መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ የመድረስ ትዕግስት – ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ

ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ የመድረስ ትዕግስት – ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ

ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ በ2005 ዓ.ም በአቶ አሰፋ ወልዴ ተመሠረተ። ደርጅቱ ሲመሠረት ከነበረው የመነሻ አምስት መቶ ብር ካፒታል አሁን ወደአለው ሀምሳ ሺህ ብር ካፒታል ለመድረስ በዘርፉ ያካበቱት የሥራ ልምድ እና የወሰዷቸው ሥልጠናዎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳደረጉላቸው የድርጅቱ መሥራች አቶ አሰፋ ይገልፃሉ።

አቶ አሰፋ የዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ከአክስታቸው ጋር እንጀራ አብረው እየሠሩ ከቆዩ በሁዋላ በግል የራሳቸውን ሥራ የመክፈት ሀሳብ እንደ መጣላቸው እና ዳቦ ቤት ብጀምርስ የሚለውን ሀሳብ ከቤተሰባቸው ጋር ከተወያዩበት በኋላ የዳቦ ቤት ሥራውን በትንሹ እንደጀመሩት ነግረውናል።

ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች

  • ኬክ
  • ቦምቦሊኖ
  • ዳቦ
  • ኩኪስ
  • ድፎ ዳቦ
  • እንጀራ
  • ለሰርግ፣ ለምርቃት፣ ለልደት እና ለሌሎችም ዝግጅቶች ሥራዎቹን ያቀርባል።

ምሥረታና ዕድገት

አቶ አሰፋ ወደ ዳቦ እና ኬክ ሙያ እንዴት ሊገቡ እንደቻሉ ሲያስረዱ ከአክስታቸው ጋር ሙያውን መማራቸው ወደ ዘርፉ ለመሰማራት በር መክፈቱን እንዲሁም ለሥራው ባላቸው ፍቅር ወደ ሙያው ሊገቡ እንደቻሉ ገልፀዋል። ሥራውን ከጀመሩም በኋላ በግል ጥረታቸው ከጓደኛቸው ጋር በመሆን ጉግል(Google) እያደረጉ አዳዲስ አሠራሮችን እየተማሩ ሲመጡ ይበልጥ ሙያውን እንዲወዱት አድርጓቸዋል። ድርጅቱ ሲጀመር በትንሽ ሱቅ በአምስት መቶ ብር የተጀመረ ሥራ አሁን የሀምሳ ሺህ ብር ካፒታል ሊደርስ ችሎአል። ድርጅቱ በዚህን ጊዜ ከደቡብ ኮሪያ(South Korea) እና ከቱርክ (Turkey) ማሽኖችን እያስገባ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ለዐሥራ አንድ ቋሚ እና ሁለት ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ለዚህ ደረጃ ለመድረስ ከአክስታቸው የተማሩት ጠንክሮ የመሥራት የሥራ ባህል እንዱ ሲሆን ቀጥሎም ትምህርት እና ቴክኖሎጂን መጠቀም እዚህ አድርሶናል ይላሉ የድርጅቱ መሥራች አቶ አሰፋ።

በአሁኑ ወቅት ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ ከትልልቅ ድርጅቶች ጋር አብሮ እየሠራ ይገኛል፤ ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ጥቁር እንበሳ እና ቦሌ ትምህርት ቤት ጋር አብሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አቶ አሰፋ ገልፀዋል። እነዚህን ሥራዎች ከክበቦቹ ጋር በመነጋገር እንደሚሠሩ አክለዋል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

ኮቪድ ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ ላይ የነበረው ተፅዕኖ ከባድ ነበር፤ ምክንያቱም የምግብ ሥራ ንክኪ ስላለው ሰው በዚህ ምክንያት ሙሉ በሙሉ የውጭ ምግብ መግዛት አቁሞ ነበር። እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠር እንደ አብዛኛው ጊዜ ከቤተሰብ ጋር በመነጋገር ጥሬ እቃዎችን በመቆጠብ ችጅሩን ለማለፍ እንደሞከሩ ገልጸዋል።

 

ማስተዋወቅ፣ ማስፋፋት እና ምክር

የጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ መሥራች አቶ አሰፋ ቴክኖሎጂ መጠቀም በጣም ጥሩ እንደሆነ ይገልጻሉ። አንድን ምርት እንዴት ነው በተሻለ መልኩ ልናመርተው የምንችለው? ዲዛየን በመቀየር ነው? ወይስ መጠኑን በመጨመር ወይም በመቀነስ? እንዲሁም ዘመናዊ ምግብ-ነክ ንጥረ ነገሮችን በማስገባት? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲሁም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ቴክኖሎጂ መጠቀም በጣም ይጠቅማል ይላሉ አቶ አሰፋ።

ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ ቢዝነሱን ከተጀመረ በኋላ ያስተዋለው ነገር ስለ ሥራው ጠለቅ ያለ እውቀት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ነው። ሥራውን በደንብ ሳያውቁት በጀመሩበት ወቅት የማቴሪያል፣ የገንዘብ እና የጊዜ ዋጋ አስከፍሏቸው ነበር። የወሰዱት መፍትሔ ከቤተሰብ አንድ ሰው በሙያው እንዲሰለጥን ከተደረገ በኋላ ትልቅ ለውጥ በገንዘብ፣ በማቴሪያል አቆጣጠብ እንዲሁም ሥራውን እራሱ በጥራት ለመሥራት እንዲችሉ አንዳስቻላቸው አቶ አሰፋ አስረድተዋል።

ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ ከተመሠረተ በሁዋላ ያመጣቸውን ለውጦች እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ፦ ከካፒታል እድገት በተጨማሪ ወደ ፊት መልሰው ሊሸጡ የሚችሉ ንብረቶች ማፍራት ችሏል። ለምሳሌ አንድ ጀነሬተር ሲገዛ በስድስት መቶ ዘጠና ሺህ ብር ነበር የተገዛው አሁን አንድ ሚሊዮን ብር ገብቷል። እንዲሁም የተለያዩ የዳቦ ማሽኖች ባለቤት ነው። ቋሚ ደንበኞች ማፍራት እና መንግሥት ምገባ የሚያደረግባቸው ትምሕርት ቤቶች ጋር ከኬጂ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ እና ከ ትልልቅ የትምሕርት ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት ራሱ ትልቅ እድገት ነው ብለው የገልጻሉ።

አዲስ ወደ ዘርፉ ለሚሰማሩ ሰዎች ሥራውን ሳያውቁ ባይጀምሩ ይመከራል። ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሰዎች ትምህርት መውሰድ በጣም አስፈላጊ ነው። በመቀጠል እንደ ዳቦ ባለሙያ በትንሽ ካፒታል ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚቻልበት ሙያ ነው፣ ግን በትዕግስት መሥራት ይጠይቃል። እንዲሁም ሥራውን ከሚያውቁ ሰዎች ጋር መነጋገር በቴክኖሎጂም ጥናት በማድረግ ራስን ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጸጋ ዳቦ እና ኬክ መጋገሪያ ማስፋፊያ ሥራውን አጠናቆ ሲጨርስ የከፍታ (kefta.2merkato.com) የጨረታ መረጃ አቅርቦት እና የፕሮሞሽን (የገበያ ትስስር) አገልግሎት የመጠቀም ሃሳብ አለው።

ወደፊት አሁን ያለበትን የሥራ ቦታ በማሻሻል ትልልቅ ማሽኖች የሚኖሩት ትልቅ ድርጅት ለመሆን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …