መነሻ / የቢዝነስ ዜና / አዳዲስ ገፅታ ያላቸው የገንዘብ ኖቶች እና አዲስ የ200 ብር ገንዘብ አገልግሎት ላይ ዋለ

አዳዲስ ገፅታ ያላቸው የገንዘብ ኖቶች እና አዲስ የ200 ብር ገንዘብ አገልግሎት ላይ ዋለ

የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲስ የደህንነት ገጽታዎች እና ሌሎችም መለያዎች የተካተቱባቸው የገንዘብ ዓይነቶችን ለግብይት እንደሚያውል በዛሬው ዕለት ተገልጿል። ነባሮቹ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ዓይነቶች ሙሉ ለሙሉ የሚተኩ ይሆናል። አዲስ የ200 ብር ገንዘብም በተጨማሪነት ለግልጋሎት ይውላል። የ5 ብር ገንዘብ ባለበት ቀጥሎ፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም የሚለወጥ ይሆናል። ይህ የገንዘብ ቅያሪ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ የታለመ ነው። የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ እጥረትን ለመቋቋም እንዲችሉም ያግዛል።

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የሕትመት ሥራ ተገባዶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግምጃ ቤት ይገኛል። የስርጭት ስርዓት እና ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት የሚተገበር ይሆናል። በገንዘብ ቅያሬው ሂደት የጸጥታ ማስከበር አካላት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ያስፈጽማሉ። ከብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ፣ ሂደቱን በበላይነት ያስተባብራል። የክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ኮማንድ ፖስት አቋቁመው ሥራውን እንዲያከናውኑም ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ገንዘቧን የሚወክል ምልክት እንዳልነበራት ይታወቃል። በቅርቡ ለብር መለያ የሚሆን አዲስ ምልክት ተዘጋጅቶ በጥቅም ላይ ይውላል።


የዜና ምንጭ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

 

ይህንንም ይመልከቱ

kefta-care-training-2

ከፍታ ለ20 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ

ከፍታ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለ20 በሴቶች ለሚተዳደሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው ያተኮረው …