ወይንሸት፣ ፍቅርተ እና ጓደኞቻቸው የቀርከሃ ሥራ ኅብረት ሽርክና ማኅበር የተመሠረተው በወ/ሮ ፍቅርተ ገብሬ እና ሁለት መሥራች አባላት በ2009 ዓ.ም. ነው። የቤት ማስዋቢያ እቃዎች እንዲሁም ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የፈርኒቸር ሥራዎችን ከእንጨት ውጤቶች ጋር በማቀናጅት (በማመሳጠር) ያመርታል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የወንድ እና የሴት ጌጣጌጥ ምርቶችን (ማጌጭያዎችን) ያመርታል።ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ምርቶች እና ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል
- የቀርከሃ አልጋ
- የቀርከሃ ሶፋ
- የቀርከሃ ወንበር
- የሎጅ እና ቤት የማስዋብ አገልግሎት
- በቀርከሃ የሚሠሩ የፍራፍሬ እና የወይን ማስቀመጫ ዕቃዎችን
- የራስጌ መብራት
- የቡና ጠጡ ሶፋዎችን
- የወንድ እና የሴት ቦርሳዎች
- የተለያዩ የአንገት፣ የጆሮ እና የእጅ ጌጣጌጦችን ያመርታል።
ድርጅቱ የምርቱን ዓይነት በሁለት የዋጋ ተመን በመለየት ያመርታል፤ እነሱም ትንሽ እና ትልቅ የሚባሉ ምርቶች ናቸው።
- ትንሽ የሚባሉት እቃዎች ዋጋቸው ከ150 ብር (መቶ ሃምሳ ብር) ጀምሮ እስከ 2000 ብር (ሁለት ሺህ ብር) ድረስ ነው።
- ሁለተኛው ደግሞ የፈርኒቸር እቃዎች ሲሆኑ ዋጋቸው ከ500 ብር (ዐምስት መቶ ብር) ጀምሮ እስከ 20,000 ብር (ሃያ ሺህ ብር) ድረስ ነው። ይህም የውስጥ ሶፋ፣ አልጋ እና ትንንሽ ኩርሲዎችን ያካትታል።
ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት
ድርጅቱ ሲመሠረተ በሦስት መሥራች አባላት ነበር። አሁን የመሥራች አባላት ቁጥር ወደ ስድስት ማደግ ችሏል። ድርጅቱ ራሱን ከመቻል በተጨማሪ ደግሞ ለዐሥር ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሮ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ወ/ሮ ፍቅርተ ወደ ቀርከሃ ሥራ የገቡት በቀርከሃ ሥራ የአራት ወር ሥልጠና ለመውሰድ በወረዳው የሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ተመዝግበው ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ሥራው እያስደሰታቸው በመምጣቱ እንደሆነ ገልጸዋል። ሥልጠናቸውን እንደጨረሱ ወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ቻድኤክስ የሚባል ድርጅት ጋር በመሆን መሥራት ከፈለጋችሁ በራችን ክፍት ነው ተብለው አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ብር በመያዝ ወደ ሥራ ገቡ። በሂደት የተለያዩ ተስፋ የሚያስቆርጡ ችግሮችን እንዳሳለፉ የድርጅቱ መሥራች ጠቅስዋል። የቀርከሃ ሥራ አቁመው ወደ ቆሎ ሥራ ገብተው ነበር። የመሥሪያ ቦታ ችግር አንዱና ተጠቃሹ በመሆኑ። ይሁንና በሆነ ወቅት አንድ ጓደኛቸው ቻይና በአገኘችው የሥልጠና ዕድል በሥልጠናው ላይ ተሳትፋ በተሰጣት የቀን አበል ላይ ትንሽ ገንዘብ በመጨመር በጣም ወሳኝ የሚባሉ ማሽኖች በመግዛት እንደ አዲስ ድርጅቱ ሥራ መጀመር ችሏል።
ድርጅቱ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ ሁሉም አባሎች በፊት ከነበራቸው ልምድ እና ተሞክሮ እንዲሁም አዲስ እውቀት በማቀናጀት በጥሩ ሁኔታ ላይ መድረስ እንዲችል አድርጎታል። በዚህም ድርጅቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 160 (አንድ መቶ ስልሳ) አልጋዎችን የማምረት አቅም አለው። ከዚህም በተጨማሪ ሲመሠረት ከነበረው መነሻ ካፒታል ብር 1,500 (አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ብር) ብር ወደ 400,000 (አራት መቶ ሺሕ ብር) ብር ማሳደግ ችሏል። ይህም ሊሆን የቻለው የድርጅቱ አባላት ሳይታክቱ በመሥራታቸው እና ራሳቸውን በማሳደጋቸው ነው። ይህም ማለት በዋናነት የተማሩት የፈርኒቸር ሥራ ሲሆን አባሎች ግን ራሳቸውን በማሳደግ የስትሪፕ እና ዌቪንግ ሥራ መሥራት በመማራቸው እና በመሥራታቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ውጭ ሀገር ሄደው ሲመጡ የተለያዩ ነገሮች ተምረዋል፤ በቀላሉ ብዙ ነገሮችን መሥራት የሚያስችላቸውን ነገሮችን ተምረዋል። ለካ እንዲህም ይሠራል በማለት መሥራት የጀመሩዋቸው ሥራዎችም አሉ።
ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት ባዛር በመጠቀም ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ እንዲሁም በሰው በሰው እና ሄሎ ማርኬት በመጠቀም ነው። የሄሎ ማርኬት አሠራር ሄሎ ማርኬት ምርቱን ወስዶ ከሸጠ በኋላ ገንዘቡን በሄሎ ካሽ ያስረክባል። አሁን ደግሞ 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት በመጠቀም ጨረታዎችን በመከታተል ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከኢንባር (INBAR) ጋር አብረው እየሠሩ ይገኛሉ። የተለያዩ ኮርሶች እና ሥልጠናዎችን ወስደዋል። ይህ ደግሞ በጣም ጥሩ ነው ሲሉ ወ/ሮ ፍቅርተ ገልጸዋል።
የኮቪድ ተፅዕኖ
ኮቪድ በድርጅቱ ላይ ከባድ ችግር ነበረው፤ ዋናው ባዛር አልነበረም ሥራውን ያለ ባዛር መሥራት ከባድ ነው። የመሥሪያ ቦታ ላስቲክ ነበር። ይህን ለመቀየር ቢፈልጉም አልቻሉም። በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ይህ ደግሞ የቀርከሃ እቃዎች እንዲበላሹ ያደርጋል። በዚህ ወቅት ጂአይዜድ በኮቪድ ለተጎዱ ሆስፒታሎች የሚሆን አልጋ ለማሠራት በኮቪድ ቢዝነሳቸው የደከሙ ሥራዎችን በመምረጥ ድርጅቱ ተጠቃሚ አድርጓል። በዚህም በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ሺሕ አልጋ ሠርቶ አስረክቧል።
ምክር እና እቅድ
ድርጅቱ በመጪው አንድ ዓመት ውስጥ የማሳያ ሱቅ የመክፈት እቅድ አለው። ከዚህም ጋር አያይዞ ተማሪዎችን በማሠልጠን በቀርከሃ ዘርፍ ብዙ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በመፍጠር እና አሠልጥኖ የመቅጠር እቅድ አለው። በቀጣይ አመታት ደግሞ ማስፋፊያ በመጠየቅ፣ ትልቅ ማሽኖችን በማስገባት እና በመትከል፣ ትልልቅ ሥራዎችን እንደ ፐርኬ ሥራ ለመሬት እና ኮርኒስ እንዲሁም በዘመናዊ መንገድ መቀቀያ በመጠቀም የቀርከሃ ትሪትመት ሥራዎችን የመሥራት እቅድ አላቸው።
አዲስ ወደ ሥራው የሚገቡ ሰዎች በቀርከሃ ሥራ ለመሥራት ፍላጎት አስፈላጊ ነው። ለምን ሥራው ከባድ እና ጥንቃቄ ስለሚፈልግ እጅ ይጎዳል፣ ያበላሻል፣ በጣም ጥንቃቄ ይጠይቃል። በብዛት የዚህ ምርት ተጠቃሚዎች የውጭ ዜጎች ናቸው። ሥራውን እና ሥራው እስከሚለመድ ድረስ ከሌሎች ቢዝነሶች በተለየ መልኩ ረዘም ያለ ጊዜ ይፈልጋል። አንዳንድ ቻሌንጆች ይኖራሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ሰው “ይህ ሸንበቆ አይደል እንዴ እንዴት እንዲህ ተወደደ?” እያለ ሊያጣጣል ይችላል ልዩነቱን ሳያውቅ። ስለዚህ አዲስ ገቢዎች ሥራውን የሚወዱት ከሆነ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ ስለሚሠሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ይመክራሉ።
የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ።