መነሻ / የጥቃቅን እና አነስተኛ መረጃ / ወቅታዊ መረጃ / ስለ ‘ከፍታ’ ፖርታል የሚያስገነዝብ ሥልጠና እየተካሄደ ነው
kefta-training-banner

ስለ ‘ከፍታ’ ፖርታል የሚያስገነዝብ ሥልጠና እየተካሄደ ነው

የተወዳጁ 2merkato.com ባለቤት የሆነው ኢቢዝ ኦንላይን ሶሉሽንስ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ 120 ወረዳዎች ለሚገኙ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና የቡድን መሪዎች ሥልጠና እያካሄደ ነው። ኢቢዝ ‘SNV’ ከተባለው የኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት ጋር በመሆን እና በአዲስ አበባ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ትብብር ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተዘጋጀ ‘ከፍታ’ የሚባል የመረጃ ማዕከል አደራጅቷል። ሙሉ በሙሉ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈው የመረጃ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወራት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ መረጃን በቀላሉ በማግኘት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር በሥራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ለማገዝ የታለመ ነው። ይህም በከተማዋ የበለጡ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ አስተዋጽዖ ያደርጋል።

ሥልጠናው በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች ባሉ ወረዳዎች ለሚገኙ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና የቡድን መሪዎች ባለፈው ሳምንት የተሰጠ ሲሆን ለቀሩት በአንድ ክፍለ ከተማ ላሉ ወረዳዎች ደግሞ ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 17 ይሰጣል። የሥልጠናው ዓላማ የከፍታን አገልግሎት በስፋት ለማስተዋወቅና የየወረዳዎቹ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና የቡድን መሪዎች ‘ከፍታ’ ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠውን ጥቅም በደንብ እንዲረዱት ለማድረግ ነው። በሥልጠናውም ወቅት ኢንተርፕራይዞችን በከፍታ አገልግሎት በኩል እንዴት አድርጎ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ውይይቶች ተደርገዋል፤ አስተያየቶችም ተሰብስበዋል።

ከፍታ የመረጃ ማዕከል በድረ ገጽ፣ በአንድሮይድ የሞባይል መተግበሪያ እንዲሁም በጥሪ ማዕከል የተደራጀ ነው። በድረ ገጽ www.kefta.net ላይ በመግባት መረጃዎቹን ማግኘት እንዲሁም 6131 ብሎ በመደወል የጥሪ ማዕከሉን ሠራተኞች ማነጋገር ይቻላል። ከፍታ ከምሥረታ እና አደረጃጀት አንሥቶ፣ ከኢንተርፕራይዝ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም መረጃ፣ አስፈላጊ የባለሙያ ስልክ ቁጥሮች፣ ልዩ ልዩ የቢዝነስ መረጃ እና ምክሮች፣ እንዲሁም ከበጎ ፈቃደኛ የቢዝነስ አማካሪዎች ጋር የመገናኛ ዕድሎችንም የያዘ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከፍታ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች እና ሌሎችም የኮንስትራክሽን ፖርታል የሆነው con.2merkato.com ላይ በመግባት የጊዜውን የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ፣ የሠራተኛ ክፍያ እና የማሽን ኪራይ ዋጋ መመልከቻ መድረክንም ያካተተ ነው። ይህ የኮንስትራክሽን ፖርታል፣ የኮንስትራክሽን ሠራተኛ ለመቅጠር ወይም የኮንስትራክሽን ሥራ ፈላጊ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ሥራ ለመፈለግም ጭምር የሚያገለግል መድረክ ነው።

ከዚህም በላይ፣ ልዩ በሆነ የኢንተርፕራይዞች የጥቅል (ፓኬጅ) አገልግሎት ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን በኦንላይን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት፣ በመላ ኢትዮጵያ የሚወጡ ጨረታዎችን በድረ ገጽ እና በሞባይል መተግበሪያ የሚከታተሉበት አማራጭም በከፍተኛ ቅናሽ ተዘጋጅቷል። በዚህም ከ3,000 (ሦስት ሺህ) በላይ የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች የአግልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኢቢዝ ከጽሕፈት ቤቶቹ ጋር በመተባበር ይሠራል።

የከፍታ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አዲስ አሰፋ የየክፍለ ከተማዎቹ እና የየወረዳዎቹ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና የቡድን መሪዎች ላሳዩት ተነሳሽነት እና ትብብር ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

kefta-training-various

ይህንንም ይመልከቱ

kefta-care-training-2

ከፍታ ለ20 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ

ከፍታ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለ20 በሴቶች ለሚተዳደሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው ያተኮረው …