ኡቡንቱ ኤራ ኅ.የተ.የግ.ማኅበር የተመሠረተው በወ/ሮ መአዛ ታምራት በ2008 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የንጽህና መጠበቂያ እና የጽዳት ዕቃዎችን በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማምረት ለገበያ ያቀርባል።
ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች
- የልብስ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና
- የዕቃ ማጠበቢያ ፈሳሽ ሳሙና
- በረኪና
- የመስኮት ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና እና
- ሳኒታይዘር
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ወ/ሮ መአዛ ይህንን ድርጅት ከመመሥረታቸው በፊት በኅትመት ሥራ ረዘም ላለ ጊዜ ሲሠሩ ቆይተዋል። በሂደት ግን የተለየ እና ሰፋ ያለ ሥራ ለመሥራት በማሰብ አንድ ጓደኛቸውን የተሻለ ሰፋ ያለ እሳቸው ሊሠሩት የሚችሉት ሥራ ምን አለ ብለው አማከሩት። ጓደኛቸውም ባለው ተሞክሮ ሁልጊዜ የሚፈለግ ምርት እና እሳቸው በቀላሉ ሊሠሩት የሚችሉት ሥራ የጽዳት ዕቃዎች ማምረት እንደሆነ ነገራቸው። እንዲሁም ሥራውን ስለሚያውቀው እንደሚያግዛቸው ከተማከሩ በኋላ ኡቡንቱ ኤራ ኅ.የተ.የግ.ማኅበር ተመሠረተ።
ድርጅቱ ሲመሠረት የነበረው መነሻ ካፒታል ሃምሳ ሺሕ ብር (ብር 50,000) ነበር። አሁን የድርጅቱ ካፒታል አምስት መቶ ሺሕ ብር (500,000 ብር) ደርሷል። በተጨማሪ ደግሞ ለስድስት ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት አሁን ባለው የማምረት አቅም በቀን አንድ ሺሕ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና እያመረተ ይገኛል። ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች ባለ አንድ፣ ሦሶስት እና ባለ አምስት ሊትር መጠን ያላቸው ናቸው። ምርቱን በቀጥታ ከድርጅቱ መግዛት የሚፈልግ ሰው ትንሹ መግዛት የሚችለው መጠን ዐምስት ደርዘን ነው።
ወ/ሮ መአዛ ድርጅቱን ከመሠረቱ በኋላ የሥራውን ክፍፍል እሳቸው ገበያ በመፈለግ፣ ጥሬ እቃ በማቅረብ እና የተለያዩ ከመንግሥት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመሥራት ሌላውን ሥራ ደግሞ ባለሙያዎችን በመቅጠር ለምሳሌ ኬሚስት እና ሌሎች ሠራተኞችን በመቅጠር እንዲሁም ያማከራቸው ጓደኛቸው እያገዛቸው የመሥሪያ ቦታ በመከራየት ነበር ወደ ሥራ የገቡት። ነገር ግን ሥራው እሳቸው እንዳሰቡት ቀላል አልነበረም፤ ለምሳሌ ገበያ ማግኘት ቀላል አልነበረም የምርቱ ተጠቃሚ ማኅበረ ሰብ እንዲሁም ነጋዴ የሚፈልገው የሚያውቀውንም ምርት ብቻ ነው። አንዳንዴ ሙሉ ቀን ዞረው ምንም ሳይሸጡ የሚገቡበት ጊዜ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር አለ። አንዳንድ ዕቃዎች ከውጪ ስለሆነ የሚመጡት ይህ ደግሞ ነገሮች ያከብዳቸዋል። በቅርቡ ራሱ የተፈጠረ ሁኔታ የእጅ መታጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና ፓምፕ ክዳን ከውጭ ነው የሚገባው። ይህ ደግሞ ገበያ ላይ የለም። በሰው በሰው ነው ዕቃው የሚገኘው እንዲህ ሲሆን ደግሞ ደረሰኝ የለውም። ይህ ደግሞ ለማወራረድ አይመችም። በነበሩት ችግሮች የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው እስከ መዝጋት ድረስ ደርሰው ነበር። “የገበያ እጦት በጣም ችግር ነበር፤ አብዛኛው ሰው አዲስ ምርት ለመቀበል አይፈልግም። ሁሉም ሰው “ጊዮን ነው?” “ጮራ ነው?” ፈሳሽ ሳሙና ከሆነ ደግሞ “ላርጎ ነው?” ነው የሚለው። ሱቆች ደግሞ አይፈልጉም ለመሞከር ራሱ ፈቃደኛ አልነበሩም” ሲሉ የነበረውን ችግር በትንሹም ቢሆን ጠቅሰዋል። ድርጅቱ ብዙ ጨረታዎች ላይ ተወዳድሯል። ጨረታውን ሲያሸነፉ ራሱ ጥሬ እቃ ከሌለ እንዴት ነው የምንሠራው ብለው ይጨነቃሉ።
ይሁን እና ወ/ሮ መአዛ ተስፋ ባለመቁረጣቸው የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ምርታቸውን ለገበያ ያቀርባሉ። ባዛር ላይ ዐይተው ሞክረው የሚወዱት እና የሚመጡ ደንበኖች አሉ። በሂደት ድርጅቱ ምርቱን ለኮልፌ ክፍለ ከተማ ዩኒየን ማስረከብ ሲጀምር ነገሮች እየተሻሻሉ መጥተዋል። ዩኒየኑ ደግሞ ለሸማች እና ሌሎች አካላት ያከፋፍላል። በሂደት ደግሞ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጋር አብረው ሠርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አቅማቸው የሚችላቸው ጨረታዎች ላይ ይሳተፋሉ። በዚህም የካቲት ዐሥራ ሁለት ሆስፒታልን ስድስት ሺሕ (6,000) ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ጨረታ አሸንፈው በሚገባ ሥራውን ሠርተው አስረክበዋል። አሁን ደግሞ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመጠቀም ጨረታ በመመልከት አንድ የጤና ጣቢያ ጨረታ ማሸነፍ ችለዋል።
ወ/ሮ መአዛ ከሥራው ጋር ተያያዥ የሆኑ ልምድ እና ክህሎቶችን ያዳበሩት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ እና በልምድ ነው። አሁን ሙሉ ሥራውን እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ ችለዋል። ለድርጅቱ ነገሮች አሁን ተሻሽለዋል፤ ከመንግሥት የመሥሪያ ቦታ ስለተሰጣቸው ሁኔታዎች ጥሩ እንደሆኑ የድርጅቱ መሥራች ገልጸዋል።
የኮቪድ ተፅዕኖ እና ምክር
በኮሮና ወቅት ድርጅቱ ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደነበር ጠቅሰዋል። ይህም ከመንግሥት በተሰጠው ፈቃድ ሳኒታይዘር ማምረት እና ማቅረብ ስለቻለ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የጥሬ እቃ አቅርቦት በመንግሥት በኩል ስለተመቻቸ ድርጅቱ በብዙ መልኩ ማደግ ችሏል።
ወ/ሮ መአዛ ወደ ዘርፉ ለሚቀላቀሉ ሰዎች ሥራው በዋናነት ትዕግስት እንደሚፈልግ፣ በመቀጠል ደግሞ የኬሚካል ሥራ ስለሆነ ከኬሚካል ጋር ንክኪ ስለሚኖረው ጥንቃቄ አንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጠቀም ያለ ገንዘብ ይዘው ቢጀምሩ መልካም እንደሆነ ይመክራሉ።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ።