መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ለችግሮች መፍትኄ በመፈለግ ለስኬት መብቃት – ዛጎል ዲዛይን

ለችግሮች መፍትኄ በመፈለግ ለስኬት መብቃት – ዛጎል ዲዛይን

ዛጎል ጋርመንት ዲዛይን በመቅደስ ተስፋዬ እና አምስት መሥራች አባላት በ2011 ዓ.ም ተመሠረተ። አሁን ላይ አምስት መሥራች አባላት ናቸው በሥራ ላይ የሚገኙት። ዛጎል ጋርመንት ዲዛይን በሦስት የልብስ ስፌት ማሽኖች ነው ሥራ የጀመረው።

ዛጎል ዲዛየን የሚያመርተው አጠቃላይ የአልባሳት ምርቶችን ነው። እንዲሁም ደንበኛ በሚፈልገው ዲዛይን የሚፈልገውን ዲዛይን ሳምፕል በማምጣት ባመጡት ሳምፕል መሠረት የሚፈልጉትን አልባሳት የሚያመርት ድርጅት ነው።

ዛጎል ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል

  • ሸሚዝ
  • ጃኬት
  • የፅዳት ልብስ
  • የሀበሻ ልብስ
  • ለተለያዩ ዝግጅቶች ቲሸርቶች
  • የጥበቃ ልብሶች
  • እና ጋውኖች በጥራት ያመርታል።

ምሥረታና ዕድገት

ዛጎል ዲዛየን ሲመሠረት በስድስት መሥራች አባላት ነበር የተጀመረው፤ አሁን ግን በሥራ ላይ ያሉት አባላት አምስት ናቸው። ከመሥራች አባላት ሊቀነስ የቻለበት ምክንያት ሲጀመር በነበረው ውጣውረድ ነው።

ወ/ት መቅደስ እንዴት ወደ ልብስ ስፌት ሙያ ሊገቡ እንደቻሉ ሲገልፁ በልጅነት እድሜያቸው ከእናታቸው ጋር አብረው የልብስ ስፌት ሙያ እያዩ ማደጋቸው ለሙያው ፍቅር አንዲኖራቸው ያደረገ ሲሆን ይህም በሙያው እንዲሰለጥኑ እና የልብስ ስፌት ሥራ እንዲጀምሩ አስተዋጽዖ አድርጓል። የልብስ ስፌት ሙያ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር የልምምድ (apprenticeship) ጊዜያቸውን እንደጨረሱ ምንም ጊዜ ሳያባክኑ ሊደራጁ ችለዋል። አብረው የተማሩ የአንድ ትምሕርት ቤት ጓደኛሞች መሆናቸው በቀላሉ ተደራጅተው ሥራ እስኪጀምሩ እና ከጀመሩም በኋላ ነገሮችን እንዳቀለለላቸው ወ/ት መቅደስ ጠቅሰዋል።

ማስፋፋት እና ማስተዋወቅ

ዛጎል ጋርመንት ዲዛይን ሲመሠረት በሦስት ማሽኖች እና በስልሳ ሺህ ብር ብድር ነበር የተመሰረተው፤ በአሁኑ ጊዜ ግን የተበደረውን ብድር በመመለስ አዲስ ካፒታል ከሚባል ድርጅት ሁለተኛ ብድር በመበደር ዘጠኝ ተጨማሪ ማሽኖችን በመግዛት ሊያስፋፋ ችሏል። እንዲሁም ጊዜያዊ ዐሥራ አራት ሠራተኞችን ቀጥሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከኮቪድ በፊት ሰላሳ ዘጠኝ ሠራተኞች በድርጅቱ ሥር ተቀጥረው ይሠሩ እንደነበር ወ/ት መቅደስ አውስተዋል። ድርጅቱ አሁን ባለው አቅሙ በቀን ሦስት መቶ ሸሚዝ የማምረት አቅም አለው። በዚህን ጊዜ ድርጅቱ ሁለት መቶ ሺህ ብር ገደማ ካፒታል ማፍራት ችሏል።

ዛጎል እዚህ ደረጃ ለመድረስ የቻለው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በመነጋገር እየፈታ እንዲሁም ምንም አይነት ችግር ሲያጋጥም ተስፋ ባለመቁረጥ እና ካጋጠሙ ችግሮች በመማር ነው።

ድርጅቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል አንዱ ገበያ ማፈላለግ ሲሆን፤ ሂደቱም በጣም ከባድ ነበር። መርካቶ እየሄዱ ለመሸጥ ሞክረው ነበር፤ አብዛኛዎቹ ደንበኛ አላቸው። ከዛም አልፎ ደግሞ ሥራ ለመስጠት እምነቱ አልነበረም።  እንዲሁም ጥሬ እቃ የሚገኝበትን የተለያዩ ቦታዎች አለማወቅ ሌላው ያጋጠመ ችግር ነበር። ሌላው እና ዋናው ችግር እና ብዙ ዋጋ አስከፍሎአቸው የተማሩበት የጋራ ሥራ ልክ እንደ ግል ሥራ አለመሆኑ እና የሰው ባሕሪ የተለያየ በመሆኑ ማኩረፍ፣ መቅረት የመሳሰሉትን ችግሮች ሥራውንም በጣም በድለውት ነበር። እነዚህን ችግሮች  ተነጋግሮ በመፍታት ድርጅቱ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ መቻሉን ወ/ት መቅደስ ገልጸዋል። እንዲሁም የነበረውን የገበያ ችግር በጅምላ የሚረከብ ደንበኛ በማግኘት አሁን በጥሩ ሥራ ላይ ይገኛሉ። እንደ ማጠቃለያ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በመነጋገር ልምድ እና ተሞክሮ መለዋወጥ በጣም ጠቃሚ እና መፍትኄ የሚያመጣ ነው።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ግዜ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ነበር፤ ትንሽ ለመሥራት የሞከሩ ቢሆንም በነበረው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ነበር። ነገሮች እስከሚስተካከሉ ድረስ የነበረው አማራጭ በሌላ የጋርመንት ድርጀት ውስጥ ሥራ ተቀጥረው መሥራት ነበር። ትንሽ ግዜ ተቀጥረው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ነገሮች ትንሽ ሲረጋጉ ወደ ራሳቸው ሥራ በመመለስ የነበረውን ከባድ ሁኔታ ሊያልፉት እንደቻሉ ወ/ት መቅደስ ገልፅዋል።

ምክር

አዲስ ወደ ልብስ ስፌት የሚገቡ ሰዎች በቅድሚያ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። ቀጥሎ ጥሬ እቃ ከየት ነው የሚመጣው፣ የት ነው የሚገኝው የሚለውን ማወቅ እንዲሁም ሠራተኞችን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ማወቅ እና ተግባብቶ መሥራት መቻል አለባቸው።

አሁን ባለው ሁኔታ በ2merkato የሚሰጥውን የከፍታ (kefta.2merkato.com) የመረጃ አገልግሎች ይጠቀማሉ ወደ ፊት ነገሮች ሲስተካከሉ የጨረታ እና የማስታወቂያ አገልግሎት ለመጠቀም እቅድ አላቸው።

ዛጎል ጋርመንት ዲዛይን ወደ ፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቱ አልባሳት በብዛት ከውጭ የሚመጡ ስለሆነ ዛጎል ጥራቱን የጠበቀ ልብስ በሀገር ውስጥ በማዘጋጀት ገበያው ላይ ተወዳዳሪ መሆን እና በሁለት አመት ግዜ ውስጥ የሚኖሩትን ማሽኖች ቁጥር ከመቶ በላይ ለማድረስ አቅዶ እየሰራ ይገኛል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …