየሠራ ይገኛል። ይህ ድርጅት ሥራዎች የሚሠራው በሰው በሰው ሲሆን አብዛኛው የድርጅቱ ሥራዎች የሚያተኩሩት የግለሰብ ቤቶች ላይ ነው። የሚወስዳቸውን ሥራዎች በኮንትራት ወስደው የወሰዱትን ሥራ ጥንቅቅ አድርገው በመሥራት በጊዜ ያስረክባሉ። ለድርጅቱ እድገትም ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረከተው ይህ ነው። ከዚህ በኋላ ሰዎች ሥራውን እያዩ በመነጋገር ይህ ሥራ የማን ነው በማለት ራሳቸው መምጣት መጀመራቸውን የድርጅቱ መሥራች ተናገረዋል። የድርጅቱ መሥራች በሥራው ውጤታማ ለመሆን የዲዛይን ትምህርት ተምረዋል።

ይህ ድርጅት አሁን ያለበት ደረጃ ሲደርስ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም፤ ብዙ ችግሮች ነበሩ። ቀንሰው ነው እንጂ አሁንም የሉም ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ እና የቦታ ችግር፤ ብድር የለም ወይም ለመበደር ኮላተራል ሊኖር ይገባል። በተጨማሪ ብድሩ ሲመጣ ራሱ ከአሥራ ስምንት እስከ ሃያ ፐርሰንት ወለድ አለው እነዚህ ችግሮች በመቋቋም እርስ በርስ በመረዳዳት ነው አሁን ያለበት ደረጃ ሊደርስ የቻለው።

አቶ አልአዛር 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት አገልግሎት በመጠቀም መረጃ እየተከታተሉ ይገኛሉ። ቢሻሻል ያሉት ነገር ለዓይፎን ስልክ ተጠቃሚዎችም የሚሆን መተግበርያ ቢሠራ ነው፤ እሳቸው ምንም የአንድሮይድ ተጠቃሚ አይደሉም። ይሄን እንደ አንድ እክል ይወስዱታል፤ ለምሳሌ ካፌ ላይ ወይም የሆነ ቦታ ሆነው በስልካቸው ነው ያለውን ነገር ማየት የሚፈልጉት፤ አሁን ግን ወይ የሆነ ብራውዘር ተከፍቶ ወይም ግዴታ ቢሮ እስኪገባ ድረስ መጠበቅ አለበት። 

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች ዋጋ በጥቂቱ

  • የመኖሪያ ቤት በሮች በመነሻ ዋጋ፦ ከዐሥራ ሁለት ሺህ ብር ጀምሮ እስከ ሃያ አንድ ሺህ ብር ድረስ
  • የኪችን ካቢኔት፦ በካሬ ከሰባት ሺህ ብር ጀምሮ እንደ ዲዛይኑ እና የተመረጠው ጥሬ እቃ ዋጋው ሊለያይ ይችላል
  • ቁም ሳጥን፦ በካሬ ከሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር ጀምሮ ያመርታል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

የኮቪድ ተፅዕኖ ከባድ ነበር ምንም ሥራ አልነበረም የነበረውን ሥራ በማጠናቀቅ እና ድርጅቱ ትንሽ ቆየት ያለ ድርጅት ስለሆነ አንዳንድ ነገሮች ከቁጠባ በመጠቀም ነው ያለፈው። አሁንም ኮቪድ ያመጣው ችግር ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም – ከነበረው ቢቀንስም።

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ ወደፊት ከሦስት ዓመት በኋላ ከውጭ የሚመጡ ማንኛቸውንም የፈርኒቸር እቃዎች ሙሉ በሙሉ በጥራት እና በውበት የሚተካ ሥራ መሥራት የሚችል ድርጅት እንደሚሆን አውቆ፣ ለመሆን እየሠራ ይገኛል።

ድርጅቱ በፐርኬ ዲዛየን ሥራ በጣም ጥራት ያለው ሥራ ይሠራል ለዚህም የሚጠቀመው ኢንዲስትሪያል ማሽን ስለሆነ በሥራው በደንብ ስፔሻላይዝ አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ምንም አይነት ሥራ ቢመጣ በደንብ የመሥራት አቅሙ አለው። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የፐርኬ ሥራዎች በጥራት በመሥራት ተጠቃሽ ነው።

አንድ አዲስ ሰው የራሱ ሥራ ለመጀመር ሲያስብ ትዕግስተኛ ሊሆን ይገባል፤ ሁል ጊዜ ራስን ማሳደግ እና ብዙ ጊዜ ወርክ ሾፕ ላይ ማሳለፍ በተቻለ መጠን ሥራውን ለማሻሻል የሚሞክር ሰው መሆን አለበት ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

እንደ ተጨማሪ አቶ አልአዛር የሚከተለውን ብለዋል። “የሃገር ውስጥ ምርት መንግሥትም ግለሰብም አይጠቀምም። ሀገር ውስጥ የሚመረት ነገር እያለ የውጭ ምንዛሬ አውጥቶ ከውጭ ያስመጣል። ከውጭ የመጣው ከተበላሸ በቀላሉ አይጠገንም። ሃገር ውስጥ ያሉ አምራቾች እድል ቢሰጣቸ በጣም ጥሩ የሆነ ሥራ መሥራት ይችላሉ። ስለዚህ የሁሉም ሰው አመለካከት በሀገር ውስጥ ምርት ቢቀየር ጥሩ ነው።”

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …