መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / የሚያውቁትን ሥራ መሥራት ለውጤታማነት – ውብዓለም ፈቃደ እና ጓደኞቻቸው የእንጨት ሥራዎች

የሚያውቁትን ሥራ መሥራት ለውጤታማነት – ውብዓለም ፈቃደ እና ጓደኞቻቸው የእንጨት ሥራዎች

ውባዓለም ፈቃደ እና ጓደኞቻቸው የእንጨት ሥራዎች የተመሠረተው በአቶ ፈቃደሥላሴ ግርማ እና በአራት መሥራች አባላት በ2006 ዓ.ም ነው።  ድርጅቱ የቤት እና የቢሮ እቃዎችን እንዲሁም አጠቃላይ የእንጨት ሥራዎችን ቃል በገባው ጊዜ አምርቶ ያስረክባል። በአምስት መስራች አባላት የተመሠረተው ድርጅት በአሁኑ ወቅት አስር ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በአንድ ቀን አምስት አልጋዎችን በጥራት የማምረት አቅም አለው።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • ኪችን ካቢኔት
  • ቁምሳጥን
  • በር እና መስኮት
  • ወንበር እና ጠረጴዛ
  • የቲቪ ማስቀመጫ

ምሥረታና ዕድገት

ድርጅቱን የተመሠረተበትን ምክንያት አቶ ፈቃደ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ። ሁሉም መሥራች አባላት በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር፤ እናም የሚከፈለው ክፍያ እና የሚሠሩት ሥራ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በራሳችን ብንሠራ የተሻለ ውጤት ይኖረናል በሚል እና ብቁ ባለሙያም በመኖሩ ምክንያት ውብዓለም ፈቃደ እና ጓደኞቻቸው የእንጨት ሥራዎች የተመሠረተው።  ድርጅቱ ከተመሠረተ ስምንት ዓመት ሆኖታል።  ድርጅቱ ከመመሥረቱ በፊት መሥራች አባላቱ የ10+3 እየተማሩ  ጎን ለጎን የእንጨት ሥራ ይሰሩ ነበር። ከዚሀም የተነሳ ሁሉም አባላት ወደ ሥራው አለም ሲገቡ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው በማድረጉ ወደ ሥራ ሲገቡ ብዙም ከባድ እንዳልነበር ገልፀዋል። ሥራው ላይ እያሉ ቀስ በቀስ አንዳንድ ማሽኖችን ስላሟሉ፣ እንዲሁም ምን ምን እንደሚያስፈልግ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ማሽኖቹን ገዝተው ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ቦታ ሲሰጣችው ቀጥታ ወደ ሥራ በመግባት ማምረት ጀምረዋል።

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

አቶ ፈቃደ ይህን ዘርፍ ሊመርጡ የቻሉበት ምክንያት እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል።  አንድ ሰው የሚያውቀውን ሥራ መሥራት አለበት ብለው ያምናሉ። ይህ አስተሳሰብ  የሁሉም የድርጅቱ መሥራቾች አመለካከት ነው፤ ምክንያቱም በአንድ ሥራ ላይ ውጤታማ ልትሆን የምትችለው የምታውቀውን ሥራ ስትሥራ ስለሆነ ነው። እኛም ጋር በሙያው ከዐሥር ዓመታት በላይ የቆዩ በጣም ብቁ የሆነ ባለሙያዎች አሉ። ስለዚህ ብቁ ነን ብለን የምናስበው በዚህ በእንጨት ሙያ ስለሆነ በዚህ ብንሰማራ የተሻለ ህይወታችንን መቀየር እንችላለንን፤ ስለሆነም የተሻለ ገቢ ማግኘት እንችላለን በሚል አስተሳሰብ ወደ እዚህ የሙያ ዘርፍ የገባነው ብለዋል፡፡  የራስ ሥራ እቅድ አለህ፤ መድረስ የምትፈልግበት ቦታ ይኖርሀል። መድረስ ለምትፈልግበት ቦታ የመጀመሪያው ነገር ሥራ ስትጀምር የመጀመሪያውን እርምጃ እንደ መጀመር ሲሆን የራስን ሥራ ስትጀምር ደግሞ ለመድረሻህ ለመቅረብ የመጀመሪያውን እርምጃ እንደ መራመድ ነው።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚያገኘው  ከዐሥራ አምስት በላይ ለሆኑ በጅምላ በሚያስረክባቸው ደንበኞቹ፣ ሳይት ላይ ደግሞ ሳይት ላይ ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በሮች መስኮቶችን በመሥራት እንዲሁም ባዛሮች ላይ የተወሰኑ ሰዎችን በመላክ፣ እንዲሁም በሳይት ላይ ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ፣ እንዲሁም ቴሌግራም ላይ በማስተዋወቅ ነው ሥራ የሚሰራው። የማምረቻ ቦታው የራቀና በደንበኞች በቀላሉ የማይደረስበት በመሆኑ ለተጠቃሚዎች ለመታየት አስቸጋሪ ነው።

ቴክኖሎጂ መጠቀም በጣም ጠቃሚ ነው ምክንያቱም ከዘመኑ ጋር በመራመድ የተሻሉ ምርቶችን ለማምረት ይቻላል። ያለ ቴክኖሎጂ ደግሞ ገበያ ላይ ተመራጭ እና ተወዳዳሪ ለመሆን እይቻልም። ድርጅቱ በተቻለ መጠን ውድም ቢሆን ዘመናዊ ማሽኖችን ለመጠቀም ይሞክራል ሥራን የበለጠ ለማዘመን ብቸኛውና ተመራጩ መንገድ ይህ ነው። ብዙ ዘመናዊ ማሽኖች አሉ ምርትን ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የሚያደርጉ ስለዚህ ቴክኖሎጂ በጣም ትልቁን ቦታ ይይዛል ብለዋል የድርጅቱ መሥራች።

ድርጅቱ  አካባቢው ካሉ በልምድ እና በሥራው ብዙ ከቆዩ ድርጅቶች ጋር የልምድ እና የተሞክሮ በመቅሰም ሥራውን እያሳለጠ ይገኛል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

የኮሮና ወረርሽኝ ከባድ ተፅዕኖ ስለነበረው የድርጅቱ ሥራዎች በብዛት የፊኒሺንግ ሥራዎች ሲሆኑ የፊኒሺንግ ጥሬ እቃ ደግሞ በብዛት ከውጭ ነው የሚመጣው። በኮቪድ ጊዜ ደግሞ ከውጭ የሚመጡ እቃዎች ቆመው ስለነበር ይህ ደግሞ የጥሬ እቃ፣ የምርት እና የገበያ ችግር እንዲፈጥር አድርጓል። ገበያ በጣም ቀዝቅዞ ነበር። ይህን ችግረ ድርጅቱ ያልፈው ለእንዲህ አይነት ጊዜ መጠባበቂያ ተብሎ የሚቀመጥ ተቀማጭ ገንዘብ ያስቀምጥ ስለነበር ያንን ገንዘብ በመጠቀም የነበረውን ችግር ሊያልፍ ችሏል።

ምክር እና እቅድ

አዲስ የሚገባ ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ አይገባም፤ የተወሰነ ጊዜ ሥራ እስከሚተዋወቅ ሙያ እስኪዳብር ጊዜ ይፈልጋል። ገንዘብ በቀላሉ አይገኝበትም፤ ዋናው እና ወሳኙ የሚግባቡ ሰዎች አብረው ቢጀምሩ ጥሩ ነው። እንዲሁም ሥራው ሲጀምር ሕጋዊ ሰንሰለቱ በጣም አሰልቺ በመሆኑ ያንን ማለፍ ራሱ ቀላል አይደለም። ወደ ሥራው ሲገባ የሥራ ማቴሪያል ማሟላት በጣም ከባድ ነው ማሽን ውድ ነው፤ እቃ በቀላሉ አይገኝም። ለምሳሌ በትንሹ ሥራ ለመሥራት ሶስት መቶ ሺህ ብር (ብር 300,000) ያስፈልጋል። ቢያንስ ድሪል፣ ጂግሶው የመሳሰሉ ማሽኖች፣ ትሬስ ማስቀመጫ፣ ቪንቴጅ ማሸጊያ ለማሟላት በጣም ከባድ ነው።

አንዲሁም ሥራውን የሚጀምሩት ከምንም በላይ ሥራውን አክብረው መሥራት መቻል አለባቸው። መሥራችና ባለቤት ከሠራተኛ በላይ መሥራት ይኖርበታል። ስለሆነም መሥራች የሁለት ሰው ሥራ መሥራት አለበት።  ባለቤት ነኝ ብሎ የሚያርፍ ወይም የሚቀር ከሆነ ይህ ሥራ አይሠራም በትዕዛዝ መሠረት በጊዜ ለማድረስ ስለማይቻል። በደንብ መሥራት አለባቸው እንደውም ሥራው ካለ አዳር ሁሉ የመሥራት ልምዱ ሊኖር እና ሊፈጠር ይገባል።

ድርጅቱ ወደ ፊት በእጥፍ የማስፋት እና የማሳያ ሱቆችን መክፈት እና ትልቅ ማሽኖችን ገንዘብ በመቆጠብ እንደ አስፈላጊነታችው ደረጃ ማሟላት እና ሠራተኛ በእጥፍ በመቅጠር የድርጅቱን አቅም ለማስፋት አቅደው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በ2merkato.com ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች የተዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት ያውቁታል፤ አቅማቸው ሲጠነክር ለመጠቀም እቅድ አላቸው።

አቶ ፈቃደሥላሴ በመጨረሻም ቅዱስ እግዚአብሔርን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውን፣ ቤተሰባቸውን እንዲሁም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3ን አመስግነዋል።

አቶ ፈቃደ እንደ ሀሳብ የሚከተለውን ብለዋል። አዲስ ተማሪዎችን መንግሥት አሠልጥኖ ቀጥታ ወደ ሥራ ይገባሉ። ይህም አላስፈላጊ እዳ እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነው የሚከታቸው፤ ምክንያቱም በሥራው ዓለም እና በቴክኒክ እና ሙያ ያለው አሥራር በጣም ይለያያል። ወጣቶቹ ሦስት ወር አይቆዩም፤ ሥራውም ይበተናል ስለዚህ መንግስት አሠልጥኖ የውጩንም ሥራ ከሚያውቁ ወይም የሙያው ሰዎች ጋር አብረው ሠርተው በሥራ ላይ እንዲሠለጥኑ ቢያደርግ ወይም ሥራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው አብሯቸው ቢገባ ጥሩ ነው። ያለበለዚያ ግን ለቢዝነሱም ለሥራውም አዲስ የሆነን ሰው ወደ ሥራው ማስገባት ያንን ሰው እንደማጥፋት ነው።  ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ተበድረው ስለሚገቡ እዳም ይኖርባቸዋል ይህ ራሱ ከባድ ነው እንኳን ለአዲስ ለቆየም ሰው ገበያው ላይ ለመወዳደር ከባድ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

ሀሌታው ሀ ኅትመት እና ማስታወቂያ

ድርጅት የተመሠረተው በአቶ ዮናታን ታደሰ እና ሦስት መሥራች አባላት በ2012 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የኅትመት …