agar-microfinance

አጋር ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ.

አጋር ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ. መጋቢት 9 ቀን፣ 1996 ዓ.ም.  ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ አግኝቶ የባንክ የፋይናንስ  አገልግሎት ለማያገኙ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች የቁጠባና የብድር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ኩባንያ ነው። ተቋሙ ከተመሠረተ ከ17 ዓመታት በላይ በሥራው ላይ የቆየ ሲሆን አጥጋቢ የሥራ ልምድ ከማካበቱም በላይ በአሁኑ ወቅት ቅርጫፎቹን ወደ ሃያ ሁለት አሳድጓል። ኩባንያው የሥራ እንቅስቃሴውን የበለጠ በማስፋት ኅብረተ ሰቡን ለማገልገልና ባለአክሲዮኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ ካፒታሉን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ ላይ ይገኛል።

አጋር ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ. ራዕይ እና ተልዕኮ

ራዕይ

በኢትዮጵያ ውስጥ አምራች ዜጎችን የሚያገለግል ተመራጭና ግንባር ቀደም የማይክሮፋይናንስ ተቋም መሆን ነው።

ተልዕኮ

የሠለጠኑና ትጉ ሠራተኞችን በማሰማራት፣ የተሻለ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ እንዲሁም ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ተመጣጣኝና ፈጣን የፋይናንስ አገልግሎትን በቀጣይነት ለአምራች ዜጎች በማቅረብ ኑሮአቸውን ማሻሻልና ለባለአክሲዮኖች ትርፍ ማስገኘት ነው።

አጋር ማይክሮፋይናንስ አ.ማ. የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምን ምን ናቸው?

የግዴታ ቁጠባ (Compulsory Saving)

ይህ የቁጠባ ዓይነት ተበዳሪዎች በሚወስዱት ጊዜ የብድሩን 4%፣ 6% ወይም 10% በማስቀመጥ የሚጀምሩትና በየወሩ ብድሩን ሲከፍሉ ብር 10፣ 30፣ ወይም ብር 40 እየቆጠቡ የሚያሳድጉት ነው። ኩባንያው ለዚህ ዓይነት ቁጠባ በዓመት 7% ወለድ ይከፍላል።

የፈቃደኝነት ቁጠባ (Voluntary Savings)

ይህ የቁጠባ ዓይነት ተበዳሪ የሆኑና ያልሆኑ ደንበኞች በማናቸውም ጊዜ ከብር 20 ጀምሮ ገንዘባቸውን ለማስቀመጥና ያስቀመጡትንም ወጪ ለማድረግ የሚችሉበት የቁጠባ አገልግሎት ሲሆን ኩባንያውም በዓመት 8% ወለድ ይከፍላል።

ልዩ ቁጠባ (Special Savings)

ይህ የቁጠባ ዓይነት በብር 10ሺ እና ከዚያ በላይ በማስቀመጥ የሚጀምርና የተሻለ ወለድ የሚያስገኝ የቁጠባ ዓይነት ነው። ወለዱም በዓመት 9.5 % ሲሆን በተቀማጭ ሒሳብ ላይ በየወሩ እየታሰበ የሚደመር ይሆናል።

የሙዳይ ቁጠባ (Muday Saving)

ይህ የቁጠባ ዓይነት ብር 100 መክፈቻው ይሆንና በሥራ ቦታቸውና በቤታቸው በመሆን ድርጅቱ ያዘጋጀውን የሙዳይ ሳጥን ተረክበው የሚቆጥቡት ቁጠባ ሲሆን ኩባንያውም በዓመት  8% ወለድ ይከፍላል።

የጊዜ ገደብ ቁጠባ (Time Deposit Saving)

የጊዜ ገደብ ቁጠባ ብር 300ሺ እና ከዚያ በላይ በማስቀመጥ የሚከፈት የቁጠባ ዓይነት ሲሆን ወለድ በዓመት ከ9.5% ጀምሮ ገንዘቡ ባደገ መጠን በድርድር የሚያድግ የተሻለ ወለድ ማግኘት ይቻላል። ወለዱም በዓመት አንዴ መጨረሻ ላይ ታስቦ የሚደመር ይሆናል።

የጥቃቅን ንግድ ሥራ ብድር

ይህ የብድር ዓይነት በጥቃቅን ንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች የሚሰጥ ብድር ሲሆን ከብር 1,000.00 እስከ 70,000.00 ድረስ ይሰጣል። ተበዳሪዎች 6 ወር የሞላው ንግድ ፍቃድ ሊኖራቸውና ለብድሩ ተመጣጣኝ የሆነ ዋስትና ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

የአነስተኛ ንግድ ሥራ ብድር

ይህ የብድር አገልግሎት በልዩ ልዩ ንግድ አገልግሎት ሰጪና የማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚሰጥ ሲሆን እስከ ብር 600,000.00 ይደርሳል። ተበዳሪዎች የንግድ ፍቃድ ሊኖራቸውና ለብድሩ ተመጣጣኝ የሆነ ዋስትና ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

የሴቶች ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ( WEDP) ብድር

ይህ የብድር አገልግሎት በተለየ መልኩ በንግድ ሥራ ላይ ለተሠማሩ ሴቶች የሚሠጥ ሲሆን ከብር 50,000.00 እስከ 900,000.00 ድረስ ይሠጣል።

የፍጆታ ብድር

ይህ የብድር አገልግሎት በተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው ለሚሠሩ ሠራተኞች የሚሰጥ የግል እና የቡድን ብድር ነው። የብድር መጠኑም በሠራተኞቹ ደመወዝ 1/3ኛ ላይ የተመሠረተ ሲሆን እስከ ብር 50,000.00 የሚደርስ ነው።

የሊፍት ብድር (LIFT LOAN)

ይህ የብድር አገልግሎት የ2ኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸውን በዋስትና በማስያዝ የእርሻ ሥራቸውን ለማስፋፋትና ለማዘመን እንዲያስችላቸው የሚሰጥ የብድር ዓይነት ሲሆን የብድር ጣሪያው ብር 50,000.00 ነው።

ለኢነርጂ አገልግሎት የሚሰጥ ብድር (Energy Loan)

የኢነርጂ አገልግሎት ብድር በእርሻ ሥራ ለሚተዳደሩና የእርሻ ሥራ ለሚሠሩ ተበዳሪዎች በቡድን በመደራጀት በጠለፋ ዋስትና፣ አሊያም በግል የሚሰጥ የብድር ዓይነት ነው።

የባዮ ጋዝ ብድር (Biogas Loan)

ይህ የብድር አገልግሎት አርሶ አደሩ ለባዮጋዝ ግንባታ የሚጠቀምባቸውን ግብዓቶች ለመግዛት የሚውል ሲሆን በእርሻ ሥራ ለሚተዳደሩ ተበዳሪዎችና የእርሻ ሥራ ለሚሠሩ በቡድን በመደራጀት በጠለፋ ዋስትና የሚሰጥ የብድር ዓይነት ሆኖ የሚሰጠውም ብድር ጣሪያ እስከ ብር 15,000.00 ይደርሳል።

የሶላር ኢነርጂ ብድር (Solar Energy Loan)

ለሶላር ኢነርጂ የሚጠየቀው ብድር የሚወሰነው በደንበኛው ፍላጎትና የቴክኖሎጂ አቅራቢው ድርጅት ለየምርቱ በሚሰጠው ዋጋ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ የብድር አገልግሎት በእርሻ ሥራ ለሚተዳደሩና የእርሻ ሥራ ለሚሠሩ ተበዳሪዎች አማራጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት አንዲችሉ በቡድን በመደራጀት በቡድን የሚሰጥ ሲሆን በጠለፋ ዋስትና፤ በግል ሲሆን ደግሞ ተበዳሪዎች የ2ኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸውን በዋስትና በማስያዝ የሚሰጥ የብድር ዓይነት ነው።  የሚሰጠውም ብድር ጣሪያ እስከ ብር 25,000.00 ይደርሳል።

የግብርና ብድር

የግብርና ብድር ለአርሶ አደሩ የሚሰጥ ብድር ሲሆን ከብር 1,000.00 እስከ 25,000.00 ይደርሳል።

የግንባታ ብድር

ይህ ብድር የሚሠጠው የቤት ግንባታ ለሚያካሄዱ ሲሆን የሚሠጥውም ብድር ከብር 10,000.00-400,000.00 ድረስ ይደርሳል። ተበዳሪዎች ለብድሩ መክፈያ የሚሆን የገቢ ምንጭ ሊኖራቸውና ተመጣጣኝ ዋስትና ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

የኢዱ ፋይናንስ ብድር(Edu-Finance Loan)

ይህ የብድር አገልግሎት ለወላጆች ወይም ለአሳዳጊዎች ለልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ የሚሆን ብድር፣ ለትምህርት ቤት ማስፋፊያ የሚሆን ብድር፣  ለአስተማሪዎች ትምህርት ማሻሻያ የሚሆን ብድር ሲሆን ከብር 3,000.00 እስከ 1,000.000.00 ድረስ ይሠጣል።

የአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች ብድር (Small and Medium Enterprises - SME)

በዚህ የብድር አገልግሎት ላይ የሚካተቱት የንግድ ሥራ መስኮች የተለዩና የተመረጡ የሥራ ዘርፎች ናቸው። እነሱም፦
    • የማምረት ሥራ (Manufacturing)
    • የማቀነባበር ሥራ (Agro-processing)
    • ቱሪዝም (Tourism)
    • የሕንጻ ግንባታ ሥራ (Construction)
ሲሆኑ የድርጅቱን ባለቤት ጨምሮ ቢያንስ 7 እና ከዚያም በላይ የሆኑ ሠራተኞችን ላካተቱ የንግድ ድርጅቶች (Enterprises) የሚሰጥ ብድር ነው። የብድር መጠኑም ከብር 150,000.00 እስከ 1,500.000.00 ድረስ ይሰጣል።

አጋር ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ. አድራሻ

ዋና መሥርያ ቤት

አዲስ አበባ ከተማ፣ ልደታ ክፍለ ከተማ፣ ባልቻ ሆስፒታል ጀርባ፣ ዳማ ሀውስ ሕንጻ፣ 3ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 306፣ 307፣ 308፣ 310 ላይ ይገኛል።

ስልክ ቁጥር

  • 011 5578232
  • 011 5577232

ማስታወሻ፦ ይሄ መረጃ የተዘጋጀው አጋር ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ በአካል ሄዶ በመጠየቅ በተገኘው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ድርጅቶች በሚጠቅም መልኩ ተቀናብሮ ነው።

ይህንንም ይመልከቱ

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ.

ኒኦ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባገኘው ፈቃድ መሠረት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ …