መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / የበጋእሸት አሰፋ እና ጓደኞቻቸው ብረታ ብረት ሥራ

የበጋእሸት አሰፋ እና ጓደኞቻቸው ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ የበጋእሸት ገብሬ እና አራት መሥራች አባላት 2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች አጠቃላይ የብረታ ብረት ሥራዎች እንዲሁም የማሽነሪ ሥራዎች ናቸው።

የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የግሪል ሥራዎች
  • የበር እና የመስኮት ሥራዎች
  • የድንጋይ መፍጫ ማሽን
  • የብሎኬት ማምረቻ ማሽን
  • ሚክሠሮች
  • እንዲሁም የተለያዩ ማሽነሪዎች

አሁን የሥራው አለመኖር ነው እንጂ ማንኛውም ሥራ ቢመጣ አስፈላጊውን ሠራተኛ በመቅጠር መሥራት ይቻላል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ነጋሽ በግል ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በቶርኖ ሥራ ላይ ተቀጥረው የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል። ለምሳሌ ለተለያዩ ማሽኖች የሞዲፌክሽን ሥራዎችን በመሥራት ወይም አዲስ ብረቶችን ወስዶ በመበየድ ለመለዋወጫ የሚያገለግሉ ማሽኖች እና የተለያዩ የማሽን ጥርሶችን ይሠሩ ነበር። በሥራው በቂ ልምድ ካካበቱ በኋላ በራሳችን ብንሠራ ለኛም የተሻለ ገቢ እናገኛለን፣ ለሌሎች ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር እንችላለን ብለው ነው አቶ የበጋእሸት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የበጋእሸት አሰፋ እና ጓደኞቻቸው ብረታ ብረት ሥራ ድርጅትን የመሠረቱት።

ድርጅቱ የሚያመርታቸውን ምርቶች በተባለላቸው የማጠናቀቂያ ጊዜ ገደብ የማስረከብ አቅም አለው። እንዲሁም የተለያዩ የማሽነሪ ሥራዎችን በአንድ ሳምንት ጨርሶ ማስረከብ ይችላል ለምሳሌ አንድ የብሎኬት ማሽን በአምስት ቀን ውስጥ ሠርቶ የማስረከብ አቅም አለው።

ድርጅቱ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኘው አንደኛ በሰው በሰው ሲሆን፣ በመቀጠል ደግሞ በከፍታ ለኢንተርፕራይዞች በተመቻቸው ፓኬጅ በ2merkato.com የቢቱቢ (B2B) የኦንላይን መድረክ ምርቱን እና ሥራውን በማስተዋወቅ፣ እንዲሁም ጨረታዎችን እያዩም በመከታተል እና በመሳተፍ ነው

ድርጅቱ ለአምስት ቋሚ ሠራተኞች እና ሥራ ሲኖር ለሚጨመሩ ዐሥራ አምስት ለሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል።

አሁን ባለው ሁኔታ በዘርፉ ያለው ችግር የብረት ዋጋ በጣም መወደድ ነው። ዛሬ ሥራ ለመሥራት የተነጋገሩት ዋጋ ሥራወን ለመሥራት እቃ ለመግዛት ሲሄዱ ዋጋ ጨምሮ ነው የሚያገኙት። ይህ ደግሞ ደንበኞችን የሚያስከፋ ነው። ስለዚህ ድርጅቱ ይህን ችግር ለመፍታት የተጠቀመው መፍትሔ ደንበኞች ሥራ ሲያመጡ የሚያስፈልጋቸውን እቃ ምን ምን እንደሆነ በመንገር እነሱ እቃውን ገዝተው ሲመጡ ድርጅቱ የሙያውን ብቻ በመጠየቅ እየሠራ ይገኛል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

የድርጅቱ መሥራቾች ሥራውን ሲጀምሩ ኮቪድ እየቀነሰ በነበረበት ወቅት ስለነበር በጊዜው ብዙ ሥራ አልነበረም፤ ይህ ደግሞ ድርጅቱ የታሰበለትን ሥራ ሠርቶ ማደግ እንዳይችል አድርጎታል።

ምክር እና እቅድ

ድርጅቱ ወደ ፊት አሁን ያለው የዶላር እጥረት ከተሻሻለ የብረት አቅርቦት ይጨምራል። በዚህም ምክንያት ብዙ ሥራዎች እንደሚፈጠሩ የድርጅቱ መሥራች አባል ተስፋ አላቸው። ድርጅቱ ወደ ፊት በሌዘር ጨረር ተጠቅሞ ብረት ላይ ቅርጻ ቅርጽ መቅረጽ የሚችል ማሽን ለመግዛት እቅድ አለው።

አቶ የበጋእሸት አዲስ ለሚጀምሩ ሰዎች የሚከተለውን ብለዋል። “አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ብረት ሥራ መግባት በጣም አስቸጋሪ ነው። ብረት በጣም ተወዷል፤ የመሥሪያ ቦታ ያስፈልጋል፤ ኪራይ አለ፤ ሥራውን በሚገባ ማወቅ አስፈላጊ ነው። እነዚህን ችግሮች አልፎ ለመሥራት ግን ምንም ሥራ መምረጥ የለባቸውም፤ ምንም ቢሆን ተስፋ ሳይቆርጡ መሥራት የሚችሉ ከሆኑ ሥራው አዋጭ ነው” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የድርጅቱን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የድርጅቱን ስልክ በዚህ ሊንክ በመግባት ዓይተው መደወል ይችላሉ

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …