ማንኛውም ምርት ወይም አገልግሎት አቅራቢ፣ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ተጠቃሚው “እንዲገዛው” ማድረግ መቻል ይኖርበታል። የአንድ ቢዝነስ ህልውና ቀጣይ ሊሆን የሚችለው ሽያጭ ማከናወን ሲሳካለት ብቻ ነው።
አንድ ምርት ወይም አገልግሎት ጥሩ ሽያጭ እንዲኖረው አንዱ ሁነኛ የሚባለው ዘዴ፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን 4 የሽያጭ ዘዴ ምሰሶዎችን ልብ ማለት ነው።
እነዚህ አራቱ ምሰሶዎች ለሽያጭ ዘዴ መሠረቶች ናቸው።
1. ምርት / አገልግሎት
ተጨባጭ የሆነ የሚቀርብ ምርትም ሆነ “የሚዳሰስ” ያልሆነ አገልግሎት፣ ለደንበኛችን ምን ጥቅም እንደሚሰጠው በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። ምንም እንኳ እንደ ቢዝነስ ገና ለሥራ ስንነሣ የምናስበው ነገር ቢሆንም፣ ለሽያጭ ስንነሣ የእኛ ምርት ወይም አገልግሎት ለደንበኛችን በገቢር ምን እንደሚጠቅመውና ምን ችግር እንደሚቀርፍለት በግልጽ መረዳትም ማስረዳትም መቻል አለብን።
ይህ ነጥብ ለደንበኛችን የምናቀርበው “ምን” እንደሆነ የምንመልስበት ነው።
2. ዋጋ
ዋጋ የምንለው ደንበኛችን ለምርት ወይም አገልግሎታችን የሚከፍለውን ድምር ሂሳብ ነው (የአገልግሎት ጭማሪ ክፍያ ወይም ግብርን ጨምሮ)። ዋጋ ስናወጣ በደንበኛችን ዓይን የእኛ ምርት ወይም አገልግሎት የሚሰጠውን ደረጃ ማሰብ ይኖርብናል። ይህ ሁሉ ሆኖም፣ ዋጋችን ተመጣጣኝና ለደንበኛ አዋጭ ሆኖ መታየት ይኖርበታል።
እንዲሁም፣ ዋጋ ስናወጣ የሚከተሉትን ነገሮች ልብ ማለት አለብን፡-
- የምንሸጠውን ነጠላ ምርት ወይም አገልግሎት ለማምረት ወይም ለማቅረብ ያወጣነውን ወጪ (ግብዓት፣ የሰው ኃይል ወዘተ)
- ቋሚ ወጪዎች (የሠራተኛ ደሞዝ፣ የቤት ኪራይ ወዘተ)
- ግብር / ታክስ
- ተገቢ ነው ብለን የምናስበውን ትርፍ መጠን
ይህ ነጥብ “ስንት” የሚለውን ጥያቄ የምንመልስበትና የምርት ወይም አገልግሎታችንን ዋጋ የምንወስንበት ነው።
3. ማስታወቂያ
የቱንም ያህል ምርጥ የሚባል ምርት ወይም አገልግሎት ቢኖረን፣ ፈላጊው ካላወቀልን ጥቅም የለውም። ማስታወቂያ ስንል፣ በአጭሩ ስለ ምርት ወይም አገልግሎታችን ተጠቃሚው እንዲያውቅ ማድረግ ነው። ለማስተዋወቅ ስንነሣ፣ እንደ ግብ ያተኮርንበት ደንበኛ እንዴት ያለ እንደሆነና እንዴት ልናገኘው እንደምንችል ማሰብ ይኖርብናል።
ልናገኘው እንደምንፈልገው ደንበኛ ዓይነት የማስታወቂያ ሰሌዳ፣ የበር ለበር ማስተዋወቅ፣ የሬዲዮ ማስታወቂያ፣ የኢንተርኔት ማስታወቂያ (እንደ ፌስቡክ ባሉ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች) የመሳሰሉትን፣ እንዲሁም እንደ ባዛር ያሉ የሽያጭ መድረኮችን እንደማስተዋወቂያ ልንጠቀም እንችላለን።
ይህ ነጥብ “ለምን” የሚለውን ጥያቄ የምንመልስበትና ደንበኛችን የእኛን ምርት ወይም አገልግሎት እንዲገዛ የምናሳምንበት ነው።
4. ቦታ
ቦታ ስንል፣ ደንበኛችን ምርት ወይም አገልግሎታችንን የሚያገኝበትን ቦታ ማለታችን ነው። የቦታ ምርጫችን ለደንበኛችን የተስማማ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል። በባዛር የምንሳተፍ ከሆነ የምንሳተፍበት አካባቢ፣ የሽያጭ ቦታችን (ከመሥሪያ ቦታችን የተለየ ከሆነ) የመሳሰሉት ለደንበኞች ምቹ መሆናቸውን ማሰብ ይኖርብናል። ከሌሎቹ ነጥቦች በተጨማሪ በምንገኝበት ቦታ ተመራጭ ለመሆን መጣር ያስፈልገናል።
ከቦታ ምርጫችን በተጨማሪ፣ የምርት ወይም አገልግሎት ማቅረቢያ ቦታችንን እንዴት ይዘነዋል የሚለው ራሱ ደንበኞችን ሊስብ ወይም ሊያሸሽ ይችላል። ደረጃውን የጠበቀ፣ ንጹሕ፣ በሚገባ የተደራጀና “ይሄስ ጥርት ያለ ቦታ ነው” የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ አድርገን ቦታንን መያዝ ለሽያጭ/ገበያ ስኬታችን ሌላው ወሳኝ ነጥብ ነው።
ይህ ነጥብ “የት” የሚለውን ጥያቄ የምንመልስበትና ደንበኛችን ምርት ወይም አገልግሎት የሚያገኝበት ቦታ እንዴት ያለ እንደሆነ የምንወስንበት ነው።
እነዚህ አራት ምሰሶዎች (ምርት / አገልግሎት፣ ዋጋ፣ ማስታወቂያ እና ቦታ) አንዳቸው ወይም ጥቂቶቹ ለብቻቸው ብዙም ለስኬት እንደማይበጁን ማስተዋል አስፈላጊ ነው። የአራቱንም ሚዛን መጠበቅ፣ አራቱንም ምሰሶዎች ማጠንከር ሁሌም ያስፈልጋል።