መነሻ / ልምድ እና ተሞክሮ / ዘውዲቱ ሽፈራው ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች አምራች

ዘውዲቱ ሽፈራው ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች አምራች

ዘውዲቱ ሽፈራው ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅት የተመሠረተው በወ/ሮ ዘውዲቱ አያሌው እና በባለቤታቸው በ2008 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ የቆዳ ውጤቶችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል።

ድርጅቱ የሚያመርታቸው ምርቶች

  • የሴቶች ክፍት እና ድፍን ጫማዎች
  • ክፍት የወንድ ጫማ (ነጠላ ጫማዎች)
  • ቀበቶ
  • የተለያየ መጠን ያላቸው ቦርሳዎች
  • የወንድ እና የሴት የኪስ/የዕጅ ቦርሳዎች

ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት

ወ/ሮ ዘውዲቱ ድርጅቱን ከመመሥረታቸው በፊት የጋዜጠኛ ሙያ ይስባቸው ነበር፤ በሙያው ለመሥራት ትንሽ ሞክረው የነበረ ቢሆንም ግን ምንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ይሁን እና ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተሰባቸው ይሠራ የነበረውን የቆዳ ሥራ ዕያዩ በማደጋቸው የቆዳን ሥራ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ወደ ዘርፉ ተቀላቅለዋል።

የድርጅቱ ምርት የማምረት አቅም እንደሚመጣው የሥራ ዲዛይን ዓይነት እና የትዕዛዝ መጠን ቢለያይም፣ ለምሳሌ መካከለኛ መጠን ያለውን ቦርሳ በቀን ዐሥራ ሁለት የመሥራት አቅም አለው። የሚያመርታቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ  ዋጋ ለገበያ ያቀርባል። ለምሳሌ የወንዶች የኪስ ቦርሳ በብዛት ለሚወስዱ በአንድ መቶ ብር (ብር 100)፣ በፍሬ ደግሞ ለሚገዙ በአንድ መቶ ሃምሳ ብር (ብር 150) አያቀረበ ይገኛል። የሴት ደግሞ ከኪስ ቦርሳ ትንሽ በመጠን በለጥ ያሉ ቦርሳዎችን ደግሞ በብዛት ለሚወስዱ በአራት መቶ ሃምሳ ብር (ብር 450)፣ በፍሬ ለሚወስዱ ደግሞ ከአምስት መቶ ሃምሳ ብር (ብር 550) እስከ ስድስት መቶ ብር (ብር 600) ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። በተጨማሪ ድፍን የሴት ጫማዎችን በስምንት መቶ ሃምሳ ብር (ብር 850) ለገበያ ያቀርባል።

ድርጅቱ ሥራዎችን የሚሠራው በዋናነት በሰው በሰው ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ ተረካቢ ነጋዴ ደንበኞች አሉት ከእነሱ በሚመጣ ትዕዛዝ እና በመጨረሻ ደግሞ ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ምርቱን በማስተዋወቅ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

ወ/ሮ ዘውዲቱ ድርጅቱን ሲመሠርቱ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በስምንት መቶ ብር (ብር 800) መነሻ ካፒታል ነበር። ድርጅታቸው አሁን ለአራት ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ የካፒታል አቅሙን ወደ አምስት መቶ ሺህ ብር (ብር 500,000) ማሳደግ ችሏል። እንዲሁም አንዳንድ ለሥራ ቅልጥፍና የሚያግዙ የተሻሉ ጥሬ እቃዎችን መጠቀም ጀምሯል፤ ለምሳሌ የጫማ ሶል ምርቱ የከነመዳሪ ጎማ ነበር የሚጠቀመው ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እና ጉልበትን መቆጠብ ባለመቻሉ ብዙ ምርት እንዳያመርት አድርጎት ነበር። አሁን ቀለል ያለ ጥሬ እቃ በመጠቀሙ የተሻለ ምርት በዐጭር ጊዜ ማምረት ጀምሯል።

የኮቪድ ተፅዕኖ

በኮቪድ ጊዜ ሥራ በጣም ቀንሶ ነበር፤ የዚህም ዋና ምክንያቱ የኤግዚቢሽን እና ባዛር ሙሉ በሙሉ መቆም ነበር። ቢሆንም ድርጅቱ ሠራተኞችን በመቀነስ፣ የተገኘውን ሥራ በመሥራት እና ተመርተው የተቀመጡ ምርቶችን እየተንቀሳቀሱ በመሸጥ የኮቪድ ጊዜን እንደምንም ማሳለፍ ችሏል።

ምክር እና ዕቅድ

ድርጅቱ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ነገሮች ከተስተካከሉ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ የመስፋት ብሎም ሽፍን የወንድ ጫማዎችን እንዲሁም የሌዘር ጃኬቶችን የመሥራት አቅድ አለው። ለዚህም 2merkato.com ለጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያዘጋጀውን የከፍታ አገልግሎት መጠቀም እንደሚጀምሩ የድርጅቱ መሥራች ጠቅሰዋል።

ወ/ሮ ዘውዲቱ ወደ ሌዘር ሥራ ለሚገቡ ሰዎች የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል። “ወደዚህ ሥራ የሚገባ ሰው የሥራ ሥነ ምግባር ሊኖረው ይገባል። ይህም ማለት ለምሳሌ ፕሮግራም ማውጣት፣ ፕሮግራሙ ደግሞ ጠዋት ጥሬ እቃ መግዛት (ቆዳ)፣ ከሰዓት ደግሞ ምርት ማምረት፤ ሌላውንም ቀን እንዳለበት የሥራ ዓይነት ፕሮግራም አውጥቶ በፕሮግራሙ መሥረት መመራት ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ በቆዳ ሥራ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሥራ ላይ ታጋሽ መሆን አስፈላጊ ነው” ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ይህንንም ይመልከቱ

ገዛኸኝ፣ ቃለአብ እና ጓደኞቻቸው እንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ

ድርጅቱ የተመሠረተው በአቶ ገዛኸኝ ተድላ በ2011 ዓ.ም. ነው። ድርጅቱ አጠቃላይ የፈርኒቸር ሥራዎችን ይሠራል፤ ድርጅቱ በአሁኑ …