መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ቤስ ማኑፋክቸሪንግ

ቤስ ማኑፋክቸሪንግ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ሲሳይ ደጉ እና በባልደረባቸው ወ/ሮ ቤተልሔም በ2007 ዓ.ም. ነው። ቤስ የተለያዩ ማሽኖች የሚያመርት እና ጠቅላላ የብረታ ብረት ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች በሦስት የዘርፍ ዓይነት ከፍሎ የሚያመርት ሲሆን ምርቶቹም እንደሚከተሉት ናቸው፦

የመጀመሪያው ዘርፍ የማሽን ምርቶች ሲሆኑ፤ እነሱም፦

  1. ፊውል ፓምፕ ቴስተር
  2. ዲዝል ፓምፕ ቴስተር
  3. አሉሚኒየም ስፒኒንግ

ሁለተኛ ዘርፍ የተመደቡ ደግሞ ለማኅበረ ሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ምርቶች ናቸው፤ እነሱም፦

  1. የሽንኩር መፍጫ ማሽን
  2. ማኮፈሻ ማሽን
  3. ኅይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ ምጣድ

በሦስተኛ ዘርፍ ደግሞ የተለመዱ እና ጠቅላላ የብረታ ብረት ሥራዎች ናቸው፦

  1.  በር፣ ጠረጴዛ፣ መስኮት
  2. እንዲሁም እንደ ደንበኛው ፍላጎት የሚመጡ የተለያዩ ሥራዎች
  3. ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ቢሠሩ የተሻለ ገቢ ያመጣሉ ተብለው የተጠኑ ሥራዎችን በማጥናት ይሠራል።

የምርቶቹ ዋጋ በከፊሉ እንደሚከተለው ነው

  • ፊውል ፓምፕ ቴስተር ከሀገር ውጪ ሲመጣ ከብር 800,000 (ስምንት መቶ ሺሕ ብር) እስከ ብር 1,500,000 (አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር) ይሸጣል። ድርጅቱ ይህንን ማሽን ራሱ በማምረት ከብር 150,000 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር) እስከ ብር 200,000 (ሁለት መቶ ሺሕ ብር) በሚሆን ዋጋ ገበያ ላይ እያቀረበ ይገኛል።
  • ስፒኒንግ ማሽን በኒኬል እና በአሉሚኒየም የሚሠሩ የተለያዩ ዕቃዎችን (ለምሳሌ የብረት ድስት) ለመሥራት የሚያስችል ማሽን ነው። ድርጅቱ ማሽኑን በብር 250,000 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር) እያመረተ ለገበያ ያቀርባል።
  • ሃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ ምጣድ በብር 2,300 (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ብር) ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።
  • ሌሎች ምርቶች እንደ ኪሎ መጠናቸው እና የሚጠቀሙት የጥሬ ዋጋ ዓይነት ተመናቸው ይለያያል። ለምሳሌ የሽንኩርት መፍጫ ማሽን ከብር 15,000 (ዐሥራ አምስት ሺሕ ብር) እስከ ብር 25,000 (ሃያ ዐምስት ሺሕ ብር) ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ሢሳይ ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት በአውቶ ቦዲ ሥራ ተቀጥረው ሲሠሩ ቆይተዋል። ይሁና እና ሥራው ዘወትር አንድ ዓይነት እና ተደጋጋሚ በመሆኑ እንዲሁም እሳቸው መሥራት የሚፈልጉትን ለየት ያሉ ሥራዎችን መሥራት እንዳይችሉ አድርጓቸው ነበር። ይህም በግላቸው ቢሠሩ የተሻለ የሚፈልጉትን ሥራ መሥራት እንደሚችሉ በማመን፣ የሚኖራቸውን የሥራ እርካታ በማሰብ፣ እንዲሁም በቅጥር ሲሠሩ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አምራች መሆን የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል ብለው በማረጋገጣቸው ከአንድ ጓደኛቸው ጋር በመሆን በብር 5,000 (ብር ዐምስት ሺሕ) ካፒታል ድርጅቱን መሥርተዋል። አቶ ሢሳይ እስከ አሁን በዘርፉ የዐሥራ ዐምስት ዓመት የሥራ ልምድ አካብተዋል።

ከድርጅቱ ምሥረታ በኋላ አቶ ሢሳይ የቡድን ሥራ አዋጭ እንደሆነ በማመን እና በተግባር በመረዳት ሌሎች ሁለት መሥራች አባላትን በመጨመር የመሥራች አባላትን ቁጥር ወደ አራት አሳድገዋል። ይህም የድርጅቱን የካፒታል አቅም የተሻለ በማድረግ ጥሩ እድገት እንዲያስመዘግብ አድርጎታል። ቤስ ማኑፋክቸሪንግ ለአራት ቋሚ እና ለአራት ጊዜያዊ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን የካፒታል አቅሙንም ወደ ብር 1,700,000 (አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር) አሳድጓል። አቶ ሢሳይ በግላቸው “ለሀገር ጠቃሚ እና ደስ የሚል የሚያኮራ ሥራ በመሥራቴ እና እየሠራሁ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።

ቤስ ማኑፋክቸሪንግ ሥራዎችን የሚሠራው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ሲሆን አንደኛ ምርት በሚያመርትበት ቦታ ከሚገኙ ደንበኞች፣ የቴሌግራም ቻናል በመጠቀም እና በሰው በሰው ነው። ድርጅቱ ሰፋ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ሥራዎችን ሠርቷል፤ ከነዚህም መካከል ሥስት መቶ ቲዲኤስ ተገጣጣሚ ቤቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በማምረት ለወረዳ አስረክቧል። እንዲሁ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ጋር ተያይዞ የቢሮ ዕቃ (office furniture) ዕጥረት በነበረበት ጊዜ ለአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ የውጭ ምርትን ተክቶ በመሥራት ሁለት መቶ ሃምሳ ጠረጴዛ ከዐሥራ ዐምስት ቀናት እስከ አንድ ወር በፈጀ ጊዜ ውስጥ አምርቶ አስረክቧል።

የኮቪድ ተጽዕኖ

በኮቪድ ወቅት ድርጅቱ በራሱ ዲዛይን ያመረተውን ያለንክኪ ለእጅ መታጠቢያ የሚያገለግል ማሽን በመሥራት እና ከአምስት መቶ በላይ ምርቶችን መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች (NGO’s) በማቅረብ ጊዜውን በጥሩ ሁኔታ ሊያልፍ ችሏል። ከኮቪድ በኋላ በመታጠቢያው ላይ ባለው የሎጎ አድራሻ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን በስልክ እየተደወለለት መሥራት ችሏል። አሁን ላይ ግን ትንሽ የመዳከም ሁኔታን እንዳሳየ የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል።ይህም የሆነበት ዐበይት ምክንያት ተጠንቶ፣ የተገኘው ችግር የድርጅቱን ሎጎ (አርማ) በምርቱ ላይ መለጠፍ መቀነሳቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ምክር

የድርጅቱ መሥራች ስለ ግል ሥራ መታወቅ ያለበት ነገር እንደሚከለው አክለዋል “የግል ሥራ ትልቁ ተግዳሮት የፋይናንስ አስተዳደር ነው። ስለዚህ ወደ ግል ሥራ ሲገቡ ጠንካራ የፋይናንስ አስተዳደር ይዞ መግባት አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ ግን የግብዓት ችግር ይመጣል፤ ይህ ደሞ የምርት ችግር በማምጣት ሥራ እንዳይሠራ ያደርጋል። ፋይናንስ ክተስተካለ ደግሞ ጥሩ ውጤት ይዞ ይመጣል፤ ይህ ደግሞ የተሻለ ምርት ለማምረት ይረዳል።” ሌላው ደግሞ ችግሮች ሲፈጠሩ  ጥሩ ልምድ እና ጠንካራ ተሞክሮ አላቸው ብለው የሚያምኗቸውን ሰዎች ማማከር፣ ኢንተርኔት መጠቀም ለሥራ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ከግል ተሞክሯቸው አካፍለዋል። “ከምንም በላይ ግን ችግሩን ፈርተው ላለመጀመር ባያስቡ የተሻለ ነው፤ ጠንካራ መሆን የሚቻለው ዋናው በችግሩ ውስጥ ሲታለፍ ስለሆነ ነው። ስለዚህ ማንኛውም ሥራ ምንም ዓይነት ችግር ቢኖረው መጀመር የተሻለ ነው። ስላሰቡ ብቻ መጀመር የተሻለ ነው” ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ዕቅድ

ድርጅቱ ምርቱን ለማኅበረ ሰቡ በሰፊው ለማቅረብ፣ በፋይናንስ በኩልም የተሻለ አቅም ያለው ተቋም የመሆን እንዲሁም በምርቱ የሚታወቅ ጠንካራ ብራንድ የመገንባት እቅድ አለው።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …